መልዕክተ ቅዳሜ፤
በመብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃ/ማርያም
የሽግግር መንግስት ጥያቄ ላስደነበራችሁ፤ ልሂቃን እና የብልጽግና መንደር ሰዎች
++++
ዛሬ ቅዳሜ ወደ ማምሻው ላይ የሚካሄደውና ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቅቱ፤ ጥቂቶች ደግሞ በስጋት፣ በጥርጣሬ እና በፍርሃት እየራዱ የሚመለከቱት የሰላም ሰላም ይስፈን፣ የጦርነት ይቁም፣ ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት ይቋቋም፣ የግፍ አገዛዝ ያብቃ በሚል የተዘጋጀው የበይነ መረብ ትዕይንተ ሕዝብ በአገዛዝ ሥርአቱ መንደር ሽብር እንደፈጠረ ከሰሞኑ ግርግር ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከአገዛዙ ካድሬዎች፣ ተከፋይ የሶሻል ሚዲያ ተንታኞች እና በምሁርነት ሽፋን ለአገዛዝ ሥርአቱ ድፋፍ ከሚሰጡ ጥቂት ልሂቃን ጩኸት እና ዘለፋ አዘል ዛቻዎችና ትችቶች ድምጽ ውስጥ ጎልቶ የወጣው እንዴት ብልጽግናችን እያለ የሽግግር መንግስት ትላላችሁ? እንዴት ምርጫ እየተካሄደ ባለበት አገር በሽግግር መንግስት ስም ሥልጣን ለመያዝ ትሞክራላችሁ፣ የሚሉ እና በእኔ ላይ ደግሞ በግል የሚቀርቡት ክሶች እንዴት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆነህ ከፖለቲካ ሃይሎች ጋር ቆመህ ስለ ሽግግር መንግስት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ጦርነት እና ስለ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ታወራለህ የሚሉ ናቸው፡፡ ለጊዜው ከእኔ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ለሌላ ቀን ላቆየው እና ስለ ሽግግር መንግስት ጥያቄው እና በአገዛዙ መንደር ለምን መሸበርን እንደፈጠረ ልግለጽ፡፡
የሽግግር መንግስት አስፈላጊነትና ባህሪውን ምን እንደሚመስል አውቀው ከሚያደናግሩት ሰዎች ውጪ በቅን ልቦና፣ ባለማወቅ እና ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ቀጣይ እጣ ፈንታ ከመስጋት በመነጨ ስሜት ጥያቄውን በጥርጣሬ ወይም ሳይገባቸው በተቃውሞ ላስተናገዱት ሰዎች ትንሽ ማብራሪያ ለመስጠት ወደድኩ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የግድ የሚለው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ ሰላም በሰፈነበት፣ የዜጎች መብትና ነጻነት በሚከበርበት፣ ግጭቶች በሕግ አግባብና በውይይቶች ብቻ በሚፈቱበት፣ ጤናማ የፖለቲካ ምህዳር፣ የተረጋጋ መንግስታዊ ሥርአት ባለበት፣ ፍትህ በሰፈነበት አገር ሁሉ መንግስታዊ የሥልጣን ሽግግር በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ስለሚካሄድ የሽግግር ጥያቄ በምንም አግባብ ሊነሳ አይችልም፡፡
የሽግግር ጥያቄ የሚነሳው በአገሪቱ ውስጥ Stability and Order/ መረጋጋት እና ሥርአት ሲጠፋና በምትኩ ሥርአት አልበኝነት ሲነግስና የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ ከመጥፎ ሥርአት የሚሸጋገር አገር ከሆነ አዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ለመተግበርና አዲስ ፍኖተ ካርታ ለመዘርጋት፣ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ የመብት ጥሰቶችን፣ ሙስና እና ዝርፊያዎችን እልባት እንዲያገኙና ተጎጂዎችን ያማከለ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ ፍትህ እንዲሰፍን እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ነው፡፡ የዛሬ 8 አመት የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥያቄ ስናቀርብ አብይ እኔ አሻግራችኋለው ብሎ ያስመለጠን አንድ ትልቅ እድል ነው፡፡ ካለፈው ምርጫ በፊትም ይሄን ጥያቄ ደጋግሜ አነሳ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅትም “አሻጋሪውን የሚያሻግር የሽግግር መንግስት ያስፈልገናል” የሚል ሃሳብ የያዘ ጥያቄዮን አቅርቤ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬየምትገኝበት ሁኔታ አንድ በችግር ውስጥ ያለና ችግሮቹን በሽግግር መንግስት እንዲፈታ ከሚመከር አገር በብዙ መልኩ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ነች፡፡ ይሄንን ለማስረዳት ጊዜ ማባከን አለብኝ ብዮ አላስብም፡፡ ብዙ ተብሎበታል፣ ብዙ ተጽፎበታል፣ ሕዝቡም የሚገኝበትን ሁኔታ ከሁለት ቀን በፊት በመላው የአማራ ክልል በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ሳይቀር በሚገባ ተገልጿል፡፡
የእኔ ትኩረት የሽግግር መንግስት የሚለውን ሃሳብ ሆን ተብሎ መንግስትን በአንድ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ቡድን የመቀየር ጥያቄ ተደርጎ በተሳሳተ መልኩ የሚቀርበውን አገላለጽ ለማጥራት ነው፡፡ የሽግግር መንግስት እንዲሁ በደመ ነፍስ አራት ኪሎ የከተመውን የብልጽግናን መንግስት በሌላ አምባገነን ወይም የሥልጣን ተራ ጠባቂ ፓርቲ ማስያዝ አይደለም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ መርሆዎች፣ መስፈርቶች እና መገለጫዎች ያሉት ነው፡፡ እነሱም፤
1ኛ/ Provisional Nature (Temporality)፤ የሽግግር መንግስት ሁሌም የሚቋቋመው እጅግ ለአጭር ጊዜ ብቻ ሲሆን ዋነኛ አላማውም በግጭት ወስጥ ወይም ከግጭት እየወጣች ያለችን አገር ማረጋጋት እና እውነተኛ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ መደላድል መፍጠር ነው፡፡ ጊዜውም እንደ የአገሩ ሁኔታ ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ተኩል ሊወስድ ይችላል፡፡
2ኛ/ Non-Constitutional Rupture: በሕገ መንግስቱ ሳይሆን የሽግግር ሂደቱ በሚመራበት ቻርተር የሚተዳደር ነው፡፡ አገሮቹ ብዙውን ጊዜ ከቀውስ፣ ከመፈንቅለ መንግስት፣ በእርስ በርስ ጦርነት ወይም ሥርነቀል የመንግስት ለውጥ ማግስት ወይም ተከትሎ የሚመጣ ስለሆነ በሕገ መንግስት የሚመራ አይደለም፡፡
3ኛ/ Legal & Constitutional Transformation: ሥልጣኑ በሽግግር ቻርተር ወይም ሕግ የተገደበ እና አላማውም አገሪቱ ተረጋግታ፣ አዲስ ሕገ መንግስት ቀርጻ ወይም ያለውን ሕገ መንግስት አሻሽላ ወደ ተረጋጋና በምርጫ የሚሰየም መንግስት እስኪመጣ ድረስ የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖርና አገሪቱን ለበለጠ ትርምስ እንዳይዳርግ አሸጋጋሪ የሆነ ነው፡፡
4ኛ/ Domestic Ownership፤ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ልሂቃን የሚዘወርና የውጭ ጣልቃ ገብነት ከፋይናንስ ድጋፍና ምክር የዘለለ እንዳይሆን ያደረገ መሆን አለበት፡፡
5ኛ/ All inclusive፡ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ የሽግግር መንግስት ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሥልጣን የሚወዳደሩበት ወይም አንድ ፓርቲ ሥልጣን የሚይዝበት አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ የሲቪም ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሁራን እና ግለሰቦች፣ የታጠቁ ሃይሎችን እና በሌሎችም አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ አካላትን ሁሉ ያሳተፈ ሂደትና መዋቅር ነው፡፡
6ኛ/ Accountability, Justice and reconciliation፤ የወንጀል ተጠያቂነትን፣ ለጉዳተኞች ፍትህን የሚሰጥ እና በጥላቻ የሚተያዩና በተቃርኖ ይኖሩ የነበሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ቅራኔዎቻቸውን በውይይትና በእርቅ እንዲፈቱ መደላድሎችን የሚፈጥር ነው፡፡
የአገዛዝ ሥርአቶች ሁሌም ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ ስለሚታገሉ የሽግግር መንግስት ጥያቄዎችን አጥብቀው ቢፈሩ የሚገርም ሊሆን አይችልም፡፡ የሚያስደምመውና የሚያሳዝነው የሽግግር መንግስት ጥያቄን ሆን ብለው የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠት ሕዝቡ ለውጥን እንዲፈራ እና የግፍና ጭካኔ የተሞላው ሥርአትን አሜን ብሎ ተቀብሎ እየተገዛ፣ እየተገፋ፣ እየታሰረ፣ እየተዋከበ፣ እየተገደለና እየታፈነ እንዲኖር የሚመክሩ ልሂቃን መኖራቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለአንድ አገር የሽግግር መንግስት የሚያስፈልግበትን ቀይ መስመር ካለፈች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ሌላውን ቀይ መስመር ልትሻገር ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ይሄኛው ቀይ መስመር እንደ አገር ግዛቷ ተጠብቆና የሕዝቧም አንድነት ተከብሮ ልትኖር የማትችልበትን ሁኔታ የሚያስከትል ለመሆኑ ብዙ ማመላከቻዎችን ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ቶሎ ካልተገታ ኢትዮጵያ የሶማሌን፣ የየመንን፣ የኢራቅና እንደ ሶሪያ ሌሎች የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባቸው አገሮችን ትቀላቀላለች፡፡
ለዚህም ነው ከ7ኛው አገራዊ ምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት ያስፈልጋታል የሚል የጸና አቋም ይዤ የምከራከረውና ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገው በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ በአንድነት በመቆም ለሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ከተሰለፉ ሃይሎች ጋር አብሬ የምቆመው፡፡ ገና የዛሬ 7 አመት ከሽግግር መንግስት ውጪ ኢትዮጵያ ሌላ መዳኛ አላት ብዮ እንዳላስብም ያደረገኝ የአገዛዝ ሥርአቱ ባህሪ ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ እጅግ ተባብሶና ወደ ከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ባለፉት ጽሑፎቼ ደጋግሜ ስላነሳሁ ለመድገም አልፈልግም፡፡
ይህ የሽግግር መንግስት ሃሳብ ቢሳካ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ በስቃይ ውስጥ ያለው ሕዝቧ እና የአገዛዝ ሥርአቱም ጭምር ብዙ ያተርፉበታል፡፡ ማንንም የማያክሰ፣ አገርን ከገባችበት አዘቅት የሚያወጣና የሚታደግ፣ ሰላም ለማውረድ፣ ጦርነት ለማቆምና የተዳፈነው የዲሞክራሲ ምህዳር ዳግም እንዲያብብና እንዲፈካ ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡
ሰላም ይስፈን!
ጦርነት ያብቃ1
የግፍ አገዛዝ ይብቃ!
ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት ይቋቋም
0:25 / 1:28
