ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የሁቲ ታጣቂዎች

ከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከሁለት ሳምንት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ እንዲሁም ቴህራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ፤ በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሁቲ ባልተለመደ መልኩ የተዐቅቦ አቋም ወስዷል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የሁቲው መሪ አብዱልማሌክ አልሁቲ አጋርነታቸው እየገለጹ ያሉት በየዕለቱ በሚያሰሙት በረመዳን ንግግር ላይ ብቻ ነው።

የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ በመገደላቸው የሐዘን መልዕክት ከማሰማት እንዲሁም ሁቲ በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ኢራንን የሚደግፍ ሰልፍ ከመጥራት የዘለለ እርምጃ አልወሰዱም።

የአማጺ ቡድን መሪው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት የካቲት 26/2018 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር “ጣቶቻችን ቃታው ላይ ናቸው” በማለት የንግግር ድጋፋቸውን ወደ ማስጠንቀቂያ ከፍ አድረገውት ነበር።

ነገር ግን እስካሁን ለኢራን ድጋፍ ለመስጠት ሲባል ምን ዓይነት ጥቃት እንደሚፈጸም የሚያሳይ ዕቅድ ስለመኖሩ አልጠቆሙም።

የአሁኑ ቁጥብነት የጋዛ ጦርነት በተጀመረ በቀናት ልዩነት ውስጥ ለፍልስጤማውያን እና በኢራን ለሚደገፈው ሐማስ ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ ካደረገው ፈጣን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተለየ ነው።

በንጽጽር ሲታይ “አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ” ተብሎ በሚጠራው የኢራን እና አጋሮቿ ጥምረት ውስጥ ያሉት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና የኢራቅ ታጣቂ ቡድኖች የበለጠ ንቁ ወታደራዊ ተሳትፎ አላቸው።

ሁቲዎችን ወደኋላ የያዛቸው ምንድነው?

ሁቲዎች ለምን ከጦርነቱ መራቅን መረጡ? ወይስ ዘግይተው ይሳተፉ ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች የተንታኞች እና የመገናኝ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆነዋል። የቡድኑን ዓላማ እና ስትራቴጂያዊ ስሌትን በተመለከተ የተለያዩ ዓይነት ትንታኔዎች እየቀረቡ ነው።

‘ሳና ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ስተዲስ’ ላይ የታተመ አንድ ትንተና የታጣቂ ቡድኑን አቋም መርምሯል። ትንተናውን ያቀረቡት ማይሳ ሹጃ አል ዲን፤ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. የጋዛ ጦርነት እንደተነሳ ሁቲዎዎች በፍጥነት በመንቀሳቀስ እስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታውሳሉ።

በቀጣዩ ወር ደግሞ “ጋላክሲ ሊደር” የተባለውን መርከብ በመጥለፍ በቀይ ባሕር የሚተላለፉ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ።

ይህ ፈጣን እርምጃ በኢራን እና አጋሮቿ በሆኑ ቡድኖች መካከል የጋዛ ጦርነት አጭር እና ብዙ ወጪ የማያስወጣ ይሆናል የሚል እምነት እንደነበር የሚያመላክት መሆኑን ተንታኟ ያነሳሉ።

የሁቲ ታጣቂዎች መርከብ ሲያግቱ

በመላው የአረብ ዓለም ተቀባይነት ያለውን ይህንን ጉዳይ ደግፎ መቆም የሚያስገኘውን ፖለቲካዊ ትርፍ ስሌት ውስጥ አስገብተው እንደሚሆንም ይከራከራሉ። ተንታኟ አክለውም የጋዛ ጦርነት ሁቲዎች አገር ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት እንደጨመረ ያክላሉ።

ይሁን እንጂ ይህንን እንቅስቃሴያቸውን ተከትሎ አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የፈጸሙባቸው ሁቲዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ተንታኗ ይገልጻሉ። ይህ ጉዳት በአሁኑ ጦርነትም ይበልጥ ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም እንዲዙ አድርጓቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

አልዲን እንደሚገልጹት በየመኖች ዘንድ ኢራንን መደገፍ ከጋዛ ጎን ከመቆም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተቀባይነት የለውም።

‘ዘ ኒው አረብ’ የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንም በተመሳሳይ ሁቲዎች ቁጥብነት ያሳዩት በሁለት ዓመቱ የጋዛ ጦርነት በሰዎች እና በመሠረተ ልማቶቻቸው ላይ በደረሰባቸው “ከፍተኛ” ጉዳት ምክንያት እንደሆነ አስነብቧል።

በ’ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ’ የየመን ባለሙያ የሆኑት አህመድ ናጊ “ሁቲዎች በርካታ አመራሮችን አጥተው ሊሆን ይችላል። አሁን ራሳቸውን ለመጠበቅ እየሞከሩ ይመስለኛል” ሲሉ ለኒው አረብ ተናግረዋል።

ሁቲዎች ሌላ ስሌት ይኖራቸው ይሆን?

ሱሃኢብ አል ሚያሂ የተባሉ ፀሐፊ ‘አል ማስዳር ኦንላይ’ በተባለው ድረ ገጽ ላይ ባሳተሙት አስተያየት፤ የሁቲ እንቅስቃሴ “በጥንቁቅነት እና በጀብደኝነት” መካከል መወጠሩን ገልጸዋል። የአሁኑም ቁጥብነትን ከዚህ የተነሳ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሁቲዎች ራሳቸው መስቀለኛ መንገድ እንደሆኑ ፀሐፊው ይገልጻሉ። ከተራማጅነት አንጻር ሲታይ፤ በፍጥነት ወደ ቀጣናዊ ጦርነት መግባት ለቡድኑም ሌላ ጣጣ ይዞበት ሊመጣ እንደሚችል ያስረዳሉ።

ፀሐፊው እንደሚገልጹት ወታደራዊ ተሳትፎ ማድረግ ቀጣናዊው ግጭት ቡድኑ ወደያዛቸው አካባቢዎች እንዲዛመት ሊያደርግ ይችላል።

ሁቲዎች ይህንን ጊዜ ማለፍ የሚፈልጉ ከሆነ “ትዕይንቱን በሙቀት ሳይሆን በመረጋጋት ማጤን” ሊኖርባቸው እንደሚችል ጽፈዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሁቲዎች ፖለቲካዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ መልዕክት በኢራን ከሚመራው ጥምረት ጋር እጅጉን የተቆራኘ በመሆኑ፤ የማፈግፈግ እርምጃ መውሰድ የቅቡልነታቸው ምንጭ የሆነውን አካል እንደ መተው እንደሚቆጠር በማንሳት ተቃርኖውን አሳይተዋል።

የሁቲ ታጣቂ

አቋማቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ?

ሁቲዎች ጦርነቱን ሊቀላቀሉ ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ሁሉንም የሚያስማማ ምላሽ አልተገኘለትም።

አልዲን እንደሚያስረዱት ሁቲዎች ጣልቃ የመግባታቸው ጉዳይ ሚወሰነው በኢራን ስትራቲጂያዊ ስሌት ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት ቴህራን እገዛቸውን ላትፈልግ ትችላለች፤ ነገር ግን ቡድኑ እንዲሳተፍ ሊያደርጉት የሚችሉ ሁለት ሁኔታዎች አሉ።

አንደኛው ኢራን ጦርነቱን ወደ ቀይ ባሕር ወይም ባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥ ለማስፋፋት የምትወስን ከሆነ ነው።

ሌላኛው ደግሞ ጦርነቱ ሳዑዲ አረቢያን በሚያሳትፍ መልኩ ይበልጥ በቀጣናው የሚፋፋም ከሆነ ሁቲዎች ከሪያድ ጋር በተያያዘ ወሳኝ ወታደራዊ ሚና ይኖራቸዋል።

እንደ አልዲን ትንተና ከሆነ፤ ሁቲዎች ራሳቸውን ድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው እና ኢራን በቡድኑ ላይ ለረጅም ጊዜ ኢንቨስት ማድረጓ፤ ግጭቱ የሚስፋፋ ከሆነ ለተራዘመ ጊዜ ራሳቸውን አቅበው መቆየት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያደረገው ‘ሚድል ኢስት አይ’ ድረ ገጽ ያነጋገራቸው የየመንን ጉዳይ የሚከታተሉ የተወሰኑ ተንታኞች፤ ጦርነቱ እንዴት ይቀጥላል በሚለው ላይ በመመሥረት ቡድኑ መቀላቀሉ እንደማይቀር ገምተዋል።

የመን ውስጥ የሚታተም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ፋቴሂ ቢን ላዝሬቅ፤ ሁቲ አሁንም ድረስ ሁኔታውን እየገመገመ እንደሚገኝ እና “ኢራን ምን ዓይነት ተግዳሮት ይገጥማታል” የሚለው ላይ በመመሥረት እርምጃ እንደሚወስድ ለሚድል ኢስት አይ ተናግሯል።

የሁቲ ታጣቂዎች

ሁቲዎችን የሚቃወም ጋዜጣን የሚመራው ላዝሬቅ “የኢራን አገዛዝ ላይ የተደቀነው የኅልውና አደጋ እንደሆነ ከደመደሙ፤ ጦርነቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ ይወስናሉ” ሲል ትንተናው አስቀምጧል።

ሌሎች ተንታኞች ግን የሁቲ በዚህ ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ የኅልውና አደጋ ሊደቀንበት እንደሚችል ይናገራሉ። በ’ሰንዓ ሴንተር’ የየመን ተንታኝ የሆኑት ያዚድ አል ጄዳዊ፤ “ጣጣው ምን እንደሚሆን ያውቃሉ፤ [መዘዙ] ከፍተኛ ይሆናል፤ ገዳይ ይሆልባቸዋል” ሲሉ ለኒው አረብ ተናግረዋል።

ጃዳዊ እንደሚገልጹት ሁቲዎች ጦርነቱ ውስጥ መሳተፋችን በእስራኤል እና በአሜሪካ ከፍተኛ ዘመቻ እንዲከፈትብን ሊያደርግ ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው።

ይህንን ዓይነቱን ዘመቻ ደግሞ ሁቲዎችም ሆነ በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ ሊቋቋመው እንደማይችል ያስረዳሉ።

ዘመቻ የሚከፈት ከሆነ በሁቲ ስር ባሉ አካባቢዎች ውስጣዊ አለመረጋጋት ሊያስከትል እንደሚችልም ይጠቁማሉ።

በዚህ ዓይነቱ ዘመቻ ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ የሚዳከም ከሆነ ተቀናቃኙ የየመን መንግሥት እና አጋር ኃይሎች ሁቲዎችን ከሚቆጣጠሯቸው ከግዛቶቹ ለማስወጣት ዕድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም አክለዋል።