March 19, 2026

ለንግድ ስራዎች እና ለቱሪዝም ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዜጎቻቸው 15 ሺህ ዶላር ዋስትና እንዲያስዙ ከሚገደዱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተካተተች። ዋስትና የማስያዝ አሰራሩ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በ11 ሀገራት ዜጎች ላይ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። 

የአሜሪካ መንግስት “ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በህገ ወጥ መንገድ በሀገሩ የሚቆዩ ሰዎችን ለመከላከል” በሚል ምክንያት ዋስትና የማስያዝ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ ነው። ይህ አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ከተደረገባቸው 38 ሀገራት መካከል ሃያ ሶስቱ አፍሪካውያን ናቸው።

ከእነዚህ ሀገራት መካከል የኢትዮጵያ ጎረቤት ጅቡቲ፣ የምስራቅ አፍሪካዎቹ ኡጋንዳ እና ታንዛንያ ይገኙበታል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 9፤ 2018 ይፋ ያደረገው የሀገራት ዝርዝር፤ ዋስትና የማስያዙ አሰራር ተግባራዊ የሚደረግባቸው የአፍሪካ ሀገራትን ቁጥር 29 አድርሶታል።

በዛሬው ዝርዝር ከተካተቱ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ዜጎቿ ለንግድ እና ለቱሪስት ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት 2.3 ሚሊዮን ብር ገደማ ዋስትና እንዲያስዙ ይገደዳሉ። 15 ሺህ ዶላር አስይዘው “ቢ 1” እና “ቢ 2” በመባል የሚጠሩትን የአሜሪካ ቪዛዎች ያገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ጉዟቸውን አጠናቀቅው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ያስያዙት ገንዘብ “ተመላሽ እንደሚደረግላቸው” የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።  

ቪዛ አግኝተው ነገር ግን ወደ አሜሪካ ጉዟቸውን ሳያደርጉ የሚቀሩ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ያስያዙት ገንዘብ እንደሚመለስላቸው መስሪያ ቤቱ ገልጿል። ዋስትና በማስያዝ አሰራር ቪዛ ከተሰጣቸው አንድ ሺህ የሚጠጉ የውጭ ዜጎች መካከል 97 በመቶ ያህሉ በተሰጣቸው ጊዜ አሜሪካንን ለቅቀው “ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን” መስሪያ ቤቱ በዛሬው መግለጫው በስኬትነት ጠቅሷል።      

እንደ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሆነ፤ “በህገ ወጥ መንገድ” በሀገሪቱ የሚገኙ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ማስወጣት በአማካይ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ (18 ሺህ ዶላር) ይፈጃል። አሜሪካ ዋስትና የማስያዝ አሰራርን ተግባራዊ ማድረጓ ሀገሪቱ ለዚሁ ጉዳይ በዓመት ታወጣው የነበረውን 800 ሚሊዮን ዶላር መቆጠብ ያስችላታል ተብሏል። 

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ሚኒስትር  ክሪስቲ ኖም በተለምዶ “ዲቪ” በመባል

በሚታወቀውን የፍልሰተኞች “የዳይቨርሲቲ ቪዛ” ፕሮግራም ላይ እገዳ ጣሉ። ዝርዝሩን ለማንበብ

https://ethiopiainsider.com/2025/16834/

#US #Ethiopia #DiversityVisa #DV

· 2,813Views

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እንደ ዋስትና ማስያዝ ያሉ “ወደ አሜሪካ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት ያስችላሉ” ያላቸውን ተከታታይ እርምጃዎች ባለፉት ወራት ሲወስድ ቆይቷል። የአሜሪካ መንግስት ካለፈው ጥር አጋማሽ ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው አሰራር፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ75 ሀገራት የፍልሰት ቪዛ (immigrant visa) መስጠት ማቆሙ ለዚህ ተጠቃሽ ነው። 

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ባለፈው ታህሳስ ወር ባሳለፈው ውሳኔ፤ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በዲቪ ሎተሪ ለሌሎች ሀገራት ቪዛ የሚሰጥበትን አሰራር ማቆሙም አይዘነጋም። ይኸው መስሪያ ቤት፤ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሀገራቸው በነበረ ግጭት ምክንያት ወደ አሜሪካ የገቡ እና የተሰጣቸው ከለላ ያበቃ ዜጎች ከየካቲት ወር ጀምሮ በግዳጅ ወደ ሀገራቸው እንደሚመልስ ያስታወቀውም በዚሁ በታህሳስ ወር ውስጥ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)