ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የታይላንዷ ማዩ ሬናሬ መርከብ መጋቢት 2 ጥቃት ደርሶባታል

ከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢራን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የጭነት መርከቦች ላይ በየጊዜው ጥቃት ብትሰነዝርም ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ 100 የማይሞሉ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ አልፈዋል።

አንዳንድ የነዳጅ እና የዕለት ተዕለት ፍጆታ እቃዎች አሁንም በወሽመጡ እየተጓዙ ቢሆንም፤ የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 21 ጀምሮ ዕለታዊው የመርከብ ፍሰት 95 በመቶ ቀንሷል።

ከጦርነቱ በፊት በየዕለቱ ወደ 138 የሚጠጉ መርከቦች ወሽመጡን አቋርጠው እንደሚያልፉ ዓለም አቀፉ የንግድ መርከሞች መረጃ ማዕከል አስታውቋል። ይህም ከዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛውን የሚይዝ ነው።

የመርከብ ተንታኙ ክፕለር ያቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ወር 99 መርከቦች በወሽመጡ በኩል ያለፉ ሲሆን ይህም ዕለታዊውን አማካይ ከ5-6 መርከቦች ብቻ አድርጎታል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ጉዞውን የሚያደርጉትን መርከቦች እና የሚጋፈጧቸውን አደጋዎች ተከታትሏል።

በቅርቡ በወሽመጡ ካለፉ መርከቦች አንድ ሦስተኛዎቹ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

14ቱ መርከቦች በቴህራን ባንዲራ ስር የተጓዙ ሲሆን ቀሪዎቹ ከቴህራን የነዳጅ ንግድ ጋር በተጠረጠረ ግንኙነት ምክንያት በማዕቀብ ስር ያሉ መርከቦችን ያካትታሉ።

ዘጠኝ መርከቦች ከቻይና ጋር ግንኙነት ባላቸው ኩባንያዎች የተያዙ ሲሆኑ ስድስቱ ደግሞ መዳረሻቸው ሕንድ እንደሆነ ታውቋል።

በግሪክ ኩባንያዎች ባለቤትነት የተያዙ መርከቦችን ጨምሮ በርካታ ከኢራን ጋር ግንኙነት የሌላቸው መርከቦች በአገሪቱ ወደቦች ላይ ደርሰው ነበር።

አንዳንድ መርከቦች ወሽመጡን በተሳካ ሁኔታ ለማቋረጥ ከወትሮው የበለጠ ረጅም መንገድ እየተጓዙ ነው።

የፓኪስታን ባንዲራየሚያውለበልበው የነዳጅ መርከብ መጋቢት 15 ቀን በወሽመጡ በኩል ሲያልፍ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ወደ ኢራን የባህር ዳርቻ ተጠግቶ እንደተጓዘ ይጠቁማል።

መርከቧ “በኢራን ለተቀመጡ አቅጣጫዎች ምላሽ እየሰጠች” ሊሆን እንደሚችል በአሜሪካው የራንድ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ብራድሌይ ማርቲን ተናግረዋል።

መንገዱ ፈንጂዎች መኖራቸውን ወይም የኢራን ባለሥልጣናት መርከቧን ለመለየት ቀላል እንዲሆንላቸው የሚያደርጉት ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

መርከቦቹ አቅጣጫ እንዲቀይሩ በማስገደድ ወደ ኢራን የውሃ ክልል እና የቴህራን የባህር ሕግ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው ሲሉ የዊንድዋርድ የባህር ኃይል አናሊቲክስ ባልደረባዋ ሚሼል ዊሴ ቦክማን ተናግረዋል።

“በእኔ ግምት ኢራን የጥቃት እና የቦምብ ፍርሃትን በመጠቀም የባህር ወሽመጥዋን እየዘጋች እና እየተቆጣጠረች ነው”።

“ለዚህም ነው ሁሉም በዓለም አቀፍ መንገድ ከመሄድ ይልቅ በግዛትዋ ዳርቻዎች ማቋረጥ ያለባቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የባሕር ኃይል ትንተና ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ማይክል ኮኔል መርከቦች የተለየ መንገድ እየመረጡ በመሆኑ ይስማማሉ።

“ምናልባትም ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር በተወሰነ መስመር ከተጓዙ ደህንነታቸው እንደሚጠበቅ ስምምነት ሊኖራቸው ይችላል።”

መርከቦች የተጋረጡባቸው ስጋቶች

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በኢራን የባሕር ዳርቻ ላይ የተጠቁ 20 የንግድ መርከቦች መኖራቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል። ሁሉም ግን በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ አልነበሩም።

መጋቢት 2 በታይላንድ የሚንቀሳቀሰው ግዙፉ ማዩሪ ናሪ መርከብ ለማለፍ ሲሞክር በሁለት ሚሳኤሎች ተመትቷል።

ከ23ቱ የመርከቡ አባላት መካከል ሦስቱ እንደሞቱ ይታመናል። መርከቧ በተመታችበት ወቅት በሞተር ክፍል ውስጥ ሳይያዙ እንዳልቀረ ይገመታል።

የመርከቧ ባለቤቶች ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደገለጹት የተረፉት መርከበኞች “መመታታቸውን ተከትሎ በባህር ላይ አሰቃቂ ሁኔታ አሳልፈዋል” ብለዋል።

በግሪክ ባለቤትነት ስር የሚገኘው ስታር ግዋይኔዝ እና የአሜሪካው ኤስ ሳፌሲ ቪሽኑ በተመሳሳይ ቀን ጥቃት ደርሶባቸዋል።

“የንግድ መርከብ መስመሮች የጦርነት ቀጠናዎች ሊሆኑ አይገባም” ሲሉ የኤም ሳፌሲ ቪሽኑ ባለቤት ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።

በጥቃቱ አንድ ሰው ሞቷል። 28ቱም የመርከቧ አባላት ከሚቃጠለው መርከብ ለማምለጥ ወደ ውሃው ውስጥ ለመግባት ተገደዋል ሲሉ ኤስ ቪ አንቻን ተናግረዋል።

“እነዚህ ባለሙያዎች ወታደሮች አይደሉም… ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲሳለጥ የሚያግዙ ባለሙያዎች ናቸው።”

ድሮኖች፣ ሚሳዔሎች፣ ፈጣን የጥቃት ጀልባዎች እና የተቀበሩ ፈንጂዎች ከባድ ፈተና ፈጥረዋል ሲሉ የኪንግስ ኮሌጅ የፍሪማን የአየር እና የጠፈር ተቋም ባልደረባው አሩን ዶውሰን ተናግረዋል።

ኢራን የአካባቢውን አቀማመጥም ልትጠቀምበት ትችላለች። ወሽመጡ ጠባብ እና ጥልቀት የሌለው የባህር ዳርቻ ብቻ ሳይሆን አካባቢው ተራራማም ነው። ይህ ደግሞ ኢራን ከፍተኛ ጥቃቶችን እንድትፈጽም ያስችላታል፤ መርከቦችም ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አይኖራቸውም።

እንዳይታዩ ለማድረግ በሚደረገው ሙከራ በርካታ መርከቦች ሆን ብለው ኤአይኤስ (አውቶማቲክ መለያ ስርዓት) የተሰኘውን የመከታተያ ስርዓታቸውን እያጠፉ ያሉ ይመስላሉ።

“ከእነዚህ [መርከቦች] አብዛኛዎቹ ዓይኖቻቸውን አጠፍተው ሲያቋርጡ ነበር” ይላል ከክፕለር የመጣው ዲሚትሪስ አምፓትዚዲስ።

ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ ሲገቡ መከታተያዎቻቸውን በማጥፋት ጀልባዎች ከካርታዎች እየጠፉ እና ከዚያም ከሰዓታት ወይም ከቀናት በኋላ በሌላ ቦታ እንደገና ብቅ ይላሉ።

ምንም እንኳን መርከቦች ያሉበትን ቦታ እንዲደብቁ ቢረዳቸውም፤ እንደ ክፕለር ያሉ በባሕረ ሰላጤው ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ለሚከታተሉ ድርጅቶች ተግዳሮቶችን ይፈጥራል።

“ሁሉም ነገር በተንታኞቻችን ማረጋገጫ እና በሳተላይት ምስሎችም ይረጋገጣል” ሲል አምፓትዚዲስ ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግሯል።