
ልደቱ አያሌው-3ኛ መንገድ ·Follow
ከሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ድጋፍ ሰጪዎች የጋራ መድረክ (የጋራ መድረክ)
የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
የነገው የበይነ-መረብ ትዕይንተ-ህዝብ የህዝቡን ትግል ወደ ላቀ ምዕራፍ
የሚያሸጋግር ታሪካዊ መድረክ ነው!!
በጋራ መድረካችን ያዘጋጀነውና በርካታ የአገራችን የፖለቲካ ተዋናኞች፣ የሲቪክ ማህበራት መረዎችና የሃይማኖት አባቶች ንግግር የሚያደርጉበት ታላቅና ታሪካዊ የበይነ-መረብ ትዕይንተ-ህዝብ ነገ ቅዳሜ መጋቢት 26 (April 4)) በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰዓት (11:00 AM Washington, DC Time) ይካሄዳል።
የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝቡ በአገራችን ኢትዮጵያ “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን! የግፍ አገዛዝ ያብቃ!
ከምርጫ በፊት ሁሉን-አቀፍ ሽግግር ይቅደም”! የሚሉ መሪ ቃሎች አንግቦ የሚካሄድ ነው።
ይህንን የሕዝባችንን የትግል እንቅስቃሴ ወደ አንድ የላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ትዕይንተ-ህዝብ በአገር
ውስጥና በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በየአሉበት ሆነው እንዲከታተሉትና የሂደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ የጋራ መድረካችን አገራዊ ጥሪውን በአክብሮት ያቀርባል።
ላለፉት 8 የመከራ ዓመታት በዐቢይ አህመድ የሚመራው አምባገነናዊ አገዛዝ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። ከአንድ ሚሊዬን በላይ የሆነ ህዝብ በጦርነት አልቋል፣ በብዙ መቶ ሺዎች
የሚቆጠር ህዝብ አካል ጉዳተኛ ሆኗል፣ ከአራት ሚሊዬን በላይ የሆነ ህዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየእስር ቤት ታጉረዋል፤ የጦርነት ተሳታፊ ያልሆኑ ንፁሃን ዜጐች በድሮንና በመድፍ በግፍ ተጨፍጭፈዋል፤
ብዙዎች አገራቸዉን እየጣሉ ለመሰደድ ተገደዋል፣ ከሰባት ሚሊዬን በላይ የሆኑ የወደፊት አገር ተረካቢ ልጆች
ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል፣ ሌሎች ሚሊዬኖች በኑሮ ውድነት ከመሰቃየትም በላይ የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ነዳያን ሆነዋል፣ በአጠቃላይ ኢትዮዽያና ኢትዮዽያዊያን በአለፈ ታሪካቸን አይተነው በማናውቀው
መጠን እንደ አገርና ህዝብ መቀጠል የማንችልበት ከባድ የህልውና ፈተና ውስጥ ወድቀናል።
ይህ ሁሉ እየሆነ በሚገኝበት አገርና በዓለም ዙሪያ ያሉ የውጭ አገራት ጭምር ዜጐቻቸው ወደ አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ደፍረው እንዳይሄዱ እያስጠነቀቁ ባለበት በአሁኑ ወቅት አገዛዙ የመንግሥት ሥልጣኑን
ለማቆየትና በውጭው ዓለም ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ በዜጐቻችን ላይ ሌላ ተጨማሪ ጫናና ማዋከብ በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ እራሱ የአገዛዙ የምርጫ ቦርድ ምርጫዉን ለማካሄድ በአገሪቱ ክልሎች ዙሪያ አደረግሁት ባለው ጥናት መሠረት በትግራይ ሙሉ በሙሉና ግማሽ በሚሆነው የአማራ ክልል የፖለቲካ ቅስቀሳም ሆነ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል አስታዉቋል፡፡
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የተለያዩ መለኪያዎችም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኝበት ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ነው። በ“ፍሪደም ሀዉስ”
መለኪያዎች ከመቶ አሥራ ስምንት (18/100)፤
“በኢንተርኔት ነጻነት” ከመቶ ሰላሳ (30/100)፣ በ2025 “የዓለም የፍትሕ ፕሮጀችት”
መለኪያ መሰረት በሕግ የበላይነት ከ143 አገራት 132ኛ፤ በአጠቃላይ ኢትዮዽያ የፍትሕና የሲቪክ ነጻነት፤ እንዲሁም መሠረታዊ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣች አገር ሆናለች።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ በተመለከተም የአገራችን ችግር
ይበልጥ አሳሳቢ ሆኗል። በዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት ሪፖርት መሰረት ከ 4 ሚልዬን በላይ የሚሆኑ እናቶችና ህጻናት በአስቸኳይ የህይዎት አድን ምግብ ያስፈልጋቸዋል። በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካላገኙ እስከ ሶስት ሚልዬን የሚደርሱ ዜጐች ለህይወታቸው አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢትዮዽያ በጦርነትና በግፍ አገዛዝ ስር ሆና መቀጠል ሳይሆን ከዚህ ሁሉ የህልውና አደጋ የሚታደጋት ዴሞክራሲያዊና ሁሉን-አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት የሚያስፈልጋት መሆኑን ነው፡፡ አገዛዙ ግን እንደተለመደው
“ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ በራሱ የጥፋት መንገድ መጓዝን ቀጥሏል።
በተቃራኒው እኛ የአገሪቱን እውነተኛ ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም የማሳወቅ ግዴታ አለብን። በዚህ ዓይነት
ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ባለች አገር ነጻና ፍትሃዊ የሆነና አገሪቱን ለማረጋጋት የሚያስችል ምርጫ ሊካሄድ እንደማይችል በመገንዘብ የኢትዮዽያ ህዝብና ዓለም-አቀፉ ህብረተሰብ የምርጫውን ሂደት እውቅና እንዲነፍጉት አጥብቀን እንታገላለን። ይህ ሰላምን ማስፈን ያቃተውና የሕግ የበላይነትን የማያከብር አገዛዝ በምርጫ ስም የስልጣን እድሜን በህገ ወጥ መንገድ ለማስቀጠል እየጣረ መሆኑን ተገንዝበው በአገዛዙ ላይ ቢያንስ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት ቅድመ-ሁኔታዎች በተግባር ለማሟላት የሚያስችል
ተጽእኖና ግፊት ሊያደርጉበት ይገባል እንላለን።
የዓለም-አቀፋ ህብረተሰቡ ጫና አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው መፍትሄ ከራሳችን የትግል ጥንካሬ
የሚመነጭ በመሆኑ ለህልውናችን መቀጠል አስተማማኝ መድህን የሚሆነውን የሽግግር ጥያቄ አገዛዙ በህዝብ
ትግል ተገዶ እንዲቀበል የሚያስችል የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኛነት ትግልን የማነሳሳትና የማጠናከር ስራ አጠናክረን እናካሂዳለን።
ኢትዮጵያዊያን በፍርሀትና በግድ ሳይሆን ሰብአዊ ክብራቸውን ሳይገፈፉ በገዛ ፍቃዳቸው በሰላም የሚሳተፉበት ነጻና ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ይናፍቃሉ። እንዲህ ዓይነቱ ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው
ግን በቅድሚያ ከተጋረጠባቸው የህልውና አደጋ ተርፈው እንደ አገርና ህዝብ መቀጠል ሲችሉ ብቻ ነው።
በነገው እለት የሚካሄደው የበይነ-መረብ ትዕይንተ-ህዝብ የኢትዮዽያን የትግል መንፈስ የሚያነቃቃ፣ አገዛዙ ህዝባዊ ማዕበል አፍጥጦ እየመጣበት መሆኑን የሚያስጠነቅቅ፣ ዓለም-አቀፋ ህብረተሰብ አገዛዙ በህዝብ ዘንድ
ምን ያህል የተጠላ መሆኑን እንዲገነዘበው ከማድረግም በላይ ትግላችንን ወደ አንድ ከፍተኛ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያበቃን ታሪካዊ ሁነት ነው። በቀጣይ መሬት ላይ በተጨባጭ ልናካሂዳቸው ላሰብነው የህዝባዊ
እምቢተኛነት ትግል ዋነኛ የመስፈንጠሪያ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለን ስለሆነ እራሱንና አገሩን ከህልውና ጥፋት ማዳን የሚሻ ማንኛውም ኢትዮዽያዊ በየአለበት ሆኖ ትዕይንተ-ህዝቡን በእጅ ስልኩ ወይም
በቴሌቪዥን በቀጥታ በመከታተል እንዲሳተፍ አገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ልዩነታችን ውበት፣ አንድነታችን ኃይል ነው!
ስንተባበር እናሸንፋለን!!
አዘጋጅ: የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ድጋፍ ሰጪዎች የጋራ መድረክ (የጋራ
መድረክ)
መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም



