ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጸጉሯን ዊግ የምትቀጠል ሴት
የምስሉ መግለጫ,ጥቁሮች በብዛት የሚጠቀሟቸው የተለያዩ ዓይነት የፀጉር ማስረዘሚያ ዊጎች ወይንም ሂውማን ሄሮች ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች ተገኝቶባቸዋል

ከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በመላው ዓለም ሚሊዮኖች የሚጠቀሙበት ፀጉር ላይ የሚቀጠለው ዊግ እና ሂውማን ሄር ከጡት ካንሰር፣ ከሆርሞን መዛባት እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳት የሚያደርሱ ኬሚካሎችን መያዛቸውን ጥናቶች አሳዩ።

በዓይነቱ ለየት ያለ እና በስፋት የተደረገ ጥናት ነው በተባለው በዚህ ምርምር ሳይንቲስቶች ዊጎቹ ላይ 50 ጎጂ ኬሚካሎችን አግኝተውባቸዋል።

እነዚህ ኬሚካሎች ፀጉር ላይ የሚቀጠሉ፣ የሚጠለቁ እንዲሁም የሚሰፉ ዊጎች እና ሂውማን ሄር ላይ በሙሉ መገኘታቸውን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።

የምርምር ውጤቱ በአሜሪካን ኬሚካል ሶሳይቲ ጆርናል ላይ የታተመ ሲሆን፣ በዚህ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሚንቀሳቀስበት ኢንዱስትሪ ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት አና ለተጠቃሚዎች የተሻለ ግልጽነት እንዲኖር ጥሪ አቅርቧል።

ጥናቱን ያካሄዱት ዶ/ር ኢሊሺያ ፍራንክሊን “ከአንዳንድ አደገኛ ኬሚካሎች የፀዱ ምርቶችን ለመፍጠር እና ለማምረት ምንም ዓይነት መስፈርት የሌላቸውን ኩባንያዎች እንዳሉ እንተማመናለን” ብለዋል።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ዊጎች ሌሎች የሚጠለቁ ፀጉሮች ለረጅም ጊዜ ስለሚደረጉ እና ከቆዳ ጋር በቅርበት ስለሚገናኙ የተለየ አደጋን ያስከትላሉ። ይህ ሥር የሰደደ ተጋላጭነት የረጅም ጊዜ የጤና አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል።

“የፀጉር ማስራዘሚያዎች (ዊጎች) ለቆዳ በጣም በቅርበት ይደረጋሉ” የሚሉት ፍራንክሊን ከዚህም በተጨማሪ “በአንድ ሰው ጭንቅላት እና አንገት ጋር ለብዙ ሳምንታት ወይም ለወራት የሚቆይ ንክኪ ይኖራቸዋል” በማለት ያለውን አደጋ ለማሳየት ያብራራሉ።

አደገኛ ኬሚካሎች

አንድ ላይ ታስረው ለሽያጭ የቀረቡ ዊጎች
የምስሉ መግለጫ,ተመራማሪዎች “ናቹራል” ወይም “ቨርጅን” የሚል ማሻሻጫ የተለጠፈባቸው ዊጎች አስተማማኝ ናቸው ማለት አይደለም ብለዋል

ዓለም አቀፉ የዊግ ገበያ በአውሮፓውያኑ 2028 ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅስ ተገምቷል።

ብዙ ሴቶች ለመዋቢያ ወይም ለፋሽን በሚል ፀጉር ላይ የሚቀጥሏቸውን ዊጎች እና የሚያጠልቋቸው ፀጉሮችን የሚመርጡ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት ግን ጥቁሮች መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል።

ሰው ሠራሽ ፀጉር እስከ 20 ዶላር ብቻ ሊያወጣ ይችላል። ከፍተኛ ጥራት ያለው የሰው ፀጉር (ሂውማን ሄር) ደግሞ በሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ሊያወጣ ይችላል።

ሳይንቲስቶች ፍተሻ ባካሄዱባቸው 43 ናሙናዎች ውስጥ 170 ኬሚካሎችን አግኝተዋል።

ተመራማሪዎቹ አንድ ነጠላ ንጥረ ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ የተለያዩ ኬሚካሎችን ለመለየት የሚያስችል ዘዴን መጠቀማቸው ተገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ 48ቱ በተባበሩት መንግሥታት እና በአውሮፓ የኬሚካል ተቋማት “አደገኛ” በሚል ዝርዝር ውስጥ የገቡ ናቸው።

ፍራንክሊን “የእሳት ተቀጣጣይነትን ለመቀነስ ከሚረዱ እስከ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች፣ ሆርሞንን ከሚያዛቡት እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳት እንደሚያደርሱ እስከታወቁት የፕላስቲክን ዕድሜ ለማራዘም ጥቅም ላይ አስከሚውሉ (phthalates) ድረስ ተገኝተዋል” ብለዋል።

በ36 የዊግ ናሙናዎች፤ ሰው ሠራሽም ሆነ ሂውማን ሄር ውስጥ ከጡት ካንሰር ጋር የተያያዙ አስራ ሰባት ኬሚካሎች ተገኝተዋል።

ከናሙናዎቹ ውስጥ ወደ 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ እሳትን የሚቋቋሙ ፕላስቲኮችን ለመሥራት የሚያገለግሉ አደገኛ የኦርጋኖቲን ውህዶችን (organotin compounds) ይዘዋል።

ሳይንቲስቶች በተለምዶ በሸማቾች ምርቶች ውስጥ የማይገኙ ኦርጋኖቲን የተባሉ አደገኛ ውህዶችን በማግኘታቸው ተገርመዋል።

እነዚህ ኬሚካሎች ከቆዳ መቆጣት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፣ የሆርሞን መዛባትን እንደሚያስከትሉ ይታወቃል። ይህም ማለት በሰውነት ውስጥ ያሉ ብዙ ሂደቶችን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችን ያውካሉ፤ ይህም ከወሊድ እና ከእድገት ጋር የተያያዙ ሆርሞኖችን ያካትታል።

በናሙናዎቹ ውስጥ በብዛት ከተገኙት ኬሚካሎች መካከል ስስ ጣውላ እና ሌሎች የእንጨት ማጣበቂያዎችን ለመሥራት የሚያገለግል ፌኖል (phenol) እና ፕላስቲኮችን የበለጠ ተጣጣፊ ለማድረግ የሚያገለግለው እና ሌሎችም ጉዳትን የሚያስከትሉ ኬሚካሎች ተገኝተውባቸዋል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት እነዚህ ኬሚካሎች የጡት ካንሰር አምጪ በመሆን የሚታወቁ ሲሆን፣ በጊዜ ብዛት የጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ከፍ ያደርጋሉ።

‘ሂውማን ሄር’ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው?

ጸጉሯን የምትላጭ ሕንዳዊት ሴት
የምስሉ መግለጫ,ሕንዳዊቷ ሴት ለሃይማኖታዊ ተግባር ጸጉሯን ትላጫለች። ‘ቴምፕል ሄር” የተባለው ቤተ መቅደስ ከእምነቱ ተከታዮች የሰበሰበውን ጸጉር በጨረታ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ‘ሂውመን ሄር’ ለሚሸጡ ያስረክባል

ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች በአብዛኛው ትኩረት ያደረጉት በሰው ሠራሽ ፀጉር ላይ ሲሆን፣ አደገኛ ብረቶች መያዛቸውን ደርሰውበታል።

ነገር ግን ይህ ጥናት 11 የቨርጂን፣ ሮው እና ከሰው እና ከሰው ሠራሽ ነገሮች ጋር የተደባለቁ ናሙናዎችንም ፈትሿል።

ቨርጂን እና ሮው (Virgin and raw) ፀጉሮች ከኬሚካል ነጻ የሆኑ በሚል በጣም በውድ ዋጋ ይሸጣሉ። ሮው የሚባሉት ፀጉሮች በፋብሪካ ውስጥ ያላለፉ እና በቀጥታ ከለጋሽ ላይ የተቆረጡ ወይም የተላጩ ናቸው።

ፍተሻ የተደረገባቸው ቨርጂን ወይንም ሮው ተብለው ለገበያ የቀረቡ ሂውማን ሄሮች ከአንዳንድ ሰው ሠራሽ ፀጉሮች የበለጠ አደገኛ ኬሚካሎችን ይዘው ተገኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ የሆርሞን ለውጦችን ወይንም መዛባቶቸን ያስከትላሉ።

የጡት ካንሰር መንስኤዎችን የሚያጠኑት የዩኤስ ሳይለንት ስፕሪንግ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ፍራንክሊን “አንድ ምርት ሂውማን ሄር ተብሎ ወይም ከአንድ ግለሰብ የተገኘ ‘የተፈጥሮ’ መባሉ ብቻ ከሰው ሠራሽ ፀጉር የበለጠ ደኅንነቱ የተጠበቀ አያደርገውም” ይላሉ።

“በሰው ሠራሽ ናሙና ውስጥ አደገኛ ተብሎ የተፈረጀ አንድ ኬሚካል ስናገኝ በሂውማን ሄር ውስጥ ግን አደገኛ የተባሉት ኬሚካሎች ብዛት ከአምስት እስከ ሰባት ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት እነዚህ ኬሚካሎች በፋብሪካ ውስጥ የፀጉሩን ይዘት ለማሳመር፣ ቆይታውን ወይም ነዶውን ለማሻሻል በሚል በሚደረግ የምርት ሂደት ወቅት ሊገቡ ይችላሉ።

ጥናቱ የአደገኛ ኬሚካሎችን መጠን ባይገመግምም፣ እንደ ሆርሞን መዛባት ያሉ አንዳንድ ኬሚካሎች በዝቅተኛ መጠን እንኳን ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ፍራንክሊን ተናግረዋል።

ተመራማሪዎቹን ስጋት ካጫሩባቸው ጉዳዮች አንዱ አምራቾች በሚያቀርቧቸው ዊግ ወይንም ሂውማን ሄሮች ውስጥ መኖር ስላለባቸው ኬሚካሎች ግልጽ የሆነ የደኅንነት ገደብ አለመኖሩ ነው።

ፍራንክሊን “ለመዋቢያነት በምንጠቀምባቸው ምርቶች ውስጥ አደገኛ ኬሚካሎች ሊኖሩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም። በየቀኑ ልናስወግዳቸው ለማንችላቸው ኬሚካሎች ተጋልጠናል” ይላሉ።

ሥዕላዊ መግለጫ

ብዙ ዊጎች በፈላ ውሃ ውስጥ እንዲሞቁ ወይም እንዲነከሩ ይደረጋሉ፤ ይህም መርዛማ ጭስ እንዲያወጡ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ኬሚካሎች ወደ ሰውነት ውስጥ በመተንፈሻ አካል በኩል ሊገቡ ይችላሉ።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በቆዳ ንክኪ ወደ ሰውነት ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ ተጠቃሚን ብቻ ሳይሆን አገልግሎቶች የሚሰጡ የፀጉር ባለሙያዎችንም ይጎዳል።

አንዳንድ ሰዎች ከሚጠቀሙት ዊግ የተነሳ ማሳከክና መቅላት፣ የራስ ቆዳ፣ አንገትና ፊት ላይ ሽፍታና እብጠት እንዲሁም አልፎ አልፎ የመተንፈሻ አካላት ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

ዊግን ወይንም ‘ሂውመን ሄር’ን እንዴት መጠቀም የተሻለ ነው?

ጸጉር ላይ ዊግ የምትቀጥል ሴት
የምስሉ መግለጫ,ለሳምንታት ጸጉር ላይ የሚቀጠል ዊግ ጎጂ ለሆኑ ኬሚካሎች እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ጠቆሙ

በኬሚካል የታከሙ የፀጉር ማስረዘሚያዎችን ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለመጠቀም የተረጋገጠ መንገድ የለም። ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚታሰቡ እርምጃዎች ቢሆኑም አስተማማኝ ላይሆኑ ይችላሉ ሲል ጥናቱ አመልክቷል።

ፀጉር ላይ ከመቀጠሉ በፊት ማጠብ ለምሳሌ የቆዳ መቆጣትን ለመቀነስ በኮምጣጤ ማጠብን ጨምሮ ደኅንነት ስለማረጋገጡ ምንም ተጨባጭ መረጃ የለም።

በጥናቱ ውስጥ ፍተሻ ከተደረገባቸው 43 ናሙናዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ሳይንቲስቶች ከለዩዋቸው አደገኛ ኬሚካሎች የፀዱ ሆነው ተገኝተዋል።

ሁለቱም “መርዛማ ያልሆኑ” ወይም “ከመርዛማ ነገር ነጻ የሆኑ” ተብለው ተለይተዋል። ነገር ግን ፍራንክሊን እንዲህ ያሉት መግለጫዎች የተሳሳተ ማረጋገጫ ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“እነዚህ መግለጫዎች በማንኛውም አካል ቁጥጥር ስር አይደሉም፤ ስለዚህ ኩባንያዎች ምርቱ ላይ ሊለጥፉት ስለሚችሉ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት አይኖርም።”

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጎጂ የሆኑ ካንሰር የሚያስከትሉ ንጥረ ነገሮችን በተመለከተ አዳዲስ ጥብቅ ሕጎች በነሐሴ 2026 ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን የፀጉር ባለሙያዎች እንደሚሉት የፀጉር ማስረዘሚያዎችን በመቆጣጠር ረገድ ያለው ክፍተት ሸማቾች ሙሉ በሙሉ ጥበቃ አያገኙም ማለት መሆኑን ያስጠነቅቃሉ።

ኮስሞቲክስ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው እና የደኅንነት ፍተሻዎች የሚካሄድባቸው ናቸው። ነገር ግን የፀጉር ማስረዘሚያዎች በአብዛኛው በተለየ መንገድ ስለሚመደቡ ፍተሻ አይካሄድባቸውም።

ቀደም ባሉት ጥናቶች የፀጉር ማቅለሚያዎች እና ማለስለሻዎች ለጡት ካንሰር እንደሚያጋልጡ ተለይተዋል። ሆኖም ግን ከፀጉር ማስራዘሚያዎች በተለየ መልኩ እነዚህ ምርቶች እንደ መዋቢያ ምርቶች ቁጥጥር የሚደረግባቸው እና የደኅንነት ፍተሻዎች የሚካሄድባቸው ናቸው።

የዩኬ ብሔራዊ የፀጉር እና የውበት ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካሮላይን ላሪሴይ “ደንቡ የሚሠራው ምርቶች በትክክል ከተመደቡ እና ወደ አገር በሚገቡበት እና በሚሸጡበት ቦታ ላይ ተግባራዊ ከተደረጉ ብቻ ነው” ይላሉ።

“ይህ እውነተኛ ክፍተት ነው፣ እናም ይህ ጥናት መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ግልጽ አድርጓል።”

በአውሮፓውኑ 2016 ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ብዙ የተሳሳቱ መግለጫዎች የተለጠፈባቸው የሰው ሠራሽ ፀጉሮችን አግኝቷል።

አንዳንድ አምራቾች በድረ ገጾቻቸው ላይ ሸማቾች ከመግዛታቸው በፊት የፀጉሩን ጥራት እንዲፈትሹ ያስጠነቅቃሉ። ነገር ግን ሳይንቲስቶች ይህ የእነሱ ኃላፊነት መሆን የለበትም ይላሉ።

ፍራንክሊን “ገበያ ላይ ባይቀርቡ ኖሮ፣ መቼም ቢሆን መምረጥ አይጠበቅብንም ነበር” ሲሉ ይሞግታሉ።

“ዊግ ወይንም ሂውማን ሄር የሚጠቀም ማንኛውም ሰው ስለ ግኝቶቹ ግድ ሊለው ይገባል።”