ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጠመንጃ እና ወታደራዊ ሬዲዮ የያዘ ወታደር
የምስሉ መግለጫ,የአይኤስ ታጣቂዎች በአገሪተ ተራራማ አካባቢዎች ካምፖቻቸውን ካደራጁ በኋላ የአገሪቱ ወታደሮች ዘመቻ ከፍተውባቸዋል

17 መጋቢት 2026

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በሶማሊያ የአል-ሚስካድ ተራሮች በሚገኙበት ስፍራ አንድ የወታደሮች ቡድን በእጃቸው ላይ በያዙት ኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ ተሰባስበው ከድሮን በሚያገኙት መረጃ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ተዋጊዎችን እንቅስቃሴ ይከታተላሉ።

በያዙት መሳሪያ ላይ በሸለቆው ውስጥ የሚሹለከለኩ ሰዎች አይተዋል።

“ለጓደኞቹ ውሃ ለመቅዳት እየሄደ ነው” ይላል የድሮን ኦፕሬተሩ። ሌላው ደግሞ “በጀርባው የሆነ ነገር ይዞ እየሮጠ ነው” ሲል ይናገራል።

በስክሪኑ ላይ የሚታየው ሰው ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የአይኤስ ታጣቂዎች መደበቂያ እንደሆነ የሚታመንበት ዋሻ አጠገብ ነው ያለው።

በዚህ ሰፈር የፑንትላንድ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ 500 የሚያህሉ ወታደሮችን አሰፍሯል።

ከአስር ዓመታት በፊት በዚህ በረሃማ እና ለመኖር ምቹ ባልሆነው መልክዓ ምድር ጥቂት አርብቶ አደሮች ብቻ ይገኙበት ነበር። ነገር ግን አይኤስ ተዋጊዎቹ ከሶሪያ እና ኢራቅ ተባርረው ትኩረቱን ወደ አፍሪካ በማዞር እዚህ ቦታ ላይ ታጣቂዎቹን ሲያሰፍር ያ ተቀየረ።

በአወሮፓውያኑ ሚያዚያ 2025፣ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ የነበሩት ጄነራል ማይክል ላንግሌይ ለአሜሪካ ኮንግረስ “አይኤስ ዓለም አቀፍ መረቡን ከሶማሊያ ይቆጣጠራል” ሲሉ ተናገረው ነበር።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ አሜሪካ ሶማሊያ ከአይኤስ ጋር የምታደርገውን ውጊያ ደግፋለች። በሶማሊያ ዋሻዎች ውስጥ ተደብቀው የነበሩትን አማፂያን በተደጋጋሚ በቦምብ የደበደበች ሲሆን፣ በ2025 የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን ሶማሊያ ውስጥ በሚገኙ የአይኤስ ዒላማዎች ላይ 60 ጥቃቶችን ፈጽሟል።

ከአይኤስ የተማረኩ የጦር መሣሪያዎች እና ባንዲራ
የምስሉ መግለጫ,የፑንትላንድ ኃይሎች የኤእ ኤስ ባንዲራን እና መሣሪያዎች በየካቲት 2025 ባደረጉት ውግያ ማርከዋል

አሁን አይኤስ “በሶማሊያ ጥቃቶችን የማካሄድ አቅሙ ቀንሷል” እና “ዛሬ ለፑንትላንድም ሆነ ለሶማሊያ ጉልህ ስጋት አይፈጥርም” ትላለች በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፀረ-ሽብርተኝነት ፖሊሲ ማዕከል ዳይሬክተር ትሪሲያ ቤከን።

ይሁን እንጂ በሶማሊያ የሚገኘው አይኤስ አሁንም “እንደ አፍጋኒስታን ባሉ ሌሎች የኢስላሚክ ስቴት ተባባሪዎች ላይ ሃብትን ማሰባሰብ፣ ድጋፍ መስጠት እና አስፈላጊ ነገሮችን በማመቻቸት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል” ስትል አስረድታለች።

በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው የፑንትላንድ ከፊል ራስ ገዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው አይኤስ-ሶማሊያ የተመሠረተው አብዱልቃድር ሙሚን በተባለ ሶማሊያዊ ነው። ይህ ግለሰብ በአንድ ወቅት በስዊድን እና በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ይኖር የነበረ ሲሆን የብሪታኒያ ዜግነትም ነበረው።

በአውሮፓውያኑ 2015 ከ17 ሰዎች ጋር በመሆን ለአይኤስ ያለውን ታማኝነት ሲገልጽ በተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ ታይቷል።

ሙሚን ቀደም ሲል ለሁለት አስርት ዓመታት መንግሥትን ሲዋጋ የቆየው እና አሁንም የደቡብ ሶማሊያን ሰፊ ክፍሎችን የሚቆጣጣረው የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን አባል ነበረ።

አይኤስ-ሶማሊያ አልሸባብን ከፑንትላንድ አል-ሚስካድ ተራሮች በማስወጣት ከተለያዩ አገራት የተመለመሉ ግለሰቦችን በማምጣት ቀስ በቀስ ለአይኤስ ሰፊ የሥልጠና እና የገንዘብ ማዕከል አደረገው።

ቡድኑ በቦሳሶ የወደብ ከተማ ላይ ጫና የሚፈጥር ሲሆን፣ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሪፖርት በ2022 አይኤስ-ሶማሊያ “ከአካባቢው ንግዶች፣ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች፣ ከከብት እርባታ እና ከግብርና በግዴታ ከሚሰበስባቸው ክፍያዎች 2 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል” ብሏል።

የፑንትላንድ ጦር በ2025 መጀመሪያ ላይ አይኤስ-ሶማሊያን ከቦሳሶ ማስወጣት ቢችልም፣ ታጣቂ ቡድኑ በአቅራቢያው ባሉ የአል-ሚስካድ ተራሮች ውስጥ መንደሮችን እና ትናንሽ ከተሞችን አሁንም ይቆጣጠራል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ዳርዳር ሲሆን፣ 600 ሰዎች ይኖሩበት ነበር።

ወደ መንደሯ ከአይኤስ ጋር ጭካኔ እና ፍርሃት መጣ።

ካርታ

የመንደሪቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት በአቅራቢያው ባለ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ወንዶች እና ሴቶች በሕዝብ ፊት እንዳይቀላቀሉ፣ ወንዶች ከቁርጭምጭሚታቸው በታች ሱሪያቸውን እንዳያስረዝሙ ወይም የፀጉር አቆራረጣቸውን እንዳያሳምሩ የሚከለክሉ ጥብቅ ደንቦች ተጽፏል።

ሴቶች ደግሞ እጆቻቸውን እና ቁርጭምጭሚቶቻቸውን የሚሸፍን ጓንት እንዲሁም ካልሲ ያለው የተለየ ሂጃብ መልበስ እንዳለባቸው ሰፍሯል፤ እንዲሁም ሙዚቃ መስማትም የተከለከለ ነው።

የቡድኑ ጨካኝ አገዛዝና ርዕዮተ ዓለም ጠባሳ አሁንም በጉልህ ይታያል።

“ሕይወት በጣም አስቸጋሪ ሆነች” ይላሉ ሰዒድ መሐመድ ኢብራሂም የተባሉ የአካባቢው ኢማም በመስጂዳቸው ወለል ላይ ተቀምጠው። “ሰዎች ፈርተው ነበር። አንዳንዶቹ ታፍነው ተወስደው እስካሁን ያሉበት አይታወቅም።”

አንዳንድ ሰዎች መንደሩን ለቅቀው ሲሄዱ እርሳቸው ግን እዚያው ለመቆየት ወሰኑ፣ ነገር ግን አይኤስ ከመስጂዱ እንዳባረሯቸው ይናገራሉ።

“‘እኛ አሁን ኢማም ነን። መመሪያችንን ካልተከተልክ እና መስጂዱን አሁኑኑ ለቅቀህ ካልወጣህ የሚገባህን ታገኛለህ’ አሉኝ።”

“ይህ ማለት አንገቴን እንደሚቀሉኝ ወይም እንደሚያግቱኝ መናገራቸው እንደሆነ ተረድቻለሁ።”

በመስጂዱ ውስጥ ከሚገለገሉት መካከል ማሃድ ጃማ አንዱ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የእህቱ ልጅ ሹክሪ በአይኤስ ታጣቂዎች ታፍና ተገድላለች።

ራሱን ከቀትር ፀሐይ ለመከላከል በጥቁር እና ነጭ ሻርፑ ጭንቅላቱን ሸፍኖ “ጥሩ ልጅ ነበረች፣ በጣም የምትወደድ ልጅ ነበረች፣ እናቷን ትንከባከብ ነበር። ሃይማኖቷን የምትወድ ሙስሊም ነበረች” ይላል።

ሹክሪ ስትገደል ነፍሰ ጡር ነበረች። ሁለት ልጆችን እና ታማሚ እናቷን ጥላ ነው የሞተችው።

ጃማ አክሎም “የእህትህን ልጅ ማጣት የሚፈጥረውን ስሜት መገመት አትችልም… እና ደግሞ ለምን እንደተገደለች እንኳን አታውቅም። የልጅ ሞት ዜና ሲደርስህ መቀበል ፈጽሞ የማይቻል ነው” ሲል ተናግሯል።

ሹክሪ፣ ሳይድ የሚባል የሰባት ዓመት ልጅ ነበራት። ትንሹ ልጅ መስማት ስለማይችል ከእናቱ ጉያ የሚርቀው እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ነው። አይኤስ ወደ ቤታቸው በመጣበት ምሽት ከእሷ ጋር ነበር፤ እናም እሱም ተገደለ።

ለብዙ ወራት ከተካሄደ ውጊያ በኋላ፣ መንደሩ በየካቲት 2025 በፑንትላንድ የመከላከያ ኃይል ቁጥጥር ሥር ገባ። አሜሪካውያን በግንቦት 2024 ሦስት የአይኤስ ታጣቂዎችን ዒላማ በማድረግ እና በመግደል አግዘዋል።

አግሮቹን አጣምሮ የተቀመጠ ሰው
የምስሉ መግለጫ,ማሃድ ጃማ አይኤስ ከሁለት ዓመት በፊት የወንድሙን ልጆች አግቶ መግደሉን ይናገራሉ

ይሁን እንጂ፣ አይኤስ አሁንም በአካባቢው የጦር ሰፈሮች አሉት።

ወታደሮች በተረራው ላይ በሚገኝ ምሽጋቸው ሆነው ከአይኤስ ጋር ግጭት ሊቀሰቀስ መሆኑን ሲሰሙ ስሜታቸው ተለዋውጦ መሳሪያዎቻቸውን ማዘገጃጀት ጀመሩ።

የ32 ዓመቷ ወታደር ሙና አሊ ዳሂር በአካባቢው ከሚገኙት ጥቂት ሴት ወታደሮቹ መካከል አንዷ ነች።

ከዚህ በፊት በተካሄዱ ጦርነቶች ተሳትፋለች። “በብርቱ ተዋግተን አሸንፈናል…ምክንያቱም ይህ የእኛ መሬት ነው” ትላለች።

አሁን ግን በጦርነቱ ሊጎዱ ለሚችሉ ሰዎች የሚሆን ነገር ለማዘጋጀት በካምፕ ቆይታለች።

አንድ ወጣት ወታደር የማረከውን የአይኤስ ተዋጊ ክንድ ይዞ የሚያሳይ ፎቶ ከስልኩ ላይ አውጥቶ ለቢቢሲ ጋዜጠኞች አሳይቷል። ምርኮኛው ከእርሱ የሚረዝም እና ግዙፍ ሲሆን፣ ወፍራም ጥቁር ጢም እና ረጅም ፀጉር አለው። ሌላ ወታደር ደግሞ የምርኮኛውን ሌላኛውን ክንድ ይዟል።

“ይህ ሐሰን ነው። ቱርካዊ ነው” ይላል የ24 ዓመቱ አብዲኬር አብዲሪዛ ጃማ።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ ወር 2025 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢስላሚክ ስቴት ቡድን በሶማሊያ እስከ 800 የሚደርሱ ተዋጊዎች አሉት በማለት ግምቱን አስቀምጧል።

ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ናቸው።

የፑንትላንድ ጦር ባለፉት 16 ወራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአይኤስ አባላትን እንደገደለ በመግለጽ ከኢትዮጵያ፣ ከሞሮኮ፣ ከሶሪያ እና ሌሎች ከ50 በላይ አገራት የመጡ የቡድኑ ተዋጊዎችን መማረካቸውን የሚያሳይ ምሥል ይፋ አድርጓል።

የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እነዚህ የተማረኩ ተዋጊዎች ለፍርድ ይቀርባሉ፤ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የሞት ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ቀደም ሲል በፍትሕ ሂደቱ እና የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን አባል ናቸው ተብለው የተከሰሱ እስረኞች አያያዝ ላይ ያለውን ስጋት አንስቷል።

በ2022 የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ሶማሊያ “ለጥያቄ በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች መብታቸው በተጠበቀ መንገድ” መያዛቸውን ለማረጋገጥ በትብብር እየሠራች ነው ብሏል።

ቁጢጥ ብላ የተቀመጠች ሴት
የምስሉ መግለጫ,ሙና አሊ ዳሂር በፑንትላንድ መከላከያ ኃይሎች ውስጥ በመሆን አይኤስን ከሚዋጉ ጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ ናት

አብዲካሂር ጃማ አይኤስ ወደ አካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ የ14 ዓመት ልጅ ነበር። “እንዳሉ አላምንም ነበር። መጀመሪያ ላይ ፕሮፓጋንዳ ብቻ እንደሆነ አስቤ ነበር” ይላል። “ግን አንዱን ስይዝ… የውጭ ተዋጊዎች አገራችንን እያጠቁ እንደሆነ ተገነዘብኩ።”

ቢቢሲ በስፍራው ቃለ መጠይቅ እያደረገ በነበረበት ወቅት በካምፑ ውስጥ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበር። ከባድ መትረየሶች እና ቁሳቁሶች በግመሎች ላይ ተጭነው ወታደሮች በትናንሽ ቡድኖች ከካምፑ ወጥተው በአይኤስ ቦታዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ይጓዛሉ።

የጦር አዛዡ አንድ የአሜሪካ የስለላ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መረጃ እየሰበሰበ መሆኑን እና ይህም የት ጥቃት መፈጸም እንዳለበት ለማወቅ እንደሚረዳ ገልጿል።

የሞርታር ጥይቶች በሸለቆው ውስጥ ይሰማሉ፣ የአይኤስ ዋሻዎችን የሚደበድቡ ፍንዳታዎችም ከተራራው ማዶ ያስተጋባሉ። ምንም ዓይነት የመልስ ተኩስ አይሰማም።

ከተወሰነ ሰዓት በኋላ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለመገምገም ድሮኗ እንደገና ወደ ስፍራው ቅኝት እንድታደርግ ተላከች። ወታደሮች በያዙት በትንሿ ስክሪን ላይ የዋሻው መግቢያ በእሳት ሲነድ ይታያል።

ቀደም ሲል በሸለቆው ውስጥ ሲሮጥ የታየው ሰው አሁን የለም። ከተራራው አናት ወደ ታች በመመልከት ጥቃቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበር ማወቅ አይቻልም።

በኋላ ላይ የፑንትላንድ መከላከያ ሠራዊት የአሜሪካ ድሮኖች ጥቃት በመፈጸም በዋሻዎቹ ውስጥ ተዋጊዎችን መምታታቸውን መረዳት ችሏል። ስንት ተዋጊዎችን ዒላማ እንደተደረጉ ግን ግልጽ አይደለም።

በሶማሊያ ከአይኤስ ጋር የሚደረገው ውጊያ ገና አላበቃም።

በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ የምትገኘው ትሪሲያ ቤከን “አይኤስ-ሶማሊያ በአሁኑ ጊዜ አቅሙ የተገደበ ቢሆንም… ከኪሳራ ማገገምና እንደገና መሰባሰብ የሚችል ጠንካራ ድርጅት መሆኑን አረጋግጧል” ስትል ታስጠነቅቃለች።

አብዱልከሪ ጃማም “የመጨረሻው ተዋጊ እስኪያዝ ድረስ መዋጋታችንን አናቆምም” ይላል።

“10 ወይም 15 ዓመታት ቢፈጅም፣ የትም ቦታ ቢንቀሳቀሱ ወይም ቢደበቁ እንሄዳለን። አካባቢው ሙሉ በሙሉ ሲጸዳ ብቻ ነው የምናርፈው።”

ይህ በእንዲህ እንዳለ እርሱ እና ሌሎቹ ወታደሮች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መኖራቸውን ቀጥለዋል።

ንጹህ የመጠጥ ውሃ ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል የለም፤ በዛፍ ቅርንጫፎች ስር በተወጠሩ ሸራዎች እና በአለቶች መካከል በተገነቡ ጊዜያዊ ድንኳኖች ውስጥ ይተኛሉ። ኑሯቸውን የሚገፉት በሚያረቧቸው ፍየሎች እና በቀን ሁለት ጊዜ በሄሊኮፕተር በሚመጣላቸው እርዳታ ነው።

በጦርነቶች መካከል በሚገኙ አፍታዎች ዳሂር ቤተሰቧ ጋር ትደውላለች። ስምንት ልጆች ያሏት ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ያየቻቸው።

ልጆቿ ሞራሏ እንደሆኑ ትናገራለች።

“እነሱ ‘እናቴ እየመጣች ነው እናሸንፋለን’ ይላሉ። ይህም ትክክለኛውን ነገር እያደረግኩ እንደሆነ እንዲሰማኝ ያደርጋል። የዚህች አገር ባለቤት እኔ ነኝ፤ የወረሯትም ተሳስተዋል።”

ወታደራዊ ልብስ የለበሰ ተዋጊ በተራራ አናት ላይ ሆኖ ቅኝት ሲያደርግ
የምስሉ መግለጫ,አብዲካሂር ጃማ “የመጨረሻው ተዋጊ እስኪያዝ ድረስ ውጊያችንን አናቆምም” ይላል