ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ዜሌንስኪ

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ተደጋጋሚ ትችት ካቀረቡ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ እና ሰር ኪር ስታርመር ተገናኝተው ልዩነታቸውን እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ።

ዜሌንስኪ ከዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ከተወያዩ በኋላ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ምንም እንኳ ትራምፕ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገር ባይችሉም ሁለቱ መሪዎች “ግንኙነታቸውን እንደገና ለማስቀጠል” ተገናኝተው መነጋገር አለባቸው ብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ አልቻሉም በሚል ከስታርመር እና ሌሎች የኔቶ አጋሮች ጋር የዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል።

ዜሌንስኪ በምዕራባውያን መሪዎች መካከል የሚኖር መከፋፈልን አስጠንቅቀው፣ በኢራን የሚካሄደው ጦርነት ዩክሬን ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል “መጥፎ ስሜት አለኝ” ብለዋል።

“ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከስታርመር ጋር እንዲገናኙ በጣም እፈልጋለሁ… የጋራ አቋም እንዲኖራቸው” ብለዋል።

ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ስታርመርን “ዊንስተን ቸርችል አይደለም” ካሉ በኋላ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር “ጥሩ ሰው” እንደሆኑ ቢያስቡም “ተስፋ እንደቆረጡ” ተናግረዋል።

ሰር ኪር በምላሹ እንግሊዝ ወደ ሰፊ ጦርነት ተስባ እንደማትገባ አጥብቀው የገለጹ ሲሆን፣ ጽህፈት ቤታቸው ደግሞ “ዘላቂ” የአሜሪካ እና የዩኬ ግንኙነት እንደቀጠለ ነው ሲል በድጋሚ ገልጿል።

ዜሌንስኪ በተጨማሪም የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በዩክሬን ጦርነት ላይ ስላለው ተጽእኖ “በጣም መጥፎ ስሜት” እንዳላቸው ተናግረዋል። በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል የሚደረጉ የሰላም ድርድሮች “በቋሚነት እየተራዘሙ ነው። አንድ ምክንያት አለ፤ ያም የኢራን ጦርነት ነው።”

ዜሌንስኪ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ እያደረጉ
የምስሉ መግለጫ,ዜሌንስኪ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በዩክሬን ጦርነት ላይ ስላለው ተጽእኖ “በጣም መጥፎ ስሜት” እንዳላቸው ተናግረዋል

ሰር ኪር ማክሰኞ ዕለት ዜሌንስኪን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዜሌንስኪ ባለፈው ሳምንት ፓሪስን ከጎበኙ በኋላ ረቡዕ ዕለት ወደ ማድሪድ ተጉዘዋል። ጉብኝቶቹ የመጡት የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ላለፉት አራት ዓመታት እያካሄደችው ያለውን ጦርነት ከጋረደ በኋላ ነው።

“ትኩረቱ በዩክሬን ላይ መሆን እንዳለበት ግልጽ መሆን በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል” ሲሉ ሰር ኪር ተናግረዋል።

የዩክሬኑ መሪ ዜሌንስኪ ለንደን በነበራቸው ጉብኝት ወቅት በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

“በሩሲያ እና በኢራን ያሉት አገዛዞች በጥላቻ ውስጥ ያሉ ወንድማማቾች ናቸው፤ ለዚህም ነው ጦር መሳሪያ የታጠቁ ወንድማማቾች የሆኑት” ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል። “በጥላቻ ላይ የተገነቡ አገዛዞች በምንም ነገር በጭራሽ እንዳያሸንፉ እንፈልጋለን። እናም እንዲህ ዓይነቱ አገዛዝ አውሮፓን ወይም አጋሮቻችንን የሚያስፈራራ እንዲሆን አንፈልግም።”

የዜሌንስኪን ንግግር በመድረኩ ተገኝተው ከተከታተሉት መካከል ሰር ኪር፣ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩት፣ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ይገኙበታል።