March 18, 2026

አግባብነት ባለው አካል “ተገምግሞ ፈቃድ ያልተሰጠው” መጽሐፍ “ለተማሪዎች ሲሸጡ” ወይም “ሲጠቀሙ” የተገኙ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የትምህርት ተቋማት፤ ከአጠቃላይ ወርሃዊ ገቢያቸው 35 በመቶ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ደንብ ተዘጋጀ። ተቋማቱ የከተማይቱ የትምህርት ቢሮ ካስቀመጠው አሰራር ውጪ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡ ከተገኙም፤ ከወርሃዊ ገቢያቸው ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ለመንግስት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል። 

“ለአንድ ጊዜ ብቻ” ተግባራዊ የሚደረገው ይህ የቅጣት ገንዘብ የተደነገገው፤ “የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር አሰራርና ተጠያቂነት ለማስፈን” በተዘጋጀ ደንብ ላይ ነው። ባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 9፤ 2018 ይፋ የተደረገው ይህ ደንብ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተዘጋጀ ነው። 

ደንቡ የተዘጋጀው በትምህርት እና ስልጠና እንዲሁም በሙያ ብቃት ዘርፍ “ይስተዋላሉ” የተባሉ የአሰራር ስርዓት “ክፍተቶችን” “በህግ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” እንደሆነ ተገልጿል። በ2015 ዓ.ም ከጸደቀው ሀገር አቀፍ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንዲሁም ባለፈው አመት ጸድቆ ስራ ላይ ከዋለው ከአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ቁጥር ጋር “የተጣጣመ አሰራርና እና የተጠያቂነት ስርዓት መፍጠር”፤ ሌላው ለደንቡ መዘጋጀት በምክንያትነት የተጠቀሰ ጉዳይ ነው።

በአምስት ክፍሎች እና በ20 አንቀጾች የተከፋፈለው ደንብ በውስጡ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል፤ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትና የሙያ ብቃት ምዘና ላይ የሚሳተፉ አካላት መብት እና ግዴታን የሚመለከተው ይገኝበታል። አዲሱ ደንብ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተጠያቂነት ዝርዝር ድንጋጌዎችንም አካትቷል።

ከድንጋጌዎቹ ውስጥ አራቱ፤ ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ከተማሪዎች ከሚሰበስቡት ወርሃዊ ገቢ 35 በመቶ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድዱ ናቸው። የትምህርት ተቋማቱ ይህ ግዴታ የሚጣልባቸው፤ በአዲሱ ደንብ ላይ የተቀመጡ እንደ መጽሐፍ አጠቃቀም፣ የማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጥ፣ የተማሪ ብዛትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ተላልፈው ሲገኙ ነው።

ከድንጋጌዎቹ አንዱ “በመንግስት ከተዘጋጀ የማስተማሪያ መጽሐፍ ውጪ” “አግባብነት ባለው አካል ተገምግሞ ፈቃድ ያልተሰጠውን መጽሐፍ ለተማሪዎች መሸጥ ወይም መጠቀምን” ይከለክላል። ይህንን ተላልፎ የተገኘ የትምህርት ተቋም “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ተሰጥቶት፤ “ለአንድ ጊዜ ብቻ” ከአጠቃላይ ተማሪዎች ከሚሰበስበው ወርሃዊ ገቢው 35 በመቶ የሚሆነውን “ለመንግስት ገቢ እንደሚያደርግ” በአዲሱ ደንብ ተደንግጓል።

የትምህርት ተቋማቱ የሚሰጡት “የማጠናከሪያ ትምህርት” የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ካስቀመጠው አሰራር “ውጪ ከሆነ” አሊያም በተማሪዎች እና በወላጆች “ፈቃደኝነት ላይ ያልተመሰረተ” ከሆነ ተመሳሳይ ቅጣት እንደሚያስከትል በደንቡ ላይ ሰፍሯል። ደንቡ “የማጠናከሪያ ትምህርት” የሚለው “በክረምት” ወይም “ከትምህርት ሰዓት ውጪ” በትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን ነው።

ሰላሳ አምስት በመቶ ወርሃዊ ገቢ ለመንግስት ገቢ የሚያስደርገው ሌላው ጥፋት “በእውቅና እና እድሳት ፍቃድ” ወቅት ከተሰጠ “የተማሪ ቁጥር በላይ ይዞ” መገኘት ነው። በዚሁ ጊዜ አግባብ ካለው አካል ከሚሰጥ “እርከን” እና “ደረጃ” ውጭ ተማሪ ይዞ የሚገኝ የትምህርት እና ስልጠና ተቋም፤ “ለአንድ ጊዜ ብቻ” ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ማድረግ እንዳለበት በአዲሱ ደንብ ላይ ተቀምጧል።

አዲሱ ደንብ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማትን ብቻ የሚመለከት የቅጣት ክፍያም በውስጡ ይዟል። የሰልጣኞች የትምህርት ማስረጃ “በተቀመጠለት ጊዜ እና ጥራት መሰረት” ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን “ያላስገባ” የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋም ከወርሃዊ ገቢው “ሃያ በመቶውን” ለመንግስት ገቢ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አዲሱ ደንብ ያዝዛል።

አንድ የትምህርት ተቋም እነዚህን ጥፋቶች “በተሰጠው ጊዜ ካላስተካከለ”፤ “በተደጋጋሚ ከፈጸመ” እና “በሚሰጠው የማስተካከያ ግብረ-መልስ እና ማስጠንቀቂያ መሰረት ማሻሻያ ካላደረገ”፤ ደንቡን ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድበትም ተገልጿል። ከአዲሱ ደንብ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ለውይይት የቀረበ መመሪያ፤ አንድ ትምህርት ተቋም የተገኘበትን ጥፋት እንዲያስተካክል እስከ ሁለት ሳምንት የሚቆይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጠው ይደነግጋል።

በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ማስተካከያ ያላደረጉ የትምህርት ተቋማት “እስከ ዕውቅና ፈቃድ መሰረዝ” የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በመመሪያው ላይ ተመልክቷል። እርምጃውን የመውሰድ ስልጣን በአዲሱ ደንብ እና መመሪያ የተሰጠው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)