ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ መሠረተ ልማት ጥቃቶች የፈጠሩት ውጥረት በተጠናከረበት በዚህ ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የኢራንን የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት የፈጸመችው ‘ብቻዋን ነው’ ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል የኢራንን ሳውዝ ፓርስ ስትደበድብ ቴህራን በበኩሏ በኳታር የሚገኙ የኃይል ማዕከላትን እና በባህረ ሰላጤው አገራት የሚገኙ የነዳጅ ዒላማዎችን በማጥቃት አጸፋውን መልሳለች።

ጥቃቶቹ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት የሆኑ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለጥቃቱ አስቀድመው እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ጉዳዩ እስራኤል እና አሜሪካ በጦርነት ግባቸው ላይ እየተናበቡ ነውን? የሚሉ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የእስራኤሉ መሪ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትራምፕ በኢነርጂ ዒላማዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በሳውዝ ፓርስ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ከአሜሪካ ጋር አስቀድሞ በተናበበ መልኩ ቢከናወንም በትራምፕ ምላሽ አለመገረማቸውን ሦስት ስማቸው ያልተገለጸ የእስራኤል ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።

ኔታንያሁ አገራቸው አሜሪካን ወደ ጦርነቱ እንደጎተተች ወይም ትራምፕን “እንዳሳሳተች” መገለጹን አስተባብለው፤ የአሜሪካን መሪ ምን ማድረግ እንዳለበት ማንም ሰው ሊነግረው እንደማይችል ገልጸዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በጀመሩት ጦርነት ተከትሎ በኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ የተሰነዘሩት ጥቃቶች የጨመሩ ሲሆን ቴህራንም በሆርሙዝ ወሸመጥ በኩል የመርከብ ጉዞን በመገደብ ምላሽ ሰጥታለች።

100 ሚሊዮን በርሜል ከሚሆነው የዓለም ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ አንድ አምስተኛ የሚሆነው በኢራን የባህር ዳርቻ ክፍል በሚገኘው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ይጓጓዛል።

ኢራን በዓለም ላይ ትልቁን የተፈጥሮ ጋዝ የሚያቀነባብረውን ፋብሪካ ጨምሮ በኳታር ራስ ላፋን የኢንዱስትሪ አካባቢ ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ፣ ኳታርኢነርጂ 17 በመቶ የሚሆነው አቅሙ መጎዳቱን አስታውቋል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አብዱራህማን አል-ታኒ ጥቃቱ “በዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር” አስጠንቅቀው “በጣም አደገኛ” ሲሉ ጠርተውታል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው ኢራን መሠረተ ልማቷ እንደገና ከተመታ “እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥ” ተናግረዋል።

ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ኢራን በኳታር ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ በፍጥነት ጨምሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በነዳጅ ገበያ ላይ የተፈጠረውን ጭማሪ ለመቆጣጠር በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችውን የተወሰኑ ማዕቀቦች ለማንሳት እያሰበች መሆኑ ታውቋል።

ኔታንያሁ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እስራኤል በኢራን ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰች እንደሆነ እና በካስፒያን ባህር የኢራንን የባህር ኃይል እንዳጠቃች ተናግረዋል።

እስራኤል የኢራንን አስተዳደር ለማዳከም እየሠራች እንደሆነ ቢናገሩም አገዛዙን ለማስወገድ ከፈለጉ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የኢራናውያን እንደሆነ ገልጸዋል።

“ሁኔታዎቹን ማመቻቸት እንችላለን፣ ነገር ግን እነዚያን አጋጣሚዎች መጠቀም አለባቸው” ብለዋል።

“[አገዛዙ] ከተረፈ በጣም ደካማ ይሆናል፣ ለአስርተ ዓመታት የገነባቸው ኢንዱስትሪዎችም አይኖሩም።”

ሐሙስ ዕለት በሰሜናዊ እስራኤል ሃይፋ በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ላይ ኢራን አደረሰችው በተባለ ጥቃት ምክንያት እሳት መፈጠሩ ታይቷል። የእስራኤል የኢነርጂ ሚኒስትር ኤሊ ኮሄን በሰሜን የአገሪቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ” ጉልህ አይደለም” ብለዋል።