Yidnekachew Kebede

♦በቃሊቲ ማ/ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞች በቂ ሕክምና ለማግኘት እንዳልቻሉ ተገለፀ ፤ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው በኩላሊት ሕመም የተነሳ በከፍተኛ ሕመም ላይ እንደምትገኝም ተሰምቷል።

ለእስረኞች የጤና አገልግሎት መስጠት ምንም እንም እንኳ የመንግስት ቀጥተኛ ኃላፊነት መሆኑ እና አድሎአዊ ድርጊት የተከለከለ ስለመሆኑ በሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ሕጎች የተገለፀ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(1) እስረኛ መሆን ማለት ሰብአዊ ክብርን የመነፈግ ማለት እንዳልሆነ በመግለጽ “በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎች በሙሉ እንዲሁም ጥፋተኛ ተብለው በቅጣት ላይ ያሉ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን በሚያከብር መንገድ የመታከም መብት አላቸው” ይደነግጋል።

የፌዴራል እስረኞች አያያዝ ደንብ ቁጥር 138/2007 ይህ ደንብ በ2007 የወጣ ሲሆን፣ እስረኞች በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በዜግነት ሳይድሉ እንዲታከሙ ያዛል ።

ይሁን እንጅ በተለይም በአማራነታቸው የተነሳ ወደተለያዩ የፌደራል ማ/ቤቶች ተወስደው የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞች ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እያገኙ አለመሆኑን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለፍ/ቤት አቤቱታዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል።

የጤና ባለሙያዎች ሳይቀር ክሊኒካዊ ነጻነታቸው እየተነጠቀ የሕክምና ውሳኔዎችን በህክምና ምክንያቶች ብቻ ከመወሰን ይልቅ በእስር ቤት አስተዳደር ሰራተኞች ፖለቲካዊ ጫና ሲቀለበሱ ይስተዋል።

የፍ/ቤት ትዕዛዝን በተገቢው ሁኔታ ባለመፈፀምም ጭምር ሕሙማን እንዳይታከሙ ማድረግ የተለመደ ሆኗል።

አንድ ተጠርጣሪም ሆነ የተፈረደበት ሰው መሰረታዊ የሆነ አለማቀፋዊ የሆነ ሕክምና የማግኘት መብቱን በመግፈፍ መቅጣት ትልቅ ኢሰብአዊ የሆነ ወንጀል ነው።

ይህን መሰረታዊ የሆነ ሕክምና የማግኘት መብት ከተነፈጉት መካከልም በቃሊቲ ማ/ቤት የሚገኙ በአማራነታቸው የተነሳ ያለፍትህ በግፍ እስር ላይ የሚገኙ ሴት የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞች ይገኙበታል።

ከእነዚህም መካከል ፦

1) ጋዜጠኛ መስከረም አበራ ፣

2) ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ፣

3) አለም በድሉ ፣

4) ሕይወት አለማየሁ እና

5) ሀሊማ መሀመድ

6) የዋስትና 150 ሽህ ብር ተጠይቃ ደጋፊ ባለማግኘቷ ለመክፈል ባልቻለችው መቅደስ አለሙ እና በሌሎችም ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እና በደል ተጠቃሽ ነው።

መንግስታዊ የሆነ የዘር ፍጅትና የጦር ወንጀል እየተፈፀመበት ስላለው የአማራ ሕዝብ ድምፅ በመሆኗ እንደ ወንጀል የተቆጠረባት መምህርትና ጋዜጠኛ መስከረም አበራ ለገጠማት ከፍተኛ የሆነ የዐይን ሕመም ከብዙ ጩኸት ፣ ልመና እና አቤቱታ በኋላ ሕክምና ለማግኘት መቻሏ ይታወቃል ፤ መጠነኛ መሻሻል ብታሳይም አሁንም በክትትል ላይ ትገኛለች።

በተመሳሳይ የግፍ እስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ከብዙ መዘግየት በኋላ የግል ሕክምና ማግኘቷ ተገልጧል ፤

ጋዜጠኛዋ ሁለት ኩላሊቷ መጎዳቱ በሀኪም ተረጋግጧል።

መጋቢት 10/2018 ወደ ቃሊቲ ማ/ቤት በመሄድ የግፍ እስረኞችን የጎበኘው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኽኝ እንደገለፀው የእስረኞቹ የጤና ሁኔታ አሳዛኝና አሳሳቢ ነው።

ጋዜጠኛ ገነት አስማማውም የኩላሊት ጠጠር ነው የተገኘባት።

ለመኝታ የሚሆን ደረቅ ፍራሽ እንዲገባላት ፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥላትም መጠየቁ ተገልጧል።

3) ሌላኛዋ የግፍ እስረኛ አለም በድሉም ሕክምና ለማግኘት በተደጋጋሚ ብታመለክትም የተሻለ ሕክምና እንድታገኝ አልተፈቀደላትም።

ዳኑ የአጥንት ሕክምና ሄዳ አስቸኳይ ሕክምና ማግኘት ባለመቻሏ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

4) ሕይወት አለማየሁ እና ሀሊማ መሀመድ በከፍተኛ ሕመም ላይ ይገኛሉ። ሁሉም ከሰብአዊነት አንጻር አስቸኳይና የተሻለ ሕክምና የማግኘት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ የሰብአዊ መብት እና የሚዲያ ተቋማት በቃሊቲ ማ/ቤት እና በችሎት እየተገኛችሁ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ተጠይቋል።

አቢይ አህመድ በሚመራው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ በአማራ ማንነታቸው ብቻ ከየ ስራ እና መኖሪያ ቤታቸው እየታፈኑ በተለያዩ የፌደራል ማ/ቤት ያለፍትህ እየተሰቃዩ የሚገኙ በትንሹ ከ300 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞች ከእነ ቤተሰቦቻቸው ሁለንተናዊ የሆነ ወገናዊ ድጋፍና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ግልጽ ነው።

© አውሎግሶን