ልደቱ አያሌው-3ኛ መንገድ

መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም

ግልጽ ደብዳቤ

‘——————-

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

ጉዳዩ፦ የተሳትፎ ጥያቄን ይመለከታል

//////////////////////////////////////////////////////

በበርካታ ድርጅቶች እና ተዋቂ ግለሰቦች የተቋቋመው የትዕይንተ-ህዝቦችና ሰላማዊ ሰልፎች አዘጋጅ ግብረ-ሃይል የወቅቱን የብልጽግና አገዛዝ የጦረኝነት ፖሊሲ የሚቃወም ታላቅ የበይነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ እያዘጋጀ ነው።

ይህ የበይነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ የሚካሄደው ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ከአመሻሹ 12 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፣ መሪ ቃሉም— “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን! ግፋዊ አገዛዝ ያብቃ! ከምርጫ በፊት ሽግግር ይኑር!!” የሚል ነው።

ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የበይነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ ኢትዮዽያውያን የብሄር፣ የኃይማኖትና የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ሳያግዳቸው ለጋራ ህልውናቸው በጋራ የሚታደሙበት ታላቅ የፖለቲካ መድረክ ነው።

በዚህ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ ላይ በወቅቱ የአገራችን ፖለቲካ ወይም የሲቪክ እንቅስቃሴ የጐላ የተጽዕኖ

ፈጣሪነት ሚናና ማህበራዊ መሰረት አላቸው ተብሎ የታመነባቸው 20 ተዋቂ ሰዎች ተገኝተው በብዙ

ሚሊዬኖች ለሚቆጠር ታዳሚ ንግግር ያደርጋሉ።

በሚያደርጉት ንግግርም- “በአገራችን እንዴት ጦርነት ሊቆም፣ ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን፣ አገዛዝነት ሊያበቃና

ሁሉን-አቀፍ የሆነ ሽግግር ሊካሄድ እንደሚችል ያላቸውን የግል ወይም የድርጅት የፖለቲካ አቋም ይገልጻሉ።

ይህ መድረክ በዋናነት የተዘጋጀው በእርሰዎ እየተመራ ያለው የብልጽግና መንግስት በሚያራምደው የጦረኝነት

ፖሊሲ ምክኒያት የአገሪቱና የህዝቧ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ለመቃዎም ነው።

ነገር ግን በእርሰዎ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ ፖለቲካ የራሴ የሚለው ማህበራዊ መሰረት ያለውና የአገሪቱን የወደፊት ህልውና በመወሰን እረገድም የራሱ ሚና እንዳለው በመገንዘብ እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል ቢጋበዝና በመድረኩ ላይ ቢገኝ ተገቢ ነው ብሎ ግብረ-ሃይላችን አምኗል።

ግብረ-ሃይላችን ባልተለመደ ሁኔታ በራሱ የተቃውሞ መድረክ ላይ የአገዛዙ ቁንጮ መሪ የሆኑትን ሰው ለመጋበዝ የወሰነውም እርሰዎ ከጦርነት ውጭ ሌላ የመፍትሄ አማራጭ የማይታየዎትና ለእንዲህ ዓይነቱ ሰላማዊ የህዝብ መድረክም አክብሮት እንደሌለዎት ሳይገነዘብ ቀርቶ ሳይሆን የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘው የወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ በሀቀኛ ድርድርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በኛ በኩል ያለንን ልባዊ ፍላጐት ለኢትዮዽያ ህዝብና ለዓለም-አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳዬት በማሰብ ነው።

ስለሆነም ፍላጐቱ ካለዎት ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በበይነ-መረብ መድረኩ ላይ ተገኝተው እየቀረበበዎት ባለው የተቃውሞ ሀሳብ ላይ ያለዎትን አቋም ለህዝብ እንዲገልጹ በአክብሮት ተጋብዘዋል።

ሁኔታዎችን በአግባቡ ለማመቻቸት ይረዳን ዘንድም ከትዕይንተ-ህዝቡ ከሶስት ቀናት በፊት በዚህ ደብዳቤ

ግርጌ ላይ በተቀመጠው የኢ-ሜል አድራሻ ለመገኘት ፈቃደኛ መሆንዎን አስቀድመው እንዲያሳውቁን

በአክብሮት እንጠይቃለን።

ከምስጋና ጋር

የትዕይንተ-ህዝቦችና ሰላማዊ ሰልፎች አዘጋጅ ግብረ-ሃይል

ስንተባበር እናሸንፋለን!!

ye.abronet2016@gmail.com