ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የእስር ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ሦስት ታዳጊዎች ተቀምጠው
የምስሉ መግለጫ,ሐሙስ ዕ፤ለትየኢራን መገናኛ ብዙኃን ሦስት ታዳጊዎች በፍርድ ቤት ሆነው ክሳቸውን ሲከታተሉ አሳይቷል

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢራን በጥር ወር በተካሄደው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ወቅት የፖሊስ መኮንኖችን በመግደል የተከሰሱ ሦስት ሰዎችን በሞት መቀጣቷን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህም ከሠልፎቹ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የመጀመሪያው ስቅላት መሆኑ ተገልጿል።

በስቅላት ከተቀጡት መካከል የኢራን ብሔራዊ የሬስሊንግ ቡድን አባል የሆነው ታዳጊው ሳሌህ መሃመድ እንደሚገኝበት ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።

የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው የሞት ቅጣቱ የተፈፀመው ሐሙስ ጠዋት በሰሜናዊ ቆም ግዛት ነው።

በታህሳስ ወር የተጀመረውና በጥር ወር የተባባሰው አገር አቀፍ ተቃውሞ በኢራን ባለሥልጣናት ከፍተኛ የኃይል እርምጃ ተወስዶ እንዲቆም ተደርጓል።

የመብት ተሟጋቾች መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ተናግረዋል።

ከኢራን አብዮታዊ ጓድ ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል መህዲ ጋሴሚ እና ሰኢድ ዳቮዲ በቆም በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች ሁለት የፖሊስ መኮንኖችን በመግደላቸው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ሲል ዘግቧል።

የዜና ተቋሙ እንደዘገበው ከሆነ ኢራን ተቃዋሚዎቹ ላይ የሞት ፍርድ ለመስጠት ከተጠቀመባቸው ክሶች አንዱ የእስላማዊ ሪፐብሊኩ ተቃዋሚዎች ላይ የምትገለገልበትን ‘በፈጣሪ ላይ ጦርነት ማወጅ’ “ሞሐሬቤህ” የተሰኘውን ነው።

እንደ የመብት ተሟጋቾች ገለጻ ሦስቱ ሰዎች የደረሰባቸውን ስቅይት ተከትሎ ጥፋተኛ መሆናቸውን ያመኑ ሲሆን ፍትሃዊ ፍርድ ሳያገኙ ተገድለዋል ብለዋል።

የታዳጊዎቹ ሞት የተሰማው ኢራን ኢራናዊ-ስዊድናዊ ዜጋን ከገደለች ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ኩሩሽ ኬይቫኒ ለእስራኤል በመሰለል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በኋላ ተሰቅሏል ሲል የኢራን የፍትህ ሚኒስቴር የዜና ተቋም ሚዛን ኦንላይን ዘግቧል።

ኬይቫኒ በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ኢራን ከእስራኤል ጋር ባደረገችው የ12 ቀናት ጦርነት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።

የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ “የስዊድን ዜጋን ለመግደል ምክንያት የሆነው ሕጋዊ ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀ እንዳልሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል።

በ31ቱም የኢራን ግዛቶች ውስጥ በ180 ከተሞችና አካባቢዎች የተዛመተው ይህ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የኢራን የውጭ ምንዛሬ ውድቀትና የኑሮ ውድነት በመጨመሩ ምክንያት የተቀሰቀሰ ነው።

የተቃውሞ ሠልፉ በፍጥነት ወደ ፖለቲካዊ ለውጥ ጥያቄዎች ያደገ ሲሆን ከ1979 የእስልምና አብዮት ወዲህ አገሪቱን ለሚመራው ቡድን እጅግ ከባድ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሆኗል።

የኢንተርኔትና የመገናኛ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በመዘጋታቸው በአገሪቱ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢያደርገውም፣ ተቃዋሚዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጸጥታ ኃይሎች የሚወሰደው ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ከዚህ በፊት ከታየው ሁሉ የተለየ ነበር።

በአሜሪካ የሚገኘው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የዜና ኤጀንሲ (ሃርና) እንደዘገበው፣ በጥር ወር በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ቢያንስ 7,000 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 6,488 ተቃዋሚዎች እና 236 ሕፃናት ይገኙበታል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ተቃዋሚዎች ከተገደሉ በኢራን ላይ “ጠንካራ እርምጃ” እንደሚወሰድ አስጠንቅቀው ነበር። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከዚያ በኋላ ተቃዋሚ ሠልፈኞቹን የመግደል “ምንም እቅድ” እንደሌለ ተናግረዋል።

በኖርዌይ የሚገኘው የኩርድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሄንጋው እንደዘገበው፣ በጥር 8 የታሰረው እና ቤተሰቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚገደል የተነገረው ኤርፋን ሶልታኒ የተባለ አንድ ተቃዋሚ በኋላ ላይ በዋስ መፈታቱ ተዘግቧል።

የኢራን የፍትህ አካላት የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ክደዋል፣ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ክሶች የእስር ጊዜ ብቻ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ሰፊ የሆነ ጥቃት በመሰንዘር የአገሪቱን የበላይ መሪ ገድለዋል። ኢራን በባህረ ሰላጤው ውስጥ በእስራኤል እና በአሜሪካ ተባባሪ አገራት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ምላሽ ሰጥታለች።