ዕጩዎችና_አባላትን_አደጋ_ላይ_የጣሉ_ምርጫውን_አስቻይ_የማያደርጉ_ኹነቶች_በአስቸኳይ_ይፈቱ!
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ
በያዝነው 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን “7ኛ ዙር” አገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ኅዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የብልጽግና መንግሥት አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ፤ በየእስር ቤቱ ታጉረው የሚገኙ የፖለቲካና የማንነት እስረኞች እንዲፈቱ፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ ማነቆዎች እንዲወገዱ፤ ሚዲያው የገጠመው ከፍተኛ የገለልተኝነት ችግር እንዲከለስና ምርጫ ለማካሄድ በተለይ ከፀጥታ አንጻር አስቻይ ኹኔታዎች አለመኖራቸውን በዝርዝር እንደቅድመ ኹኔታ ሊሟሉ ይገባቸዋል ያልናቸውን አንኳር ጉዳዮች መግለጻችን ይታወሳል። በአንጻሩ እነዚኽ ያነሳናቸው መሠረታዊ የምርጫ ቅድመ ኹኔታዎች ስለመመለሳቸው መንግሥትና ታጣቂ ኃይሎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወይንም የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በምርጫ ቦርድ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቀናል።
ይኹን እንጂ ወደ ሥልጣን መንበር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ለአፍታ እንኳ ሰላማዊ መንገድን መከተል ያልፈለገውና ከታጣቂ ኃይሎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር ችግሮችን ለመፍታት ፍላጎት ያላሳየው መንግሥት ለጥያቄያችን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት አገር እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችበት ኹኔታ ወደምርጫ እየተንደረደረ ይገኛል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ዛሬም ለጀመረው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኝነቱን እየገለጸና የምርጫ ሂደቱንም ሕዝብ ጋር ለመድረስ፣ አማራጭ ፖሊሲዎችን ለማቅረብ፣ እንደአንድ የሰላማዊ ትግል አማራጭ ለመጠቀምና ሥርዓቱ ከስህተቱ ከተማረ የዴሞክራሲ ጎሕ ለመቅደድ እንዲያስችል ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ኾኖም ከዕጩዎቻችን፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከሚወጡ ይፋዊ መግለጫዎችና ነባራዊ ኹኔታዎች አኳያ በመረጃና ማስረጃ ተመርኩዘን በመተንተን በተለይ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አማራ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ ከፊል ኦሮሚያ(ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች) እና በቤኒሻንጉል ክልል- መተከል ዞን ባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የደህንነትና ለምርጫ አስቻይነት እጅግ አዳጋች መኾናቸውን ተረድተናል፡፡ ይኽንንም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡
በተለይ በአማራ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ማግስት ጀምሮ በትብብር ስንሠራ የነበርን ፓርቲዎች በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ጦርነቶችን በኃይል አማራጭ መፍታት እንደማይቻልና በገለልተኛ አደራዳሪዎችና በሦስተኛ አገር በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር መፍትሄ እንዲበጅ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ያለማቋረጥ ድምጻችንን ስናሰማ ቆይተናል። ይኹን እንጂ ጩኸታችን ሰሚ አጥቶ ዛሬ መላ ክልሉ የጦር አውድማ የኾነበት ኹኔታና ንጹሓን ዜጎቻችን ዕለት ዕለት በራሱ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ገንዘብ በሚገዛ ከባድ መሳሪያና ድሮን የሚጨፈጨፉበት ኹኔታ እጅግ ልብ ሰባሪ የታሪክ ክስተት ኾኖ ቀጥሏል።
በዚኽም ውስጥ ሆኖ የቀረቡት ቅድመ ኹኔታዎች በጎ ምላሽ አግኝተው እየተካሄደ ያለው ጦርነት በድርድር ሊፈታ ይችላል በሚል ተስፋ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጠበቀውን ያኽልም ባይኾን ዕጩዎችን አስመዝግቧል። ኾኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲኽ ዕጩዎችን እና ምርጫን ለማስተባበር የሚወጡ የመንግሥት አካላት ጭምር በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለከፍተኛ ሰቆቃና ሕልፈተ ሕይወት ጭምር መዳረጋቸውን መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡ እንደማሳያ በቅርኑ በታጣቂ.
ኃይሎች የወጣው መግለጫ፤ ያን ተከትሎ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ በአዘዞ ፀዳ ክ/ከተማ ባለፈው እሑድ መጋቢት 12 ቀን የኾነውና በመራጩ፣ በዕጩዎችና በአስተባባሪዎች ላይ ያደረሰው ፍርኃት፣ ሥነልቡናዊ ጫናና ተስፋ መቁረጥ በቂ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ያ ማለት የዕጩ ምዝገባ በተጠናቀቀበትና የምርጫ ቅስቀሳ በተጀመረበት በአኹኑ ወቅት የእያንዳንዱ የትብብሩ ዕጩ እንቅስቃሴ ከየትኛውም ወገን ሊቃጣበት ከሚችል የሕይወት አደጋ ላይ ነው፤ ያ እንዳይኾን መጠበቅ እንደሚገባ ደግሞ ትብብራችን በጽኑ ያምናል።
ስለኾነም አማራ ክልልን ጨምሮ በጠቀስናቸው አካባቢዎች የሚደረጉ ጦርነቶችና አጠቃላይ ለሕይወት አስጊ የፀጥታ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅላቸውና ጦርነቱ በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር እንዲቋጭ ለዚኽም መንግሥት ትልቁን ድርሻ እንዲወጣ በድጋሚ እናሳስባለን። ኹኔታዎቹ በአስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ተሰጥቷቸው የዕጩዎቻችን ደህንነት ዋስትና እስካላገኘ ድረስ በተጠቀሱ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ስለሚከብደን ይፋዊና የአደባባይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከማድረግ እንቆጠባለን፤ ቀጣይ እርምጃችንንም ለሕዝባችን በይፋ እንገልጻለን፡፡
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት- ለኢትዮጵያ
መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ


