
4 ሚያዚያ 2026, 08:02 EAT
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ
የአሜሪካ ወታደሮች ከመሬት በታች የተከማቸውን የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመቻ የማካሄዳቸው ነገር የማይሆን ነገር ቢመስልም አንደኛው አማራጭ ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ ውስጥ ዋና ዓላማቸው የሆነውን የቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸግን ለመግታት አንደኛው አማራጭ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ ዘመቻ እጅግ ፈታኝ እና በአደጋ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የገለጹ ወታደራዊ ባለሙያዎች እና የቀድሞ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራት እንደሚያስፈልግ እና ንጥረ ነገሩን አንቀሳቅሶ ለማጠናቀቅም በርካታ ቀናትን ወይም ሳምንታትን ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።
የዩራኒየም ክምችትን ማስወገድ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ውስብስብ ከሆኑ ተግባራት አንዱ ነው” ሲሉ በአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ማይክ ሙልሮይ ገልጸዋል።
ይህ እርምጃም ትራምፕ በኢራን ውስጥ ሊወስዷቸው ከሚችሏቸው በርካታ ወታደራዊ አማራጮች መካከል አንዱ ነው።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ እንድትከፍት ጫና ለማድረግ አሜሪካ የኻርግ ደሴትን ልትቆጣጠር መቻሏ ሌላኛው አማራጭ ነው። ኢራንን ወደ ክብ ጠረጴዛ ለማምጣት አዳዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በመጠቀምም ሊያስገድዱ ይችላሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ሳያስወግዱ ወይም ሳያጠፉ በጦርነቱ ማሸነፋቸውን ማወጅ ይቻል እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ከለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
