ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች በ አል አቅሳ ሆስፒታል ተቃቅፈው ሐዘናቸውን ሲገልጹ
የምስሉ መግለጫ,ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች በ አል አቅሳ ሆስፒታል ተቃቅፈው ሐዘናቸውን ሲገልጹ

ከ 9 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በማዕከላዊ ጋዛ በእስራኤል የአየር ድብደባ እንዲሁም በሐማስ እና በእስራኤል በሚደገፈው የፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 10 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ጥቃቶቹ ከማጋዚ የስደተኞች ካምፕ በስተምስራቅ ከሚገኙት የሚሊሻ አባላት ጋር የተጋጩትን የሐማስ የደህንነት ሠራተኞችን ዒላማ እንዳደረጉ ተዘግቧል።

ከሠራተኞቹ መካከል ስንት ሰዎች በጥቃቶቹ ምክንያት ወይንም በውጊያው መካከል እንደሞቱ ግልጽ አይደለም።

በዴር አል-ባላህ የሚገኘው የአል አቅሳ ሆስፒታል ቃል አቀባይ እንዳሉት በጥቃቱ እና በግጭቱ የተገደሉ የ10 ሰዎች አስከሬን ወደ ሆስፒታላቸው መጥቷል።

በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና አንዳንዶቹ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል።

ከእስራኤል ጦርም ሆነ ከሐማስ ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም።

ሰኞ ዕለት ታጣቂዎቹን ወደ ግጭት ያስገባውም ሆነ ለአየር ድብደባው ምክንያት የሆነው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ የዓይን እማኞች እንዳሉት በእስራኤል የሚደገፉት ታጣቂዎች ከማጋዚ በስተምስራቅ የሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ ሲያቋቁሙ ከሐማስ የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን ይህም ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል።