
ከ 3 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የነበረችውን ሴኔጋልን በመንጠቅ ለሞሮኮ መስጠቱን የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
በአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታው ወቅት የሴኔጋል ተጫዋቾች ጨዋታውን አቋርጠው መውጣታቸውን ተከትሎ በተነሳው ውዝግብ ምክንያት ውጤቱን በመቀልበስ ሞሮኮ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ መሆኗን የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ካፍ አውጇል።
ባለፈው ጥር በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል ሞሮኮን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፋ ነበር። የሴኔጋል ተጫዋቾች በመደበኛው 90 ደቂቃ መጠናቀቂያ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥባቸው ጨዋታ አቋርጠው ከሜዳ ሲወጡ ጨዋታው በእጁጉ ተስተጓጉሎ ነበር። የሴኔጋል ተጫዋቾች በቡድን አጋሮቻቸው ማግባባት ወደ ሜዳ ተመልሰው ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ የሪያል ማድሪዱ ብራሂም ዲያዝ ፍጹም ቅጣት ምቱን ስቶ ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቆ ወደ ጭማሪ ደቂቃ አመራ።
በጭማሪ ሰዓት የሴኔጋሉ ፓፔ ጉዬ ባስቆጠራት ግብ ሴኔጋል በወቅቱ አሸናፊ ሆና ነበር። ነገር ግን ለአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ቦርድ በቀረበው ቅሬታ መሠረት የሴኔጋል ድል ተቀልብሶ ለሞሮኮ ተሰጥቷል።
ካፍ በመግለጫው “በጨዋታው ሴኔጋል ተሸንፋለች” በዚህም ለሞሮኮ “የ3 ለ0 ውጤት ተሰጥቷል” ብሏል።
ውሳኔውን የሴኔጋል እግር ኳስ ፌደሬሽን “ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ያልተጠበቀ እና ተቀባይነት የሌለው” ብሎታል።
ጉዳዩንም ወደ እግር ኳስ አሸማጋይ አካል እንደሚወስደው ገልጿል።
ካፋ ውሳኔውን ያስተላለፈው ሞሮኮ ይግባኝ ማለቷን ተከትሎ ነው። ካፍ በመግለጫው የሴኔጋል ቡድን ባሳየው ያልተገባ ባሕርይ የካፍን አንቀጽ 82 መመሪያ በመጣሱ ምክንያት አንቀጽ 84 ተግባራዊ መደረጉን ገልጿል።
አንቀጽ 82 እንደሚያትተው አንድ ቡድን በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ ከዳኛው ፈቃድ ውጭ ጨዋታ አቋርጦ ከወጣ ወይም ለመጫዋት ፈቃደኛ ካልሆነ እንደተሸነፈ ይወሰዳል ይላል።
አንቀጽ 84 ደግሞ ይህንን ድንጋጌ ይደግፋል። አንቀጹ “ማንኛውም ቡድን አንቀጽ 82ን ከጣሰ ለተቃራኒው ቡድን የ3 ለ0 ውጤት ይሰጣል ይላል።
ፈደሬሽኑ መመሪያዎችን ለማስከበር፣ በውድድሩ ማዕቀፍ ግልጽነትን ለማስፈን እና የተረጋጋ የውድድር ሂደትን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጫው አክሏል።
የሰሜን አፍሪካው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ማሄር መዛሂ ውሳኔው በወቅቱ የነበረውን ስሜት አይቀይረውም በማለት ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።
“በመጨረሻዎቹ 16 ደቂቃዎች የተመለከትነውን ትዕይንት ከአዕምሯችን ማጥፋት አንችልም” ብሏል ማሄር።
“የሴኔጋል ተጫዋቾች አሸንፈው ሜዳሊያ ማጥለቃቸውን እና በአገራቸው የጎዳና ላይ የደስታ መግለጫ ማድረጋቸውን መርሳት አንችልም”
በአፍኮን ፍጻሜ የሆነው ምንድን ነው?
መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በ8ኛው የባከነ ደቂቃ ላይ የወቅቱ የመሃል ዳኛ ጂን ጃኩይስ ንዳላ ለሞሮኮ ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ።
ዳኛው የተሰራውን ጥፋት ድጋሚ እንዲመለከቱ በቫር ዳኞች ምክረ ሃሳብ ቀርቦላቸው ነበር። ይህ ከስተት ከመፈጠሩ ከጥቂት ሴኮንዶች በፊት ሴኔጋሎች ግብ አስቆጥረው በመሻሩ ዋና አሰልጣኙ ፓፔ ቲያው በዳኛው ውሳኔ ቅሬታቸውን እየገለጹ የነበረበት ወቅት ነው። በሴኮንዶች ልዩነት በቡድናቸው ላይ የፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥ አሰልጣኙ የቡድን አባላቱ ሜዳውን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ።
የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ግን ሜዳ ውስጥ በመቆየት የቡድን አጋሮቹ እንዲመለሱ ሲያግባባ ቆዬ።
ከ17 ደቂቃ መዘግየት በኋላ የሴኔጋል ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ተመለሱ።
ወዲያውኑ የፍጹም ቅጣት ምቱን የሪያል ማድሪዱ ብራሂም ዲያዝ ሲመታ በሴኔጋሉ በረኛ ኤዱዋርዶ ሜንዲ በቀላሉ ተያዘበት። በዚያው ቅጽበት የመሃል ዳኛው የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚገልጽ ፊሽካ አሰሙ።
30 ደቂቃ ተጨምሮ ጨዋታው ሲቀጥል በአራተኛው ደቂቃ የቪያሪያሉ አማካይ ጉዬ ለሴኔጋል የማሸነፊያ ግብ አስቆጠረ።
ከጨዋታው በኋላ የወቅቱ የሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉይ የሴኔጋል ተጫዋቾች ድርጊት “አሳፋሪ” እና “አፍሪካን ያላካበረ” ብለው ነበር።
በወቅቱ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ድርጊቱን በጥብቅ ማውገዛቸውን በኢንስታግራም ገልጸው ነበር።
የሴኔጋሉ አሰልጣኝ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ እያለ ግርግር በመነሳቱ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን አቋርጠው ወጥተዋል። ነገር ግን በኋላ ላይ በሰጡት መግለጫ ድርጊቱ ትክክል እንዳልነበር እና በወቅቱ ስሜታዊ ሆነው እንደነበር ተናግረዋል።
በወቅቱ የሞሮኮን ብሔራዊ ቡድን ለፍጻሜ ያበቁት ዋና አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉይ ከየከቲት መጨረሻ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ለቀዋል።
