March 19, 2026

በሽብር ወንጀል ተጠርጥራ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ያለችው ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፤ ባጋጠማት የጤና እክል ምክንያት በራሷ ወጪ ፍራሽ ለመግዛት እንዲፈቀድላት ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረበች። ጋዜጠኛዋ ጥያቄዋን በዛሬው ዕለት በጠበቃዋ በኩል ያቀረበችው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።

የተከሳሿ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ጋዜጠኛ ገነት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኩላሊት ህመም ውስጥ ቆይታለች። ደንበኛቸው በቅርብ ጊዜ ባደረገችው ምርመራ በሁለቱም ኩላሊቶቿ ላይ “ጠጠር” መገኘቱን የገለጹት ጠበቃው፤ በህመሟ ምክንያት “ለመቀመጥ እና መተኛት” መቸገሯን አስረድተዋል።

ጋዜጠኛ ገነት በታሰረችበት ማረሚያ ቤት የሚገኘው ፍራሽ “ቶሎ የሚጎደጉድ” በመሆኑ ህመሟን ሊያስታግስላት እንዳልቻለም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። በሀኪም ትዕዛዝ መሰረት ማረሚያ ቤቱ “ተስማሚ እና በቀላሉ የማይጎረጉድ ፍራሽ እንዲያቀርብ” ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠበቃው አክለዋል። 

ሆኖም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሁሉም ታራሚዎች እያቀረበ ካለው ውጪ የተለየ ፍራሽ እንደማያቀርብ ምላሽ መስጠቱን ጠበቃው ተናግረዋል። ይህን ምላሽ መሰረት በማድረግ ጋዜጠኛ ገነት በራሷ ወጪ ፍራሽ ለመግዛት ከማረሚያ ቤቱ ፈቃድ ብትጠየቅም፤ ተቋሙ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልደረሰው በቀር ጥያቄውን እንደማያስተናግድ ማሳወቁን አቶ ገዛኸኝ አብራርተዋል።

የማረሚያ ቤቱን ምላሽ በመንተራስም ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 10፤ 2018 ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባታቸውን ጠበቃው ተናግረዋል። ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ፣ አንደኛ የህገ መንግስት እና ሕገ መንግስት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት የቀረበው አቤቱታ፤ ለኩላሊት ህመም የሚሆን ደረቅ ፍራሽ በግል ገዝቶ መጠቀም እንዲፈቀድ የሚጠይቅ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይኸው አቤቱታ፤ ከፍርድ ቤቱን ፍቃድ በተጨማሪ ጋዜጠኛ ገነት ታስራ ለምትገኝበት ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ጥያቄ የቀረበበት ነው። አቤቱታው የቀረበለት ችሎት፤ የማረሚያ ቤቱን አስተያየት ለመስማት ለመጪው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 16፣ 2018 ቀጠሮ ሰጥቷል።

“መድሎት” የተሰኘ የበይነ መረብ ሚዲያ ላይ በመስራት ላይ የነበረችው ጋዜጠኛ ገነት፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው በመጋቢት 2015 ዓ.ም. ነበር። ዐቃቤ ህግ ጋዜጠኛ ገነት እና ሌሎች ሶስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተካተቱበትን የሽብር ወንጀል ክስ የመሰረተው ደግሞ በሰኔ 2015 ዓ.ም ነው።

በእነ ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ስር ከተከሰሱ 51 ተጠርጣሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ገነት፤ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ጉዳይዋን በማረሚያ ቤት ሆና ስትከታተል ቆይታለች። የጋዜጠኛዋን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ባሳለፈው ውሳኔ እርሷን ጨምሮ በድምሩ 14 ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ችሎቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ከሚያዝያ 26 እስከ 30፤ 2018 ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ ቀጠሮ ይዟል። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ከሳምንት በፊት የተከበረውን የዓለም ሴቶች ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ጋዜጠኛ ገነት እና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሰችው መስከረም አበራ ለእስር የተዳረጉት “በሙያቸው ምክንያት” እንደሆነ አስታውሶ ነበር። 

ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እስር “በመናገር ነጻነት ላይ የተቃጣ የቀጥታ ጥቃት” መሆኑንም ሲፒጄ በዚሁ መግለጫው ላይ አስገንዝቧል። ጋዜጠኛ ገነት እና መስከረም በቀረበባቸው የሽብር ክስ “ጥፋተኛ” ሆነው ከተገኙ “የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው” የጠቀሰው ሲፒጄ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስር እንዲለቅቃቸውም ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)