
ኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ መርከቦች እንዲያልፉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ። ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ማክሰኞ ሌሊት ድረስ ማትከፍት ከሆነ “ዛሬ ማታ ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” የሚል ዛቻ ካሰሙ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ጭምቅ ሃሳብ
- አሜሪካ እና ኢራን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ
- አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ
- የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስንም ያካትታል?
- የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጦርነቱ “ድል ማድረጓን” ገለጸች
- የእስራኤል ጦር ኢራንን ማጥቃት ማቆሙን፣ የሊባኖስ ዘመቻውን ግን እንደሚቀጥል ገለጸ
- አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች
- በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ ዓለም በስጋት የሚጠብቃቸው ቀጣይ ሰዓታት
- የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 13 ሺህ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች
- ኢራን ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት” እንደተፈፀመባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን ገለፀ
የቀጥታ ሽፋን
- ከ 55 ደቂቃዎች በፊትየእስራኤል ጦር ኢራንን ማጥቃት ማቆሙን፣ የሊባኖስ ዘመቻውን ግን እንደሚቀጥል ገለጸ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየእስራኤል ጦር ዛሬ ጠዋት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ፈጸመ። ይህ ጥቃት እስራኤል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስ ውስጥ ተግባራዊ እንደማታደርግ የሚጠቁም ሆኗል።የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ኢራን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማቆሙን፤ ሊባኖስ ውስጥ የሚያካሂደውን ዘመቻ ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል።በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ትይሬ እና ናባቲህ አካባቢዎች ረቡዕ ጠዋት ጥቃት የተፈጸመባቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፤ የተኩስ አቁሙ በኢራን ከሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የሚካሄደውን ግጭትም ያካትታል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።የሊባኖስ መንግሥት እና ሄዝቦላህ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም። ስምምነቱን ያሸማገለችው ፓኪስታን በበኩሏ ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጻለች።ባለፉት ቀናት ኢራን በምታደርገው ድርድር ውስጥ በሊባኖስ የሚደረገውን ግጭትም እንድታካትት ሄዝቦላህ መጠየቁ ተዘግቦ ነበር።የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ “ኢራን ውስጥ የሚፈጽመውን ተከታታይ ጥቃት ማጠናቀቁን” ገልጿል። ከፖለቲካዊ አመራሩ “በደረው መመሪያ መሠረት” ኢራንን ማጥቃቱን እንዳቆመም አክሏል።እስራኤል ላይ ለሚፈጸም “ማንኛውንም ጥሰት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን” ጠቅሷል።ሊባኖስ እና ሄዝቦላህን በተመለከተ ግን “የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዒላማ ያለውን የምድር ዘመቻ ማከናወኑን ይቀጥላል” ብሏል።እስራኤል በበኩሏ የሊባኖስ ግዛትን ተቆጣጥራ የመቆየት እንዲሁም ድንበሩ ውስጥ የደኅንነት ዞን የማቋቋም ዕቅድ እንዳላት ገልጻለች።የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስን የወረሩ ሲሆን ይህ እርምጃቸው የአገሪቱን ክፍሎች ተወርረው እንደተያዙ እንዲቀሩ ያደርጋል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። እስራኤል ወርራ በምትቆየው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን እንደምታፈርስ እና ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።ያጋሩ, የእስራኤል ጦር ኢራንን ማጥቃት ማቆሙን፣ የሊባኖስ ዘመቻውን ግን እንደሚቀጥል ገለጸ - ከ 1 ሰአት በፊትየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጦርነቱ “ድል ማድረጓን” ገለጸች
የፎቶው ባለመብት,Reutersዋሽንግተን እና ቴህራን የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት አማካሪ ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ በተከታታይ የኢራን ጥቃቶችን ያስተናገደችው አገራቸው “ድል ማድረጓን” ተናገሩ።አማካሪው አንዋር ጋርጋሽ “ሉዓላዊነትን እና ክብርን እንዲሁም ክህደት በተሞላበት ጥቃት ፊት ስኬቶቻችን ባስጠበቀ ድንቅ ብሔራዊ መከላከያ ድል አድርገናል” ብለዋል።ኤምሬቶች ዛሬ ላይ “የገዘፈ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም፣ የሰላ ዕይታ እንዲሁም በወደፊቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና ለመቅረጽ የሚያስችል ይበልጥ ጠንካራ አቅም” እንዳላት አማካሪው ጠቅሰናል። ይህንንም ተጠቅመን “ውስብስብ የሆነውን ቀጣናዊ ሁኔታ ለመምራት ወደፊት እንጓዛለን” ብለዋል።የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ያከሸፋቸውን የኢራን ጥቃቶችን በተመለከተ በየጊዜው መደበኛው መረጃ ሲያወጣ ቆይቷል።ማክሰኞ ዕለት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ 2,221 ድሮን፣ 26 የክሩዝ ሚሳዔል እና 520 ባሊስቲክ ሚሳዔል ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተተኩሷል።የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን በበጎ ተቀብሎታል።ፓኪስታን ለማሸማገል ላከናወነችውን ሥራ ዕውቅና የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ፤ ወደ ቋሚ ተኩስ አቁም ለመድረስ ወደፊት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ “ጥረቶችን ማጠናከር” አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል።ያጋሩ, የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጦርነቱ “ድል ማድረጓን” ገለጸች - ከ 2 ሰአት በፊትየተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስንም ያካትታል?
የፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለችአሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ የሊባኖስ መካተት እና አለመካተት አካራካሪ ጉዳይ ሆኖ ወጥቷል።ኢራን እንዲሁም የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ያሸማገሉት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹህባዝ ሻሪፍ ስምምነቱ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጸዋል።በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የኢራን ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿ ጭምር ወደ ሊባኖስ አሰማርታለች።ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ግን የተደረሰው የተኩስ አቁም “ሊባኖስን አያካትትም” ብሏል።ነገር ግን በተኩስ አቁሙ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ጉዳዮች የበለጠ መብራራት ያስፈልጋቸዋል።ባለፉት ሳምንታት ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ እግረኛ ወታደሮቿን ያሰማራችው እስራኤል፣ ከሄዝቦላህ በኩል የሚመጣ ማንኛውም ዓይነት ስጋት እስኪወገድ ድረስ ወታደሮቿ ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ እንደሚቆዩ አስታውቃለች።እስራኤል በአካባቢው የሄዝቦላህ አባላት ይንቀሳቀሳሉ በማለት ቤቶች እና መንደሮችን በማፍረሷ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ከአካባቢው ሄዝቦላህ እስኪወገድ ድረስ ነዋሪዎቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እንደማይፈቀድላቸውም አስታውቃለች።በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም መደረሱ ከመገለጹ ቀደም ብሎ በደቡባዊ ሊባኖስ ሲዶን ከተማ ውስጥ በተፈጸመ የእስራኤል ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን እና 22 መቁሰላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ቀጥሏል።ያጋሩ, የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስንም ያካትታል? - ከ 4 ሰአት በፊትአሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesአሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚያደርግ የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳየ።ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋን ለመለካት ጥቅም ላይ የሚውለው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ በርሜል ዋጋ በ13 በመቶ ገደማ ቀንሶ 94.80 ዶላር ገብቷል። በአሜሪካ የሚሸጠው ነዳጅ ደግሞ የ15 በመቶ ቅናሽ በማሳየት ዋጋው 96.75 ዶላር ደርሷል።አሁንም ቢሆን ግን የነዳጅ ዋጋ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ሲሸጥ ከነበረበት በበርሜል 70 ዶላር ገደማ ዋና የጨመረ ሆኖ ቀጥሏል።በአሜሪካ እና ኢራን ጥቃት ተከፈተባት ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ከዛተች በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦች የተስተጓጎለ፣ ሲሆን የኤነርጂ ዋጋም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።ወሽመጡ መዘጋቱን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ ባሕር ላይ የቆዩ በርካታ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአሁኑ ስምምነት እንዲያልፉ እንደሚፈቀድላቸው ይጠበቃል። የመርከቦቹ ማለፍ ለዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።ያጋሩ, አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ - ከ 5 ሰአት በፊትአሜሪካ እና ኢራን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ነዋሪዎች የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋልኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ መርከቦች እንዲያልፉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ።ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ማክሰኞ ሌሊት ድረስ ማትከፍት ከሆነ “ዛሬ ማታ ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” የሚል ዛቻ ካሰሙ ከሰዓታት በኋላ ነው።አገራቱን ሲያሸማግሉ የነበሩት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የተኩስ አቁሙ ወዲያውኑ ገቢራዊ መሆን እንደሚጀምር አስታውቀዋል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ቴህራን ከባሕረ ሰላጤው የሚወጡ የነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የምትከፍት ከሆነ “ሁለት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ድብደባ እና ጥቃት ለማቆም” መስማማታቸውን ገልጸዋል።ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በዚህ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም የተስማሙት “ሁሉንም ወታደራዊ ግብ ስላሳኩ እና ከዚያም በላይ” ስላገኙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ኢራን ከወታደራዊ ኃይሏ ጋር በመቀናጀት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ትፈቅዳለች።ኢራን በበኩሏ 10 ነጥቦች ያሉት እቅድ ይፋ አድርጋለች። በእቅዱ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና የመን ውስጥም ጥቃቶች መቆም አለባቸው የሚል ነው።ኢራን ላይ የተጣሉ ማእቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲኖር ማድረግ፣ በአሜሪካ የተያዙ የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶችን መልቀቅ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ የደረሰው ውድመት “መልሶ የሚገነባበትን ወጪ የሚሸፍን ሙሉ የካሳ ክፍያ” መፈጸሙም በእቅዱ ውስጥ ተጠቅሰዋል።የአገሪቱ መንግሥት፤ “ኢራን ማንኛውም የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት ላለመፈለግ ሙሉ ቁርጠኛ ይሆናል” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ይህ ”የኢራን ድል በፖለቲካዊ ድርድር ላይም ይጸናል” ብሏል።የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ፤ የተኩስ አቁሙ እስራኤል በኢራን የሚደገፈውን ሄዝቦላህ ላይ ዘመቻ ከፍቻለሁ ባለችበት ሊባኖስ ውስጥም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በሄዝቦላህ የተጋረጠው ስጋት እስከሚወገድ ድረስ ከሊባኖስ እንደማይወጡ ተናግረዋል።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ የተኩስ አቁሙ ይፋ ከተደረገ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ “ኢራን በአፋጣኝ ሆርሙዝ ወሽመጥን የምትከፍት እንዲሁም አሜሪካ፣ እስራኤል እና ሌሎች የቀጣናው አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የምታቆም መሆኗን ተከትሎ የሚሰነዘርባት ጥቃት ለሁለት ሳምንት እንዲቆም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያስተላለፉትን ውሳኔ እስራኤል ትደግፋለች” ብለዋል።የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አክሎም “የተኩስ አቁሙ ሊባኖስን አያካትትም” ሲሉ እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿን ባሰማራችባት ጎረቤት አገር ተፈጻሚ እንደማይሆን ገልጿል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የተኩስ አቁም ለማድረግ ውሳኔ ባሳለፉበት ሂደት ውስጥ እስራኤል ምን ያህል ተሳትፎ እንደነበራት ግልጽ አይደለም።ያጋሩ, አሜሪካ እና ኢራን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ - 7 ሚያዚያ 2026በሆርሙዝ ላይ ለተመድ የቀረበው ውሳኔ በሩሲያ እና በቻይና ውድቅ ሆነ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ድምጽ በሰጡበት ጊዜለሆርሙዝ ወሽመጥ በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግ በባሕረ ሰላጤው አገራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሩሲያ እና በቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ውድቅ ሆነ።ከምክር ቤቱ አባለት አስራ አንዱ የውሳኔ ሃሳቡን ሲደግፉ፣ ፓኪስታን እና ኮሎምቢያ ድምጻቸውን አቅበዋል፤ ሩሲያ እና ቻይና ስለተቃወሙት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።የውሳኔ ሃሳቡ ረቂቅ ላይ ለሳምንታት ድርድር ሲደረግ ቆይቶ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ወታደራዊ ኃይል መጠቀምን የሚፈቅደው ክፍል እንዲቀር ተደርጎ አገራት የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ በሚል ተለውጦ ነበር።የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስሰብባን የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አብዱላጢፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ በሰብሳቢነት መሩት ነበር።ሰብሳቢው ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት የውሳኔ ሃሳቡ አዲስ ሁኔታን የሚፈረር ሳይሆን፣ በሆርሙዝ ላይ ኢራን የፈጠረችውን ተደጋጋሚ ችግር ለማስቆም አስፈላጊ በመሆኑ የቀረበ ነው ሲሉ አስረድተው ነበር።የውሳኔ ሃሳቡ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ መስመሮችን በመሳሪያነት መጠቀምን በማበረታታት ከሆርሙዝ ባሻገር በሌሎችም ቦታዎች እንዲደገም በማድረግ ዓለምን ወደ ሕግ አልነባት ያሸጋግራታል ብለዋል።ውሳኔውን ድምጽን በድምጽ በመሻር ውድቅ ያደረጉት ቻይና እና ሩሲያ በሆርሙዝ መዘጋት እምብዛም ችግር እንዳልገጠማቸው ሲዘገብ ቆይቷል።ቻይና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦቻቸው ያለችግር መተላለፍ ከቻሉ አገራት መከካል እንዷ ስትሆን፣ ሩሲያ ደግሞ ተጥሎባት የነበረው የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት ላልቶላታል።ያጋሩ, በሆርሙዝ ላይ ለተመድ የቀረበው ውሳኔ በሩሲያ እና በቻይና ውድቅ ሆነ - 7 ሚያዚያ 2026ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአገራቸው የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እየቀረበባቸው ነው
የፎቶው ባለመብት,Reutersፕሬዳንት ትራምፕ ኢራን ከተቀመጠላት የጊዜ ገደብን በፊት ስምምነት ላይ ካልሰደረች “ሥልጣኔዋ በአንድ ሌሊት ያከትማል” ማለታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።በተለይ የትራምፕ ፓርቲ ተቀናቃኝ የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴዎች በቶሎ መፍትሄ እንዲፈለግ እየጠየቁ ነው።በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር “ይህ ግለሰብ በጣሙን የታመመ ሰው ነው። ይህንን የግድየለሽነት ጦርነት ለመቃወም ፈቃደኛ ያልሆኑ እያንዳንዳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ለትኛውም ዓይነት አስከፊ ዳፋ ኃላፊነት አለባቸው” ሲሉ ሪፐብሊካንን ወቅሰዋል።የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪው ሐኪን ጄፍሪስ በበኩላቸው “ዶናልድ ትራምፕ በግዴለሽነት የገባበት የኢራን ጦርነት ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሳያስገባን በፊት ምክር ቤቱ ማስቆም አለበት። ይህንን እብደት በማስቆም በኩል ሁሉም ሪፐብሊካኖች ብሔራዊ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።የምክር ቤት አባሉ ጄሰን ክሮው ደግሞ የአንድን አገር “ሥልጣኔን ለማጥፋት መዛት የጦር ወንጀል ነው። በተደጋጋሚ እንዳልኩት ጦር ሠራዊታችን ሕጋዊ ትዕዛዞችን ብቻ ነው መከተል ያለበት። መልካም ህሊና ያላቸው ሁሉም አሜሪካውያን ይህንን ድርጊት መቃወም አለባቸው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።ሌላኛው የምክር ቤት አባል ጂም ማክጋቨርን “ይህ የለየለት ክፋት ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የጦር ወንጀል ለመፈጸም የሚሰነዝረው የዘር ማጥፋት ዛቻ በፌደራል እና በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ነው” በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር ነቅፈዋል።ያጋሩ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአገራቸው የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እየቀረበባቸው ነው - 7 ሚያዚያ 2026ትራምፕ አስካሁን ምን ያህል ጊዜ ለኢራን የጊዜ ገደብ አስቀመጡ?
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የኢራኑ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።ጦርነቱ በጀመረ በመጀመሪያው ሳምንት ኢራን እጅ የማትሰጥ ከሆነ ከባድ ውድመት እንደሚደርስባት በመገልጽ ፕሬዝዳንቱ ከማስጠንቀቅ አልፈው ከስድስት ሳምንት በኋላ የኢራንን ሥልጣኔ በአንድ ሌሊት ዶግ ዓመት እንደሚያደርጉት እየዛቱ ነው።ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያወጧቸው ማስጠንቀቂያዎች እና የጊዜ ገደቦች እየተራዘሙ አሁን ዛሬ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሚጠናቀቀው የመጨረሻው የኢራን መሪዎች ያላቸው ዕድል መሆኑን አስጠንቅቀዋል።ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምን ያህል ጊዜ ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብን አስቀመጡ?- መጀመሪያ፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም. ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች “ከትልቁ ጀምሮ ያሏት የኃይል ማመንጫዎች ፍረስርሳቸው ይወጣል” ብለው ዝተው ነበር።
- ሁለተኛው፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ከኢራን ጋር “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ንግግር’ መደረጉን በመግለጽ የጥቃቱን ቀነ ገደብ በአምስት ቀናት አራዘሙት።
- ሦስተኛው፡ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም. ደግሞ “በኢራን መንግሥት ጥያቄ መሠረት” የኃይል መሠረተ ልማቶችን የማጥቃት ቀነ ገደባቸውን በ10 ቀናት ማራዘማቸውን ሰኞ መጋቢት 28ን የመጨረሻው ቀን አደረጉት።
- የ48 ሰዓታት ማስጠንቀቂያ፡ የሰኞው ቀነ ገደብ በተቃረበበት ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ “መአት” ከማዝነቸባው በፊት “48 ሰዓታት” እንደቀሩ አስጠንቅቀው ነበር።
- ባለፈው ዕሁድ፡ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሰዓታት ውስጥ የማይከፈት ከነሆ ኢራን ‘ሲኦል” እንደምትሆን ዝተዋል።
- የማክሰኞው ማስጠንቀቂያ፡ ዛሬ ማክሰኞ አስከ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ኢራን የቀረበላትን የድርድር ሃሳብ የማትቀበ ከሆነ “ሥልጣኔዋ ተመልሶ እንዳይመጣ ሆኖ ይሞታል” ሲሉ ዝተዋል።
- 7 ሚያዚያ 2026ስለ ነዳጅ ልናውቃቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮችኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ተከትሎ ዋነኛው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ነዳጅ ምርት መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል።በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የነዳጅ አቅርቦት የቀነሰ ሲሆን፣ ዋጋውም ጭምሯል።ለመሆኑ ነዳጅ ስንል ምን ማለታችን ነው? ኢትዮጵያ ከየትኞቹ አገራት ነው ነዳጅ የምታገኘው? በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ እንዴት ይወሰናል?ብሬንት ነዳጅ የሚባለው ምንድን ነው? የትኞቹ አገራት ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት አላቸው? ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ቁልፍ ጉዳዮችን ከስር ካሉት ሰሌዳዎች ላይ ይመልከቱ።https://flo.uri.sh/visualisation/28331727/embed?auto=1ያጋሩ, ስለ ነዳጅ ልናውቃቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች
- 7 ሚያዚያ 2026ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” – ፕሬዝዳንት ትራምፕ
የፎቶው ባለመብት,EPAኢራን የቀረበላትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ “ሙሉ ስልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ይሞታል” ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቁ።የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሌሊት የሚጠናቀቀውን ለኢራን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ባለፉት ቀናት ሲሰጡ የነበረውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን አጠናክረው ደግመውታል።ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባሰፈሩት መልዕክት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት ያበቃለታል” ሲሉ በኢራን ላይ ዝተዋል።ትራምፕ ጨምረውም:”ያ እንዲሆን አልፈልግም፣ ነገር ግን ሳይከሰት አይቀርም። ቢሆንም ግን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ እና አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ አለ፤ የተለዩ ብልህ እና ብዙም ጽንፈኛ ያልሆኑ የበላይነትን ይይዛሉ፤ ምናልባትም የሚያስደንቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ ማን ያውቃል?” በማለት ጽሁፋቸው ላይ የጠየቁት ትራምፕ ዛሬ ሌሊት ሊከሰት የሚችለውን አመልክተዋል።”በዓለም ረጅም እና ውስብስብ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነውን ነገር ዛሬ ማታ የምናየው ይሆናል። የ47 ዓመታት ጭቆና፣ ሙስና እና ሞት በመጨረሻም ያበቃል። እግዚአብሔር ታላቁን የኢራን ሕዝብ ይባርክ!”ትራም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ሃሳብን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ያበቃል።ኢራን የተኩስ አቁም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት እና የሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላትን በመጠየቅ የራሷን ቅድመ ሁኔታዎች አቅርባለች።በሌላ በኩል ደግሞ በፓኪስታን መሪነት ዲፕማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ በቀሩት ሰዓታት አንዳች ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ለስድስት ሳምንታት የተካሄደው ጦርነት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።ያጋሩ, ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” – ፕሬዝዳንት ትራምፕ - 7 ሚያዚያ 2026የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ ፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሳዑዲ አረቢያን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካዎችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ከፍተኛ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።በጥቃቱ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአሜሪካ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ በመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች እና በአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች “የተሳካ ጥቃት” መፈጸሙን አመለክቷል።ዘቡ እንዳለው ከተቋማቱ በተጨማሪ “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጥቅሞች እና ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላት” ዒላማ መሆናቸውን ገልጿል።በመግለጫው ላይ ኢራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ሰኞ ዕለት “በአሳሉዬህ የፔትሮኬሚካል ማዕከል” ላይ የተፈጸመባትን ጥቃት ለመበቀል መሆኑ ተጠቅሷል።አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ “ቀይ መስመራችንን የምታልፍ ከሆነ ምላሻችን ከመካከለኛው ምሥራቅም የሚያልፍ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቋል።አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ እና አጋሮቿ ኢራን ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች ውስን ሆነው ቆይተው” የነበረ መሆኑን ገልጿል።ይህ ለመልካም ጉርብትና ሲባል ኢራን አሳይታው የነበረው “ቁጥብነት” ዒላማዎችን እንድትለይ አድርጓት መቆየቱን፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ “ይህ ቁጥብነት እንደማይኖር” በመጥቀስ አስፈላጊ በተባሉ ዒላማዎች ላይ “ያለማወላወል” እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።ያጋሩ, የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ ፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ - 7 ሚያዚያ 2026በቱርክ ኢስታንቡል የእስራኤል ቆንስላ አካባቢ “ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው” ተገደሉ
የፎቶው ባለመብት,Reutersበቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።በተኩሱ ሁለት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።መገናኛ ብዙኃኑ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች “እርምጃ ተወስዶባቸዋል’ ያሉ ሲሆን ቢያንስ ሁለቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።የቱርክ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በፖሊስ ጋር ተኩስ የከፈቱት ሦስት ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።የኢስታንቡል አስተዳዳሪ ከአጥቂዎቹ ውስጥ አንዱ መገደሉን እና ሁለቱ ላይ ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ለሲኤንኤን ተርክ ተናግረዋል።”በፖሊስ ኃይላችን ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ሁለቱ ፖሊሶቻችን ቆስለዋል። ከአሸባሪዎች ውስጥ አንዱ ተገድሏል። ሁለቱ ደግሞ በተወሰደባቸው እርምጃ ቆስለዋል” ያሉት ገዢው ጥቃቱ ትልቅ ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አነስተኛ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።በቱርክ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የእስራኤል ዲፕሎማት አለመኖሩን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።የእስራኤል ኤምባሲ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኝ ሲሆን በኢስታንቡል ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ነው።የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር በቆንስላው አካባቢ ስለተከፈተው ተኩስ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።በርካታ የፖሊስ አባላት በቆንስላው አካባቢ ታይተዋል። ቆንስላው የሚገኘው በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል ሰሜናዊ ክፍል ነው።ጥቃቱ የተፈጸመው በቀጣናው እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ውጥረቶች በተባባሱበት ወቅት ነው።ያጋሩ, በቱርክ ኢስታንቡል የእስራኤል ቆንስላ አካባቢ “ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው” ተገደሉ - 7 ሚያዚያ 2026አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች
የፎቶው ባለመብት,Social mediaእንደ አሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እና የምሥል ትንተናዎች ከሆነ አሜሪካ እስካሁን ድረስ በጦርነቱ ቢያንስ ዘጠኝ አውሮፕላኖችን አጥታለች።መጋቢት 27 2018 ዓ.ም.- ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄትን ለማገዝ የተጓዙ ሁለት የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ከኢራን መነሳት አልቻሉም። አውሮፕላኖቹ በጠላት እጅ እንዳይወድቁ በሚል እንዲወድሙ መደረጉ ተዘግቧል። የተረጋገጡ ምሥሎች አውሮፕላኖቹ በማዕከላዊ ኢራን እንደወደሙ አሳይተዋል። ቢቢሲ ቨሪፋይ የአውሮፕላኖቹን ዓይነት ለመለየት ባለሙያዎችን ጠይቋል።መጋቢት 25- በማዕከላዊ ኢራን ተዋጊ ጄት ተመትቶ ወድቋል። ባለሙያዎች ከስብርባሪው ባገኙት መረጃ ተመትቶ የወደቀው ጄት “ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኤግል” የተባለው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት መሆኑን ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ቀን ኒዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤ-10” የተባለ ጄት በባሕረ ሰላጤው ተከስክሷል። አብራሪው ቀድሞ ተመንጥቆ በመውጣት ሊተርፍ ችሏል።መጋቢት 20- ማረጋገጥ የቻልነው ምሥል “ኢ-13” የተባለ አውሮፕላን የኢራንን ጥቃት ተከትሎ በሳዑዲ አረቢያ ልዑል ሱልጣን አየር ጣቢያ ለሁለት መከፈሉን ያሳያል።መጋቢት 3- “ኬሲ-135” የተባለ የነዳጅ መሙያ አውሮፕላን በምዕራብ ኢራቅ ተከስክሶ ስድስት ወታደሮች ሕይወታቸው ማለፉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) አስታውቋል። ክስተቱ እየተመረመረ ቢሆንም ኮማንዱ በጠላት አሊያም በወዳጅ አገራት ተኩስ አለመውደቁን ግን ጠቁሟል።የካቲት 23- ሦስት የአሜሪካ “ኤፍ-15ኢ” ጄቶች ሴንትኮም “በወዳጅ አገራት ያልተጠበቀ ክስተት” ሲል በገለፀው ሁነት በኩዌት ወድቀዋል። ስድስቱም አባላት አስቀድመው መውጣት መቻላቸውንም አክሏል። ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተንቀሳቃሽ ምሥል ማረጋገጥ እንደቻለው ጄቶቹ በኩዌት ከተማ ምዕራባዊ ክፍል ወደ መሬት ሲሽከረከሩ ነበር።ያጋሩ, አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች - 7 ሚያዚያ 2026በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ ዓለም በስጋት የሚጠብቃቸው ቀጣይ ሰዓታት
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ አውዳሚ ጥቃት ይፈጸማልበማለት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።አሜሪካ እና እስራኤል በአንድ በኩል ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘው ጥቃታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ ኢራንም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ አገራት ላይ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ካልተከበረ ኢራንን “ወደ ድንጋይ ዘመን” ይመልሳታል ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ሰዓት እየተቆጠሩ ናቸው።ይህ የኢራንን የሲቪል የኃይል ማመንጫ ተቋማትን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደርጋል የተባው የትራምፕ ዛቻ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ “የጦር ወንጀል ነው” በማለት ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።ይህ ሁሉ የጥቃት እና የውድመት ዜና እየተሰማ ባለበት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው። በፓኪስታን መሪነት የሚደረገው ጥረት ወደ ወሳኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።ፓኪስታን ጦርነቱን ለማብቃት በአሸማጋይነት “አዎንታዊ እና ውጤታማ ጥረት” እያደረገች መሆኑን በኢስላማባድ የኢራን አምባሳደር ጠቅሰው በሂደቱም “ወሳኝ እና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ደረጃ ላይ እየተደረሰ” መሆኑን ተናግረዋል።ቀደም ሲል አሜሪካ በአስቸኳይ ከተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣላችው ዕቀባ ካነሳች በኋላ ቀጣይ የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ ሃሳብ ብታቀርብም፤ ኢራን ግን የራሷን የድርድር ሃሳብ በመቅረብ ውድቅ አድርጋዋለች።ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት የተከፈተባት ጦርነት በዘላቂነት እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና በጥቃቱ ለደረሰባት ውድመት የመልሶ ግንባታ ሃሳብን አቅርባለች።እየተካሄዱ ያሉት ንግግሮች በፍጥነት ተቋጭተው በቀጣይ ሰዓታት ውስጥ ከስምምነት ካልደረሰ አሜሪካ ባላት ኃይል ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ እርምጃ እንደምትወስድ፣ ኢራንም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ አጸፋ እንደምትመልስ እየዛቱ ነው።ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ያሉት መጪዎቹ ሰዓታት ለኢራን ብቻ ሳይሆን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ብሎም ለመላው ዓለም መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች የሚተላለፉበት ሊሆኑ ይችላሉ።መላው ዓለምም ምን ሊከሰት እንደሚችል በስጋት እና በጉጉት እየጠበቀ ነው።ያጋሩ, በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ ዓለም በስጋት የሚጠብቃቸው ቀጣይ ሰዓታት - 7 ሚያዚያ 2026የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 13 ሺህ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች
የፎቶው ባለመብት,US CENTCOMእስራኤል በኢራን ተጨማሪ ጥቃቶችን መፈፀሟን ሪፖርት ካደረገች በኋላ የአሜሪካ ጦር ጦርነቱ ከተጀመረ ከየካቲት 21 ወዲህ 13 ሺህ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል።አሜሪካ በኢራን እያካሄደች ባለችው እና “ኤፒክ ፉዩሪ” ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ዘመቻ ከ155 በላይ የኢራን መርከቦችን መውደማቸውን አሊያም መጎዳታቸውንም አስታውቃለች።የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) ከደበደባቸው ዒላማዎች መካከል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና መስሪያ ቤት፣ የአየር መቃወሚያ ስርዓት፣ የባላስቲክ ሚሳኤል ጣቢያዎች እና የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ሰርጓጅ መርከቦች ይገኙበታል ብሏል።ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ዜና ወኪል የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,665 ንፁሃንን ጨምሮ 3,500 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።ያጋሩ, የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 13 ሺህ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች - 7 ሚያዚያ 2026ኢራን ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት” እንደተፈፀመባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን ገለፀ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየእስራኤል-አሜሪካ ጦርነት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,600 የሚሆኑ ንፁኃንን ጨምሮ 3,500 የሚሆኑ ሰዎች በአገሪቱ እንደተገደሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የዜና ወኪል (ሀራና) አስታውቋል።ትናንት ሠኞ ብቻ 59 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 58 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን በምሽት ዳሰሳው ገልጿል።ያለፉት 24 ሰዓታት “ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ከተፈፀሙት ጥቃቶች ከፍተኛ መጠን ነው” ብሏል።ሠኞ ዕለት በቴህራን የሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርስቲ፣ በመኖሪያ ሕንፃ እና በኬሚካል ፋብሪካ ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ትላልቅ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።ቡድኑ በመስክ ሪፖርት፣ ከአካባቢው ምንጮች፣ ከሕክምና እና ድንገተኛ አደጋ ምንጮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረቶች እንዲሁም ከፎቶግራፎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ከመንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫዎች በመጭመቅ አሃዛዊ መረጃውን እንደሚያጠናክር ገልጿል።ያጋሩ, ኢራን ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት” እንደተፈፀመባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን ገለፀ - 7 ሚያዚያ 2026የፀጥታው ምክር ቤት በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን ለመጠበቅ ድምፅ ሊሰጥ ነው
የፎቶው ባለመብት,EPAየመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢራን ለአብዛኛው መርከቦች የተዘጋውን ቁልፍ የባሕረ ሰላጤው መተላለፊያ ለማስከፈት ድምፅ ይሰጣል።የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በሆነቸው ባሕሬን የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት ቀርቦ የነበረ እና ወደዚህ ሳምንት የተላለፈ ነው።የውሳኔ ሀሳቡ ይዘት መጀመሪያ ከቀረበ በኋላ ማሻሻያ እንደተደረገበት ታውቋል።በመጀመሪያው ረቂቅ አባል አገራት “ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እና ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃዎችን እንዲወስዱ “ይፈቅዳል።”አዲሱ ማሻሻያ ደግሞ ደኅንነት የተሞላበት ጉዞ ለማድረግ “ጥረቶችን ማቀናጀት፣ ተፈጥሯዊ መከላከል፣ ከሁኔታው ጋር የሚመጣጠን እርምጃ” “በጥብቅ እንደሚያበረታታ” ይጠቅሳል።ያጋሩ, የፀጥታው ምክር ቤት በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን ለመጠበቅ ድምፅ ሊሰጥ ነው - 7 ሚያዚያ 2026የእስራኤል ጦር ኢራናውያን ዛሬ ባቡር እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየእስራኤል ጦር በይፋዊ የማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ በፋርስ ቋንቋ ባሰፈረው መልዕክት በኢራን የሚኖሩ ሰዎች “ለደህንነታችሁ” በማለት ”በባቡር ከመጓዝ ተቆጠቡ” ብሏል።ማስጠንቀቂያው በመላው አገሪቱ ለሚኖሩ ኢራናውያን መሆኑን የገለጸው ጦሩ በኢራን ሰዓት አቆጣጠር “እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት” ድረስ ማስጠንቀቂያው እንደሚቆይ ገልጿል።አክሎም “በባቡር ውስጥ መሆን አና በባር ሃዲዶች አቅራቢያ መገኘት ሕይወታችሁን አደጋ ላይ ይጥለዋል” ብሏል።የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ኢራን የሚገኘው የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛታቸውን ተከትሎ ነው።ሠኞ ምሽት የእስራኤል ጦር ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ያላቸውን “የቴህራን መሠረተ ልማቶችን” ዒላማ በማድረግ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀሙን እና የሄዝቦላህ አባላትን መግደሉንም ገልጿል።ከዚህ ውጭም የእስራኤል ጦር ከኢራን ወደ እስራኤል የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን መቀልበሱን አስታውቋል።ያጋሩ, የእስራኤል ጦር ኢራናውያን ዛሬ ባቡር እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀ - 7 ሚያዚያ 2026የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ቡድን በኢራን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ነው ሲል አስጠነቀቀ
የፎቶው ባለመብት,vahidonlineየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ጥቃቶች በመላው ኢራን እየተፈጸሙ በመሆናቸው ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታወቀ።እአአ ከመጋቢት 17 እስከ ሚያዚያ 3 ባለው ጊዜ ውስጥ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ ገበያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች እና የባህል ቅርስ ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲል ቡድኑ ገልጿል።ኦቻ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጋቢት 30 ድረስ ከ2,100 በላይ ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን፣ ከ27,900 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ 3.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጦርነቱ እንደጎዳቸው አስታውቋል።እናም ከጦርነቱ መጀመሪያ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ሳምንታት ከ115,000 በላይ የሰላማዊ ሰዎች መገልገያዎች ተጎድተዋል ሲል አክሎ ተናግሯል።ኦቻ በተጨማሪም “ወሳኝ በሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና የኢንዱስትሪ መንደሮች ላይ የተካሄደው ጥቃት የመብራት፣ የውሃ እና የቴሌኮሙኒኬሽንን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስተጓጎሉ ፈጣን እና ረዥም ጊዜ የሚቆይ የአካባቢ እና የጤና አደጋዎችን አስከትሏል” ብሏል።ያጋሩ, የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ቡድን በኢራን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ነው ሲል አስጠነቀቀ - 7 ሚያዚያ 2026በኩዌት ሌሊቱን በተፈጸመ ጥቃት አሜሪካውያን ተጎዱኢራን በኩዌት አሊ አለ ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት 15 አሜሪካውያን ጉዳት እንደረሰባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ተናገሩ።አንድ ባለሥልጣን አብዛኛዎቹ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 373 የአሜሪካ ጦር አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል።ከእነዚህ መካከል 330ዎቹ ወደ ሥራቸው ሲመለሱ አምስቱ ግን ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ለሲቢኤስ ተናግሯል።ያጋሩ, በኩዌት ሌሊቱን በተፈጸመ ጥቃት አሜሪካውያን ተጎዱ
