March 19, 2026

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ሊያካሄደው የነበረውን መደበኛ ስብሰባ፤ የፓርላማ አባላት ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ በመቅረቱ ለመሰረዝ ተገደደ። ምክር ቤቱ ውሳኔውን ከማስተላለፉ አስቀድሞ፤ የፓርላማው ሰራተኞች “ዝግ ስብሰባ” እንደሚደረግ በመግለጽ ጋዜጠኞች ከስብሰባ አዳራሽ እንዲወጡ አድርገዋል።

መደበኛ ስብሰባዎቹን ዘወትር ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለዛሬ መጋቢት 10፤ 2018 በስድስት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት አጀንዳ ይዞ ነበር። ከአጀንዳዎቹ አራቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያደረጋቸውን የብድር ስምምነቶች የሚመለከቱ ናቸው።

ፓርላማው በዛሬው ስብሰባው በአጀንዳነት የያዘው ሌላው ጉዳይ፤ ላለፉት 12 ዓመታት በስራ ላይ የቆየውን የጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያን ተመልክቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት ነበር። ሆኖም ከዚህ ቀደም እምብዛም ባልተለመደ መልኩ፤ ፓርላማው “ምልዐተ ጉባኤ አልተሟላም” በሚል ምክንያት መደበኛ ስብሰባውን ሳያካሄድ ቀርቷል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አራት የፓርላማ አባላት፤ ይኸው ምክንያት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በኩል እንደተነገራቸው ገልጸዋል። ምልዓተ ጉባኤው ካልተሟላባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ ለእረፍት ወደ ምርጫ ክልላቸው የሄዱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጊዜ ባለመመለሳቸው መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ እንደተረዱ የፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።

በ1994 የተሻሻለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የዕረፍት እና የስራ ጊዜ ለመወሰን የወጣ አዋጅ፤ ፓርላማው በዓመት ለሁለት ጊዜያት ለዕረፍት እንደሚበተን ይደነግጋል። የመጀመሪያው የዕረፍት ጊዜ በየዓመቱ ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 30 የሚቆይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሐምሌ 1 እስከ መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ዋዜማ ድረስ ያለውን ወቅት የሚሸፍን ነው።

በአዋጁ በተደነገገው መሰረት በዚህ ዓመትም ለዕረፍት የተበተኑት የፓርላማ አባላቱ፤ በየካቲት አጋማሽ ካሉበት ተጠርተው የዓመቱን የመጀመሪያ አስቸኳይ ስብሰባቸውን አካሄደዋል። የተወካዮች ምክር ቤት በዚህ አስቸኳይ ስብሰባው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለተጨማሪ ስምንት ወራት ማራዘሙ አይዘነጋም።

በዚሁ የየካቲት ወር የዕረፍት ጊዜ በፓርላማው ስር ያሉት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ስብሰባቸውን ሲያካሄዱም ቆይተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ በጠራው በዛሬው ስብሰባ ግን 547 መቀመጫ ካለው ፓርላማ ግማሽ ያህሉ ሳይገኙ ቀርተዋል።

የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ እና የስራ ዘመን በሚዘረዝረው ድንጋጌው ስር፤ የምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ የተሟላ እንደሚሆን አስፍሯል። ምክር ቤቱ የዛሬውን መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ ያልቻለው ምልዓተ ጉባኤው ባለመሟላቱ እንደሆነ ለፓርላማ አባላቱ ቢነገራቸውም፤ የተገኙ አባላት ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።  

በዛሬው መደበኛ ስብሰባ የፓርላማ አባላት ተሟልተው ያልተገኙበት ሌላው ምክንያት፤ ለመጪው ምርጫ በድጋሚ ዕጩ የሆኑት ተመራጮች ራሳቸውን የማስተዋወቂያ መድረክ ስላላቸው እንደሆነ መስማታቸውንም እነዚሁ ምንጮች አክለዋል። በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ሀገር አቀፍ መጨረሻ የሚወዳደሩ ዕጩዎች፤ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው ከጥር 1 እስከ ግንቦት 19 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)