Yared Hailemariam 

መልዕክተ ቅዳሜ

አሥርቱ የብልጽኛ ክሽፈቶች፤ ለአቅመ መንግስት ባልደረሰ አካል እጅ የወደቀች አገር

+++++++

በቴሌግራም ለመከታተል፤ https://t.me/yaredH_2024

እንደምን ከርማችኋል የመልዕክተ ቅዳሜ አንባቢዎች፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታን በሥራ ብዛት የተስተጓጎለችው መልዕክተ ቅዳሜ የዛሬ ትኩረቷ በተደጋጋሚ በቃለ ምልልሶቼ የገለጽኳቸው የአብይ አስተዳደር አገር ለመምራት የሚያስችል ብቃት እና ቁመና ማጣት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቴ ሰዎች ብልጽግና አገር የመምራት ብቃቱ እንደውም ጨምሯል፣ ተጠናክሯል የሚሉ ጥቅል መከራከሪያዎችን ሲያነሱ ስላስተዋልኩ ነው፡፡

በመጀመሪያ ለአንባቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያህል አንድ መንግስታዊ አስተዳደር ጥሩ ወይም ጠንካራ ወይም ጤኔኛ እና መካከለኛም ቢሆን አገር የማስተዳደር አቅም አለው የሚባለው ከዚህ በሚከተሉት መመዘኛዎች ተፈትኖ ነው፡፡ እነሱም፤ የሕግ የበላይነት እና ፍትሃዊ የሆነ የጸና የሕግ ሥርአት ሲኖር፣ ተጠያቂነት እና ግልጽነትን ያረጋገጠ መንግስታዊ ሥርአት ሲኖር፣ የመንግስታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ውጤታማነትና ብቃት ሲኖር፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና ቅቡልነት ሲኖር ወይም ሲረጋገጥ፣ የተደላደለና የተረጋጋ ኢኪኖሚያዊ አቅም መፍጠር ሲቻል፣ ለሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የሚችል እና የረዥም ጊዜ ግቦችን ሊያሳካ የሚችል ፖሊሲና እቅዶች ያሉት፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ የአገሪቱን ግዛቶች በበቂ ሁኔታ መስጠበቅ እና ሉአላዊነቷን አለማስደፈር፣ ሰብአዊ መብቶችን በአግባቡ የሚያስጠብቅ እና ለህዳጣን ልዩ ጥበቃዎችን ማድረግ የሚችል ሆኖ መገኘት እና ጠንካራ እና ብቃት ያለው የምርጫ ሥርአት በመዘርጋት ዜጎች በዲሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ መደላድሎችን መፍጠር መቻል ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ቁልፍ የመመዘኛ ነጥቦች በውስጣቸው ዝርዝር ንዑስ የመመዘኛ መስፈርቶችንም ይያዙ ናቸው፡፡

ከላይ በዘረዘርኳቸው አሥር ነጥቦት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው መንግስት ሲመዘን አንድም ለመንግስትነት የሚያበቁትን ሥራዎች እንዳልሰራ ብዙ ጥናቶችን እያመላከትኩ እና መረጃዎችን እያቀረብኩ ለማሳየት እችላለሁ፡፡ ይሁንና በዚህ አጭር እበይነ መረብ ጽሑፍ እያንዳንዱን ነጥብ በዝርዝር ማብራራት ባልችልም ዋና ዋና ነገሮችን በማንሳት ሃሳቡን ለውይይት ክፍት ላድርገው፡፡

1ኛ/ Rule of Law and Legal Certainty/ የሕግ የበላይነት እና ፍትሃዊ የሆነ የጸና የሕግ ሥርአትን በተመለከተ የአገዛዝ ሥርአቱ ለሕግ የበላይነት ያለው የተዛባ ግንዛቤ የተስተዋለው ገባ በጊዜ የአብይ አስተዳደር ሥልጣኑን በተቆናጠጠ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ነበር፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፓርላማ ከመሰየሙ በፊት የነበረው ምክር ቤት የለውጡ መንግስት ለሕግ የበላይነት መስፈን ያለው ተነሳሽነት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የደቦ ፍርድ እና ሥርአት አልበኝነት ሰፍኗል በሚል ለጠቅላዩ ማሳሰቢያ ሰጥቶ መሰናበቱን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን በአገሪቱ ውስጥ የታየው የሕግ የበላይነት መጥፋት እና የተረጋጋ የሕዝ ሥርአት አለመኖር አገሪቱ ዛሬ ለገባችበት ውጥንቅጥና ሥርአት አልበኝነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ብልጽግና እና የሕግ የበላይነት ፈጽሞ የማይተዋወቁ እስኪመስሉ ድረስ ብዙ ዘግናኝ የሆኑ ነገሮችን አስተናግደናል፡፡ ፍትህ በብሄር፣ በጥላቻና በቂም ስትጠለፍ አይተናል፡፡

2ኛ/ Accountability and Transparency/ ተጠያቂነት እና ግልጽነትን ያረጋገጠ መንግስታዊ ሥርአት መጥፋት እንዲሁ የብልጽግና መንግስት አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ከጠቅላዩ አንስቶ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት ለፈጸሟቸው ከሙስና አንስቶ በጦርነቶች ወቅት ለተፈጸሙ አስከፊ አለም አቀፍ ወንጀሎችና የሰባአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የለም፡፡ ወንጀለኞች በነጻነት ጠያቂ ሳይኖራቸው የሚንጎማለሉበትና የሚሾሙበት፣ ግፏን የሚሳደዱባት አገር ሆናለች፡፡ ጠቅላዩ ለምሰራው የኮሪደር ልማት ማንም በጀቱንም ሆነ አፈጻጸሙን ሊጠይቀኝ አይችልም ብለው ፓርላማውን እና ሕገ መንግስቱን ከጫማቸው ሥር ያደረጉበት አስከፊ ወቅት ነው፡፡

3ኛ/ Government Effectiveness and Efficiency/ የመንግስታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ውጤታማነትና ብቃት እንዲሁ በወሬ የቀረበት፣ ዜጎች በሄዱበት የመንግስት ተቋማት ሁሉ አልቅሰው፣ ተጉላልተው፣ አይን ባወጡ ሙሰኛ የመንግስት ሠራተኞች በጠራራ ጸሐይ ተዘርፈው እና ተራቁተው የሚሸኙበት፣ መሰረታዊ የሚባሉ የመንግስት አቅርቦቶች በጠቅላላ ዜጎች በአስተዳደሩ ብቃት ማነስ የተነሳ የተስተጓጎሉበት፣ መሰረታዊ አቅርቦቶች እንደ ኤለክትሪክ፣ ውሃ፣ ኢንተርኔት፣ ሕክምና፣ ትራንስፖርት፣ ነዳጅ፣ የአህል እና ሌሎች አቅርቦቶች ከዋጋ መናር በላይ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ያልቻለ መንግስት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሽንኩርት ከሱዳን እና ከቻይና፣ ብርቱካን ከግብጽ የምታስገባ አገር የሆነችው በዘመነ ብልጽኛ ነው፡፡

4ኛ/ Political Stability and Legitimacy/ የፖለቲካ መረጋጋት እና ቅቡልነት መጥፋት ሌላው የብልጽኛ መንግስት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ ጠቅላዩ በማጭበርበር ኢህአዴን አፍርሰው፣ የቅርብ ወዳጆቻቸውን እነ አቶ ለማ መገርሳን ክደው ብልጽግናን ከፈጠሩበት እለት አንስቶ ላለፉት ሰባት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ጠፍቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር የተከሰቱት ጦርነቶችና ግጭቶች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰቱን ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ በጋምቤላ አልፎ አልፎ የሚታየው ጥቃት ከአገዛዝ ሥርአቱ ቅቡልነት ማጣት ጋር የተያያዙ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የፈጠሯቸው ናቸው፡፡ ዛሬም አገሪቱ በግጭትና የጦርነት አውድ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ብልጽግና ጦርነትን መጥመቅና መጀመር የሚችለውን ያህል ጦርነትን አቁሞ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብቃትም ያለው ድርጅት አለመሆኑ በበቂ ሁኔታ ታይቷል፡፡

5ኛ/ Economic Performance/ የተደላደለና የተረጋጋ ኢኪኖሚያዊ አቅም መፍጠር አለመቻሉን የማህበረሰቡ የእለት ተዕለት ኑሮ ከሚናገረውም በላይ የአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ አገሪቱ ብድሯን መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰች መሆኗን ለአለም ያጋለቱት በአብይ አስተዳደር ነው፡፡ የአገሪቱ ሃብትና ገንዘብ በሁለት መንገድ ሲባክን ተስተውሏል፡፡ አንደናው ማቆሚያ የሌለው እና የአገሪቱን በጀት እንክት አድርጎ እየበላ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት በሁለት መልኩ የአገርን ሃብት ያቆረቁዛል፡፡ አንደኛው ጦርነቱን ለማካሄድ፣ ወድ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን እና ድሮኖችን ለመግዛት እና ለሰራዊቱ አቅርቦት ለማሟላት የሚወጣው በጀት በብዙ እጥፍ መጨመሩ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በጦርነቱ የሚወድሙ ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ መንደሮች፣ የግለሰቦች ሃብት እና የሚፈናቀለው ሕዝብ ብዛት ነው፡፡ ሌላኛው የአገሪቱ ሃብት ብክነት ደግሞ ከጦርነት የተረፈውን ገንዝብ ለቅንጡ ሪዞርቶች፣ ለመንግስት ቢሮዎች ማስዋቢያ፣ አዳዲስ ቤተመንግስቶች መገንቢያ እና የቱሪስት መዳረሻ ለሆኑ ግንባታዎች ማዋሉ ነው፡፡ ጦርነት ባለበት አገር ቱሪስት ምንስ ሊሰራ ይመጣል?

6ኛ/ Responsiveness and Long-term Vision / የለሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ምላሽ አለመስጠት እና የረዥም ጊዜ ግቦችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በጠቅላዩ ምኞትና ቅዠቶች ላይ ተመስርቶ መቅረጽ ሌላው አደጋ ነው፡፡ የአገዛዝ ሥርአቱ ሕዝብ ለሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ካቆመ እና ጆሮ ዳባ ልበስ ካለ ቆይቷል፡፡ መቼም የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይችለው ጉድ የለም እንጂ ዱሮ ነበር የአብይ ሥርአት በዚህ ዝንባሌው ብቻ በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ሊወገድ የሚገባው፡፡ ሌላው አሳዛኝ ነገር የአገሪቱ የቅርብም ሆነ የሩቅ ተስፋዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቀት፣ ፍላጎት፣ እና ቅዠት የመሰሉ እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው አገሪቱ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቷን ያሳያል፡፡ በየመድረኩ ብቅ እያሉ የዛሬ ሰላሳ፣ አርባ፣ አምሳ አመት ከአለም ሁለተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ አገር፣ የዛሬ 10 አመት የአፍሪካን ኢኮኖሚ በአንደኝነት ወዘተ የሚሉ የቅዠት ንግግሮችን መስማት እጅግ ያሳዝናል፣ ያሳስባልም፡፡

7ኛ/ Peace and Stability/ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን መፍጠር ያለመቻል ብቻ ሳይሆን ያለመፈለግም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ የመገለጫ ነው፡፡ አገሪቱ ከአንድ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት እንድታመራ እና የእርስ በርስ ጦርነቱ አልበቃ ቡሏቸው የአፍሪቃ ቀንድ ቀጠናን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተት እጅግ በተሳሳተ እና ጥናት ባልታከለበት የጭፍን ዲፕሎማሲ እና ሁሉንም የመዋጥ ምኞት ያለው የፖለቲካ እቅድ እየተመሩ አገሪቱ ብቻ ሳይሆን የአፍርካ ቀንድ ሰላም እና የተረጋጋ እንዳይሆን ብዙ እርቀት በመሄድ ኢትዮጵያን አጣብቂን ውስጥ ከተዋታል፡፡

8ኛ/ Effective control over territory and Sovereignty / የአገሪቱን ግዛቶች በበቂ ሁኔታ ማስጠበቅ እና ሉአላዊነቷን ማስከበር አለመቻላቸውም እንዲሁ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኤርትራን ጋብዘው በደ ትርግራይ በማስገባት ከማስወረርና የገዛ ሕዝባቸውን ከማስጨፍጨፍ አንስቶ ኢትዮጵያን የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አገር አድርገዋታል፡፡ የሱዳን ታጣቂዎችን ቤኒሻንጉል ጉምዝ ውስጥ አስገብቶ ማሰልጠን፣ አገሪቱን UAE የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እንደልቧ መሳሪያ የምታራግፍባት እና ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለውጪ ሃይሎች ወረራ የተጋለጠችበትን ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡

9ኛ/ Respect for human rights and Protection of minority groups/ ሰብአዊ መብቶችን በአግባቡ ማስጠበቅ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ሆነ ብሎ እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ መጣስ፣ ለህዳጣን ልዩ ጥበቃዎችን ማድረግ ሲገባው ለጥቃት እንዲጋለጡ ትርክቶችን ከማዛባት አንስቶ ጥላቻዎችን በማባዛት ዜጎች በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ታጣቂ ሃይሎች ኢላማ ተደርገው እንዲገደሉ፣ በገፍ እንዲሳደዱና እንዲፈናቀሉ፤ ከዛም አልፎ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታዎች እንዳይደሩስ በማድረግ ዜጎችን መቀጣጫ የሚያደርግ ሥርአት ፈጥረዋል፡፡

10ኛ/ Strong and effective election governance (Democratization process)/ ጠንካራ እና ብቃት ያለው የምርጫ ሥርአት በመዘርጋት ዜጎች በዲሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ማድረኛ መደላድሎችን መፍጠር ሲገባ ምርጫውን ለሥልጣናቸው መቀጠል እና የግፍ ሥርአቱን ለማጽኛነት በማዋል ኢትዮጵያ ውስጥ ታይተው የነበሩ የዲሞክራሲ ጭላንጭሎች እንዲዳፈኑና እንዲጠፉ አድርገዋል፡፡

አሁን የሚካሄደው 7ኛው አገር አቀፍ ምርጫም ግፍን እና አፈናን ከማጽኛነ የዘለለ ሚና እንዳይኖረው ተደጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ቀደም ብዮ በጻፍኳቸው ጽሁፎች ላይ ይህን ምርጫ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በማስቆም አገሪቱ ለቀውስ ጊዜ መፍትሄ የሚሰጥ የሽግግር መንግስት ሥርአት ውስት እንድትገባ ጥሪ ያደረኩትም በእነዚህ ምክንያቶች መሆኑን በመጠቆም እዚህ ላይ ላብቃ፡

በእነዚህ ነጥቦች ላይ የአገዛዝ ሥርአቱ የተሻለ ውጤት ሊሰጠው ይገባል የሚል ሰው ካለ እንዲሞግተኝ ጥሪ በማቅረብ ጽሑፌን ልዝጋ፡፡

መልካም ሰንበት!