
ከ 2 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
የዓለም ባንክ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር በተዘረጋበት ፕሮጀክት ላይ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እና ማጭበርበር ፈጽመዋል ያላቸውን ሦስት የዩናይትድ ኪንግደም አማካሪ ተቋም የአፍሪካ ቅርንጫፎች አገደ።
እገዳው የተጣለው ‘ፕራይስዋተርሐውስኩፐር’ (ፒደብሊውሲ) የተባለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሞሪሺሽ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ውስጥ በሚገኙ ቅርንጫፎች ላይ ነው።
እንደ ዓለም ባንግ ገለጻ፤ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት የፒደብሊውሲ ቅርንጫፎች በኢትዮጵያ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ኬንያ በሚያስተላልፈው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚከናወንበት ወቅት ነው።
ምሥራቅ አፍሪካ አገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የተያዘ እቅድ አካል በሆነው በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት፤ 2,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተላልፉ መስመር በሁለቱ አገራት መካከል ይዘረጋል።
በዓለም ባንክ በሚደገፈው የመጀመሪያ ምዕራፍ፤ ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር የሚያስተሳስር አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኤሌክትሪክ መስመር እንዲዘረጋ ያደርጋል።
ዓለም ባንክ በሦስቱ ኩባንያዎች ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ኩባንያዎቹ ለቀጣይ 21 ወራት የዓለም ባንክ በገንዘብ በሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች እና የተለያዩ ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም።
የዓለም ባንክ እንደገለጸው ኩባንያዎቹ፤ በአማካሪ ተቋምነት እንዲመረጡ ለማድረግ ሲሉ በአውሮፓውያኑ 2019 ምሥጢራዊ የግዥ መረጃን ከፕሮጀክት ኃላፊዎች አግኝተዋል።
ኩባንያዎቹ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያስችል መረጃ ተቀብለውበታል የተባለው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት ለማዘጋጀት የሚታሰር ውል እንደነበር ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ኩባንያዎቹ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ቋሚ የንብረት ቆጠራ እና የዋጋ ግመታ አገልግሎት የሚያካትት ውል ለማግኘት ተጽዕኖ ለማድረግ ሞክረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
እንዲሁም ከኩባንያዎቹ አንዱ፤ የዋና ባለሙያዎችን ብቃት በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ እንደሸጠ እና በኮንትራት አፈጻጸም ወቅት ንዑስ ኮንትራትን የተመለከቱ መረጃዎችን ሙሉ ለሙሉ ይፋ እንዳላደረገ ተገልጿል።
በኩባንያዎቹ የተፈጸሙት ድርጊቶች፤ ውድድርን ለማስቀረት የመመሳጠር እና የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከል የዓለም ባንክ የሚከተለውን መመሪያ የጣሱ መሆኑንም አመልክቷል።
የባንኩን የምርመራ ግኝት ተከትሎ ኩባንያዎቹ ድርጊቶቹን መፈጸማቸውን ማመናቸው በባንኩ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
እንዲሁም በባንኩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ በሚታገዱባቸው 21 ወራት ውስጥ በፕሮጀክቶች ሥራ ውስጥ መመሪያዎችን ለማክበር እና ተዓማኒነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ፕራይስዋተርሐውስኩፐር (ፒደብሊውሲ) ዋና መሥሪያ ቤቱ በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን የሚገኘው ዓለም አቀፉ የማማከር፣ የኦዲት፣ የማረጋገጥ፣ የታክስ እና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለንግድ እና ለሌሎችም ድርጅቶችን የሚሰጥ ተቋም ነው።
ኩባንያው በተለያዩ አገራት ውስጥ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በተያያዘ አሁን በዓለም ባንክ ዕገዳ የተጣለባው በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት ሦስቱ ናቸው።
