ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ቪኦኤ ከመቋረጡ በፊት በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በዲጂታል ይዘቶችን በ50 ቋንቋዎች ያሰራጭ ነበር
የምስሉ መግለጫ,ቪኦኤ ከመቋረጡ በፊት በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በዲጂታል ይዘቶችን በ50 ቋንቋዎች ያሰራጭ ነበር

ከ 3 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) የተዘጋበት መንገድ “ሕገ-ወጥ” መሆኑን በመጥቀስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ወሰኑ።

ዳኛው ሮይስ ላምበርዝ ባለሥልጣናት ዓለም አቀፉን መገናኛ ብዙኃን በድጋሚ ወደ አየር እንዲመልሱ የአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥተዋል።

ቪኦኤ የናዚ ፕሮፓጋንዳን ለመመከት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር የተቋቋመው።

ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለግራ ዘመም ቡድኖች ያደላል ሲሉ የሚከሱትን ቪኦኤ እንዲዘጋ የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ትራምፕ እንደ ሬዲዮ ፍሪ አውሮፓ እና ሬዲዮ ፍሪ እስያ ያሉ ድረ-ገጾች “ከሚመለከተው ሕግ ጋር በሚስማማ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ እንዲወገዱ” አዝዘዋል።

የአሜሪካ ሬዲዮን፣ ሬዲዮ ፍሪ አውሮፓ እና ሬዲዮ ፍሪ እስያን ጭምር የሚቆጣጠረው እና የሚደግፈው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩኤስኤጂኤም) እንዲመሩም ካሪ ሌክን ሾመዋል።

ሌክ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የተቋማቱን ሠራተኞችን አባርረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት የቪኦኤ ሠራተኞችን ናቸው። ጥቂቶቹን ብቻ በሥራቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ክፍያ የሚፈጸምበት በአስተዳደራዊ እረፍት ላይ ነበሩ። እስራኤል ባለፈው ሰኔ ኢራንን ካጠቃች በኋላ የፋርስ አገልግሎት ዘጋቢዎች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

ባለፈው ሳምንት ላይ ዳኛ ላምበርት፤ አዲሷ ኃላፊ ሌክ በአሜሪካ ሴኔት ሹመታቸው ባለመጽደቁ የተቋማቱ ሠራተኞች እንዲታገዱ የማዘዝ ሥልጣን የላቸውም ብለው ነበር።

የፌዴራሉ ዳኛ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ብይን ደግሞ ጋዜጠኞቹን ከሥራ ለማባረር የተላለፈውን ውሳኔ “የዘፈቀደ እና የግዴለሽነት” ሲሉ ገልጸውታል። መንግስት ቪኦኤ የትኛዎቹን ቋንቋዎችንእና ቀጣናዎች ማገልገል እንዳለበት የሚወስነውን ሕግን ግምት ውስጥ እንዳላስገባ አክለዋል።

“ተከሳሾች ለውሳኔያቸው ምክንያት የሆነ፤ በመርህ ላይ የተመሰረተ ምንም ነገር አላቀረቡም” ሲሉ ላምበርት በውሳኔያቸው ጽፈዋል።

የትራምፕ አስተዳደርን የከሰሱት ሦስት የቪኦኤ ጋዜጠኞች ናቸው። ከከሳሾቹ አንዷ የሆኑት ፓትሲ ዊዳኩስዋራ የዳኛውን ውሳኔ አመስግነዋል።

«የአሜሪካ ህዝብ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የጋዜጠኝነት ሥራችንን መደገፍ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን» ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የአገሪቱ ሴኔት ውሳኔ በመጠበቅ ላይ የሚገኙት እና ሌክ እንዲተኩ ዕጩ ሆኑት ሳራ ሮጀርስ ይግባኝ ስለማለታቸው የተገለጸ ነገር የለም።

ቪኦኤ ከመቋረጡ በፊት በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በዲጂታል ይዘቶችን በ50 ቋንቋዎች ያሰራጭ ነበር።