ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

መሬት ላይ ተንበርክካ ዘለግ ባለ ክብ እንጨት እንሰት ትፈቀፍቃለች።
የምስሉ መግለጫ,መሬት ላይ ተንበርክካ ዘለግ ባለ ክብ እንጨት እንሰት ትፈቀፍቃለች።

ከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሰለፈች አብቴ መሬት ላይ ተንበርክካ ዘለግ ባለ ክብ እንጨት እንሰት ትፈቀፍቃለች።

“እንሰት መፋቅ እጅ እና ደረት ያደክማል። አራት ቀን የሚወስድ ሒደት ነው። እሱንም ማጠናቀቅ ከቻልን ነው” ትላለች።

በዶርዜ መንደር ተወልዳ ያደገችው አሰለፈች ከልጅነቷ ጀምሮ እንሰት ስታዘጋጅ ነው የኖረቸው።

በደቡብ ክልል ሴቶች እንሰት ለማዘጋጀት ሰዓታት ይወስድባቸዋል። ከወገባቸው አጎንብሰው ለሰዓታት በእጃቸው አድካሚውን ሥራ ያከናውናሉ።

እንሰት በኢትዮጵያ ለ20 ሚሊዮን ሰዎች በምግብነት ያገለግላል። ይህም ከአጠቃላዩ ሕዝብ 15 በመቶው ነው።

እንሰት ድርቅን ለመቋቋም ካለው ተፈጥሯዊ አቅ ምአንጻር ‘ረሃብ የሚዋጋው ዛፍ’ (the tree against hunger) እንዲሁም ሙዝን ስለሚመስል ‘የውሸት ሙዝ’ (the false banana) የሚሉ ስያሜዎችን አግኝቷል።

እንሰት በኢትዮጵያ ለ20 ሚሊዮን ሰዎች በምግብነት ያገለግላል።
የምስሉ መግለጫ,እንሰት በኢትዮጵያ ለ20 ሚሊዮን ሰዎች በምግብነት ያገለግላል።

የእንሰት ተክል ድርቅ እንዲሁም በሽታ መቋቋም ይችላል። ቆጮን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦች ለማዘጋጀትም ይውላል።

እንሰት ማዘጋጀት የሴቶችን ጤና የሚፈታተን እንዲሁም ጊዜ የሚፈጅም ነው።

በዶርዜ መንደር ያደረገችው ገበያነሽ አልታ “ሁለት ሴቶች ለአራት ቀናት ያህል ይፍቃሉ” ትላለች።

አሁን ግን አዲስ ቴክኖሎጂ ባህላዊውን አሠራር ለውጦታል።

ከአምስት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የተሠራ አዲስ ማሽን እንሰትን ለመፋቅ ይውላል።

ማሽኑ በኤሌክትሪክ ወይም በነዳጅ ይሠራል። እንሰት ለማዘጋጀት የሚወስደውን ረዥም ጊዜ በእጅጉ ያሳጥራል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ እና የማሽኑ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ “ከዚህ ቀደም እናቶች ከስምንት እስከ 10 ሰዓት እና እስከ ሁለት ሙሉ ቀን ድረስ እንሰት ይፍቁ ነበር” ይላሉ።

ወገባቸውን አዘቅዝቀው ለሰዓታት በእጃቸው አድካሚውን ሥራ ያከናውናሉ።
የምስሉ መግለጫ,ወገባቸውን አዘቅዝቀው ለሰዓታት በእጃቸው አድካሚውን ሥራ ያከናውናሉ።

ዶ/ር አዲሱ “አሁን ግን ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመላው ቤተሰባቸው የሚበቃ ምግብ ከእንሰት ያዘጋጃሉ” ሲሉ ያክላሉ።

ዩኒቨርስቲው ማሽኑን ካጠናቀቀ በኋላ በመላው አገሪቱ ማሽኑን የሚያዳርሱ 40 ማኅበሮች ተቋቁመዋል። እያንዳንዱ ማኅበር ከ12 እስከ 20 አባላት አሉት።

“ሴቶች እና ወጣቶችን እያደራጀን ማሽኑን እንሰጣቸዋለን። እነሱም አገልግሎቱን ከ1000 እስከ 2000 ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ያዳርሳሉ” ይላሉ ዶ/ር አዲሱ።

ልክ እንደ ወፍጮ ቤት ድርጅቶቹ እንሰት የመፋቅ አገልግሎት እንደሚሰጡም ያስረዳሉ።

ማሽኑ ወደ 150 ሺህ ብር ገደማ ያወጣል። የተለያዩ ተቋማትም ድጋፍ ሰጥተዋል።

እነ ገበያነሽ መንደር ያለውን ማሽን ወጪ የሸፈነው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2025 የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ኤጀንሲ እንዳለው በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች “ወደለየለት ቀውስ ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሰዋል።”

የእንሰት ማሽኑ የተዘጋጀውም ይህ ቀውስ አሳሳቢ በሆነበት ወቅት ነው።

ከአምስት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የተሠራ አዲስ ማሽን እንሰት ለመፈቅፈቅ ይውላል።
የምስሉ መግለጫ,ከአምስት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የተሠራ አዲስ ማሽን እንሰት ለመፈቅፈቅ ይውላል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባወጣው መረጃ መሠረት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ ደኅንነት ቀውስ ተጋርጦባቸዋል። በቅርብ ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶች፣ ድርቅ፣ በሽታ እና የዋጋ ንረት ችግሩን አባብሰዋል።

የእንሰት ምርት የአገሪቱን የምግብ ዋስትና በማስጠበቅ ሚና አለው።

በአውሮፓውያኑ 2024 ብሔራዊ የእንሰት ዕድገት መርሃ ግብር ተዘርግቷል። አገር በቀል ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግ፣ የእንሰት ምርትን ለማዘመን እና የሴቶችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ያለመ ነው።

የቀድሞው የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ “መርሃ ግብሩ በዘመናዊ ግብርና እና ደረጃውን በጠበቀ ግብዓት አማካኝነት ምርታማነትን ይጨምራል፤ የገበያ ትስስርንም ያሳድጋል። በጥናት እና በፈጠራ ኢንቨስት ለማድረግ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ለማጎልበትም ያግዛል” ብለዋል።

የተዘረጋው መርሃ ግብር በስድስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር ሲሆን፣ የግብርና ሚኒስቴር እንደሚለው 13 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት ነው።

ቢቢሲ ስለ ብሔራዊ የእንሰት መርሃ ግብር ከግብርና ሚኒስቴር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

እንሰት እየከተፈች የምታዘጋጅ ሴት

እንደ ገበያነሽ ያሉ ሴቶች አዲሱ ማሽን ድካማቸውን ቀንሶላቸዋል።

“ማሽኑ እንደመጣ ሁሉም ሰው እንሰቱ እንዲፋቅለት ወስዷል። ሁለት የእንሰት ዛፍ ተፍቆ ከተዘጋጀ ከሦስት እስከ አራት ወር እንጠቀምበታለን” ትላለች።

ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት፤ እንሰት በአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ቀውሶችን እያስተናገደች ላለችው ዓለም ልዕለ ምግብ እንዲሁም ነፍስ አድን ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

እንሰት ረሃብን ለመቋቋም ካለው ጠቀሜታ አንጻር 'the tree against hunger' ይባላል።
የምስሉ መግለጫ,እንሰት ረሃብን ለመቋቋም ካለው ጠቀሜታ አንጻር ‘the tree against hunger’ ይባላል።

“ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ፣ ኪው” የተባለው ተቋም የጥናት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጄምስ ቦረል፤ እንሰት በአስቸጋሪ ወቅት የምግብ ዋስትናን ለማሳደግ እንደ መከታ የሚጠቅም ሰብል እንደሆነ ያስረዳሉ።

ሙዝ መሳዩ ተክል እንዴት እየሞቀች ባለችው ዓለም ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የመመገብ አቅም እንዳለው ጥናቱ አመልክቷል።

እንሰት ከኢትዮጵያ ውጪ ባይታወቅም በገንፎ እና ቆጮ መልኩ ተሠርቶ ለምግብነት ይውላል። ጥናቱ እንደሚያመለክተው ተክሉ በአፍሪካ ሰፋ ባለ መጠን ሊበቅል ይችላል።

የእንሰት ሙዝ የመሰለ ፍሬው ባይበላም በካርቦሃይድሬት የበለጸገው የተክሉ ዘለላዎች እንዲሁም ሥሩ እርሾ በሚኖረው መልኩ ገንፎ እና ቆጮ ለመሥራት አገልግሎት ላይ ይውላል።

ከእንሰት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ እና እንደ ምግብነት የማይቆጠሩ ተክሎች እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ መብቀላቸው ታይቷል።

ይህም ተክሉ ሰፊ ክልልን በመሸፈን የተለያየ የአየር ሁኔታን መቋቋም እንደሚችል የጠቆመ ነው።

ሳይንቲስቶች የግብርና ዳሰሳዎች እንዲሁም የተከላ ሥራ በመሥራት እንሰት በሚቀጥሉት አራት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን አቅም ተንብየዋል።

ተክሉ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መመገብ የሚችል ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እንዲሁም እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ባሉ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናን እንደሚያሳድግ ጥናቶች ያሳያሉ።