
በኢራን እየተካሄደ ያለው ጦርነትና መዘዙን አስመልክቶት ትናንት ባቀረብኩት ጽሁፍ ላይ መነሻ የምላቸውን ሃሳቦች በማካተት በተለይ በሙያ፣ በእውቀትና በልምድ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው ምሁራንን ያካተተ ሀገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሙ በጥናት ላይ የተመሰረተ አማራጭ እንዲያቀርብ ጠቁሚ ነበር።
የጽሁፉ ዓለማ በጉዳዮ ላይ ወይይት መቀስቀስና ወደ ተግባር እንዲገባ ስለነበር ወይይት ተካሂዶበታል፣ መልካም ጅማሮ ነው። አሁንም ከችግሩ ጥልቀትና ተገማች አለመሆን አኳያ በተከታታይ በየመድረኩ ውይይት ቢደረግበት ፈተናውን በብቃት ለመሻገር ያግዛል የሚል እምነት አለኝ። ሶሻሊስቶች የነቃና የተደራጀ ሕዝብ ያሸንፋል እንዲሉ መንቃትና መደራጀት አለብን
ይህም ሆኖ ከጽሁፉ መነሻ ጋር ያልተሰናሰሉና (Out of context ) የሆኑ ኃሳቦች መከራከሪያ ሆነው ቀርበው ስለነበር በጥቅሉ ሐሳቤን ፈርጅ ማስያዝ አስፈላጊ ስለሆነ፣ እንደገና ተመልሽያለሁ።
ዛሬ ላይ በተለይ የገጠመን ፈተና ለዘመናት ቀይዶ የያዘን የምርታማነት ችግርና ነዳጅ ላይ የነበረው ተቋማዊ ውጥንቅጥና ሙስና ብቻ ሳይሆን መቋጫው መቼ እንደሆነ ያልታወቀ ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ አቅርቦት ፈተና ነው።
ይህ ደግሞ ድሮም አለ ሊባል የማይችለውን የትራንስፖርት ስርዓታችንን ይበልጥ እያዛባው ነው። እንኳን አዲስ ምርት ጨምረን ለማጓጓዝ እስከ አሁን የተመረተውን ምርት ከቦታው ለማንሳት እያዳገተን ነው።
አልፎ ተርፎም በትራንስፖርት ችግር የተጫነ ምርት ሲበሰብስና ሲደፋም እያየነ ነው። ከውጭ የምናስገባውን ምርትን አስመልክቶም ትኩረታችን ለኑሮ ወሳኝ የሆኑት ላይ ካላተኮረና እንደተለመደው ማግበስበሳችንን ከቀጠልን ሸቀጡን ከወደብ ማነሳት ባለመቻላችን የሚገጥመን ውጥቅጥና ፈተና ቀላል አይሆንም።
ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደማይችል በቂ ምልክት መታየቱ ብቻ አይደለም ጦርነቱ ቢጠናቀቅ እንኳ የተዛባው የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ስርዓት ወደ ቦታው እስኪመለስ ድረስ ጊዜ ይፈልጋል። ኢትዮጵያም የተለየ ትኩረት አግኝታ ችግሩን ለመቅረፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚችሉ ሃገራት ተርታ ስላልሆነች ችግሩ ቢፈታ እንኳን ውጤቱ በፍጥነት እኛ ጋር ለመድረስ ያለው እድል ጠባብ ነው።
ስለዚህ ያለንን ውስን የምርት አቅርቦትና የዝውውር ስርዓት ራሳ ገዝ/ራስን ቻይ (Self Sufficient) ና ቁጠባና እንደ አስፈላጊነቱ ቁጥጥርና ክትትል (Auster ) የታካለበት ማድረግ አለብን። እንዴት ?!
1) ያለን አቅርቦት ውስን ነው። ያንኑንም ውስን ምርት ወደ ገበያ ለማምጣት እየተቸገርን ነው። ስለዚህ አጠቃቀማችን ላይ ማሻሻያ ማድረግ አለብን።
2) ይህንን ክፍተት እንደ እድል በመቁጠር ምርት በመደበቅና ጥራት በማጎደል የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከማስተማር ጋር ጥብቅ ክትትልና ቆንጣጭ ሕጋዊ ቅጣት ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (ሕዝብን ተገን አድርጎ)
3) በተለይ መንግስት ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ያለውን በሰበብ አስባቡ ከቀበሌ አጥቢያው ጀምሮ የሚያደርገውን ድግስና ብክነት ማቆም አለበት። ( የተሽከርካሪ ዓይነት፣ የነዳጅ ፍጆታ፣ ብዛትና አጠቃቀም ጨምሮ)
4) በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለመቀነስና ለመወሰን ሰራተኛን እረፍት በመስጠት ስራ እንዳይበደል ደግሞ የስራ ሰዓትን ማራዘምና ደርቦ ማሰራትን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
5) ቁጠባ ብክነትን መከላከል ለወቅታዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ባህል መሆን የሚገባው ነገር ነው። ቁጥጥር ግን ወቅታዊ መፍትሔ ነው። ዞሮ ዞሮ “ሁሉም ገዢ ሻጭ ነው። ሁሉም ሻጭ ገዢ ነው በሚል መርህ ላይ ተመስርተህ ሕዝብን ካስተባበርክና በዓለማው ካመነበት የማይቻል ነገር የለም።
6) ይህ አካሄድ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተሻለው አማራጭ ነው እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይደለም።
7)ዘላቂ መፍትሔው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በማጥፋትና ሙስናን በቆራጥነት በመታገል፣ መንግስት ለኢንቨስትመን መዋል የሚገባውን ሐብት መቀራመትና መሻማትን በማቆም፣ ትኩረቱን እሴት ፈጣሪ በሆኑ ዘርፎች ላይ በማድረግ በተለይም ደግሞ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ወዘተ ነው።
