March 19, 2026

ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ አማካሪ እና ሁለት እህት ኩባንያዎቹ፤ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወኑ ስራዎች ለ21 ወራት እንዳይሳተፉ ታገዱ። ኩባንያዎቹ የታገዱት “በምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት” ውስጥ ፈጽመዋቸዋል በተባሉ “የመመሳጠር” እና “የማጭበርበር” ድርጊቶች ምክንያት ነው።

የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት፤ ከወላይታ ሶዶ እስከ ኬንያዋ ሱስዋ ከተማ ድረስ የተዘረጋ 1,045 ኪሎሜትር የሚሸፍን የኃይል ማስተላለፊያን የያዘ ነው። ይህ ፕሮጀክት መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው “የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ፕሮግራም” (Eastern Africa Power Integration Program) የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው።

በኬንያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መጠንን ለማሳደግ እና ዋጋውን ለመቀነስ የተነደፈው ይህ ፕሮጀክት፤ ኢትዮጵያን ወደ   ጎረቤቷ ከምትልከው ኤሌክትሪክ ገቢ እንድታገኝ ያደረጋት ነው። በሁለቱ ሀገራት መካከል 500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ቮልቴጅ መስመር የተዘረጋ ሲሆን ኬንያ በአሁኑ ወቅት 200 ሜጋዋት ኤሌሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ትገዛለች።

በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በፈረንሳይ የልማት ፋይናንስ ተቋም (AFD) ድጋፍ የተገነባው ይህ ፕሮጀክት፤  1.2 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ወጥቶበታል። በዚህ ፕሮጀክት የእቅድ ስራ ላይ ዋና መሥሪያ ቤቱን በለንደን ያደረገው  “ፕራይስ ዋተር ሀውስ ኩፐርስ” (PwC) የተሰኘው እውቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ተሳትፏል። 

የኦዲት እና ማማከር ሥራዎችን በማከናወን በዓለም ሥመ ጥር ከሆኑ የዘርፉ ተቋማት አንዱ PwC በፕሮጀክቱ የተሳተፈው፤ በአፍሪካ ባቋቋማቸው ተቀጥላ ኩባንያዎች አማካኝነት ነው። የዓለም ባንክ ትላንት ረቡዕ መጋቢት 9፤ 2018 ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ በተቋሙ ሶስት ተቀጥላ ኩባንያዎች ላይ የእገዳ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

የታገዱት ኩባንያዎች መቀመጫውን በሞሪሺየስ ያደረገው “ፕራይስ ዋተር ሀውስ ኩፐርስ አሶሺየትስ አፍሪካ” ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ (PwC Associates)፣ “ፕራይስ ዋተር ሀውስ ኩፐርስ ኬንያ” እና “ፕራይስ ዋተር ሀውስ ኩፐርስ ሩዋንዳ” የተሰኙት ናቸው። እነዚህ የተቋሙ የአፍሪካ ተቀጥላ ኩባንያዎች እርምጃ የተወሰደባቸው፤ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ አማካሪ ለመቅጠር ከወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ ነው። 

ኩባንያዎቹ “ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተጽዕኖ ለማሳደር ከፕሮጀክት ባለሥልጣናት ምስጢራዊ የቅጥር መረጃ መቀበላቸው” መረጋገጡን ዓለም ባንክ በትላንቱ መግለጫው ጠቅሷል። ኩባንያዎቹ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት “የቋሚ ንብረት ቆጠራ እና ግምት የሥራ ውልን”፤ መቀመጫውን በሞሪሺየስ ላደረገው PwC Associates እንዲሰጥ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ዓለም ባንክ በመግለጫው ይፋ አድርጓል። 

PwC Associates በቋሚ ንብረት ቆጠራ እና ግምት ሥራ ውል መረጣ እና ትግበራ ወቅት፤ ቁልፍ የሆኑ ባለሙያዎች  ብቃት፣ የቅጥር ሁኔታ እንዲሁም ለስራ የሚገኙ መሆናቸውን በተመለከተ “በተሳሳተ መንገድ” እንዳቀረበ ዓለም ባንክ ከዋሽንግተን ባወጣው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። ከዚህ በተጨማሪ ኩባንያው የንዑስ አማካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ይፋ ሳያደርግ መቅረቱንም አመልክቷል። 

እነዚህ ድርጊቶች በዓለም ባንክ የአማካሪዎች መመሪያዎች መሰረት፤ “መመሳጠር እና ማጭበርበር” ተብለው የተበየኑ መሆናቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። በእዚህ ምክንያት በሶስቱ ኩባንያዎች እና እነርሱ በሚቆጣጠሯቸው ሌሎች ተቋማት ላይ የተጣለው ዕገዳ፤ በዓለም ባንክ በገንዘብ በሚደገፉ ማናቸውም ስራዎች እንዳይሳተፉ ክልከላ የሚጥል ነው።

ሶስቱ ኩባንያዎች “ጥፋታቸውን በማመናቸው”፣ “በመተባበራቸው” እና “ተዓማኒነትን በተመለከተ የውስጥ የአሰራር ስርዓታቸውን ማሻሻላቸው”፤ በዓለም ባንክ የተጣለባቸው ቅጣት “ወደ 21 ወራት ዝቅ እንዲልላቸው” ማድረጉ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)