ነፃ አስተያየት

April 1, 2026

Updated: April 3, 2026

ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group

ማስተካከያ ፡ ቀደም ሲል በዚህ ጽሁፍ ላይ የተጠቀምነው ፎቶግራፍ የተሳሳተ በመሆኑ ይቅርታ እየጠየቅን ጽሃፊዎቹ ካላይ ያያዝነው ፎቶግራፍ እንዲሆን ስለጠየቁ በዛ መሰረት ተስተካክሏል፡፡

ከቀድሞ 4ኛ ክ/ጦር የፖለቲካ እስረኞች 
አብዱልለጢፍ አባስ፣ አስተዋይ መርዕድ፣ ብርሃኑ ደኑ፣ ደረጀ ዓለማየሁ፣ ኤፍሬም ዳኜ፣ ፍቃዱ ሽፈራው፣ ግርማ ዓለማየሁ፣ ኃይለሥላሴ ወልደገሪማ፣ መላኩ በቀለ፣ መስፍን አየለ፣ ሲሳይ ታከለ፣ ተካልኝ መሃሪ፣   የራስወርቅ አድማሴ፣ ዘካሪያስ ኃይሉ፣ ዘላለም በንቲ

አማረ ተግባሩ፣ ከውልደቱ ጀምሮ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥና በመኢሶን ውስጥ ስለነበረው ተሳትፎ የሚተርክ  “ከአዲስ አበቤነት እስከ ሉላዊነት” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ አቅርቧል። ከዚያ ቀደም ሲልም ከኃይሌ ፊዳ ጋር በነበረው “ቅርበት” ላይ የሚያተኩር “ኃይሌ ፊዳና የግል ትዝታዬ” የሚል መፅሐፍ አሳትሟል። 

በነዚህ ፅሑፎች ራሱን ለማሞገስ እየፈጠረና እያጋነነ፣ ብዙዉን ጊዜም በሕይወት የሌሉ ሰዎችን ለምስክርነት እያቀረበ፣ ስለራሱና በድርጅቱ ውስጥ ስለነበረው ሚና ያሰኘውን ትርክት አቅርቧል። 

Advertise here _ borkena

ብዙዎቻችን በግል ከመገረምና አንዳንዴም ተገናኝተን ስናነሳው ከመሳቅ አልፈን የመተቸት ፍላጎት አልነበረንም። እስከ አሁን ድረስ ከመተቸትና ውሸቶቹን ከማጋለጥ የተቆጠብንበት አንዱ ምክንያት የሚዘረዝራቸው ነጥቦች ትርኪምርኪ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለቅጥፈቶቹ ሁሉ መልስ መስጠት ለእርሱ የማይገባውን ክብር መስጠት መስሎ ስለታየን ጭምር ነበር። 

ሆኖም፣ በፅሑፍ የሰፈረና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቅጥፈት እውነት ሊመስልና ብዙዎችን ሊያሳስት እንደሚችል እናውቃለን። እኛም ታሪክ ሲንጋደድ፣ እውነት ሲንሸዋረር ያየነውን እንዳላየን ሆነን ማለፍ እንደሌለብን እንረዳለን። ስለዚህም እንደዚህ አይነቱን አስነዋሪ ተግባር የማጋለጥ ሃላፊነትና የተጣመመውን ትርክት ማቃናት እንዳለብን በማመን ይህንን ፅሑፍ አዘጋጀን። 

ይኽ ሰዉ፤ አነዚህን ሁሉ ዉሸቶችና ማጋነኖች ሲተርክ በጊዜውና በቦታው የነበርን ሰዎች እውነት እንዳልሆኑ በሚገባ እንደምናውቅ ሊሳተው አይችልም። አያዩብኝም ብሎም ሊሆን አይችልም። ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ እንደልቡ ሲዘላብድ፣ ከዛሬ አርባ አምስት አመት በፊት የተፈፀሙት ድርጊቶች ተረስተዋል፣ ማንም አያስታውሳቸውም  ብሎ ሊሆን አይችልም። እነዚህን ውሸቶች የሚያቀርበው ለማያውቁት ሰዎች ብቻ ከሆነ፤ “ጅብ፣ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” እንደሚባለው መሆኑ ነው። 

ይኽ ሐተታችን የተፃፈው በርካታ ውሸቶች በታጨቁባቸው በመፅሐፉ አስራ ሁለቱም ምዕራፎች ላይ ሳይሆን፣ “ከዳግም እስራት እስከ ዳግም ስደት” በሚል ርዕስ ስር በሰፈረው ምዕራፍ ላይ ብቻ ነው። ትኩረታችን  በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሁላችንም አብረነው 4ኛ ክ/ጦር እስርቤት ውስጥ በነበርንበት ጊዜ “ተከናውነዋል” ብሎ በዘረዘርቸው ቅጥፈቶች ላይ የተወሰነ ነው። ይኽን የሚያነቡ ሁሉ በሌሎቹ ምዕራፎች ላይ ስንትና ስንት ውሸቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በቀላሉ መገመት ይችላሉ። 

Advertise here _ borkena

ውሸትና ጉራ ተደጋጋፊ መንትዮች ናቸው። አንድ ሰው ጉረኛ ለመሆን መጀመርያ ያልሆነውን ነኝ ብሎ እራሱን ማሳመን አለበት። ማለትም፣ ለራሱ መዋሸት አለበት። ከዚያ በኋላ ጉራ ሹፌር፣ ውሸት ነዳጅ ይሁኑና ጉዞው ይቀጥላል።

“ከዳግም እስር ወደ ዳግም ስደት” ውስጥ የሰፈሩ ቅጥፈቶች

ቅጥፈት አንድ፡ ኃይሌ ፊዳ የእስርቤቱን አለቃ አስጠርቶ አቤቱታ ስለማቅረቡና “አንድም እስረኛ ሳይቀር” ሁላችንም እየተደበደብን ወታደራዊ ቅጣት ስለመቀጣታችን አማረ 4ኛ ክ/ጦር ታስረን በነበርንበት ጊዜ ስለነበረብን የምግብ እጥረት ከዘረዘረ በኋላ “እንደማስታውሰው” በማለት ቅጥፈቱን ይጀምራል። 

“እንደማስታውሰው፣ ኃይሌ ፊዳ በተረኛ ዘብ አለቃው በኩል የእስር ቤቱ ኃላፊ ወደ እኛ እንዲመጣለት ካደረገ በኋላ “ቀለብ የሌለው እስረኛ የሞተ ሬሳ ማለት ነውና እናንተም የምትጠብቁን ሰዎች መኾናችን ቀርቶ አስከሬን ከመኾናችን በፊት ለደርግ የቀለብ ጥያቄያችንን አቅርቡልን” ብሎ ይናገራል። ቂም የቋጠሩት የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ዕድሉን እንዳገኙ ቆጥረው፣ በመኢሶንነት የታሰረ አንድም እስረኛ ሳይቀር ወደ ውጪ አስወጥተው፣ ሲሚንቶና አሸዋ ላይ እያንከባለሉና በሽመል እየጠበጠቡ በእንፉቅቅ ሳይቀር እያስኬዱ ቀጡት” (ገፅ 283) ይላል። 

አጭሩ መልስ፤ ኃይሌ የእስርቤቱን ኃላፊ በማስጠራት በዚህ ጉዳይ ላይ አነጋግሮ አያውቅም። እስረኞች ችግሮች ሲኖሯቸው ጥያቄዎቻቸውን የሚያቀርቡት በቤቱ ካቦ በኩል ብቻ ነበር። ኃይሌ ደግሞ የቤት ካቦ ሆኖ ስለማያውቅ ለእሰርቤቱ ኃላፊ ስለ ምግብ አቤቱታ ሊያቀርብ አይችልምም፣ አላቀረበምም። በመሆኑም በኃይሌ የምግብ ስጡን ጥያቄ መነሻነት እና ይህንን ሰበብ በማድረግ የእስርቤቱ አስተዳዳሪዎች ቅጣት ፈጸሙብን የሚለው ከመነሻው የአማረ ፈጠራ ነው።

አማረ የሚለውም ቅጣት ፈጽሞ አልደረሰብንም። ለመሆኑ፤ “በመኢሶንነት የታሰረ አንድም እስረኛ ሳይቀር” ወጥቶ ወታደራዊ ቅጣት ሲቀጣ፡ ከፍራሹ ላይ ፍጹም መነሳት አይችል የነበረው በሽተኛው ራሱ አማረስ እንዴት ችሎ ተነስቶ ተቀጣ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። በመፅሐፉ ላይ በተደጋጋሚ የፍራሽ ቁረኛ ነበርኩ እያለ የፃፈው አማረ ለዚህ ውሸቱ ማስተካከያ ምን ሊያቀርብ ይችላል? 

አስገራሚው ነገር፣ ሁላችንም የመኢሶን አባል ወይንም ደጋፊ በመባል ታስረን በዚያ እስርቤት ባሳለፍነው የድፍን አምስት ዓመታት ረዠም ጊዜ ውስጥ፤ ከሃያ ዓመታት ዕድሜ በታች የሆኑትን ወጣቶች ጨምሮ፣ ለአሳሪዎቻችን ምንም ሰበብ ላለመስጠት ስለምንጠነቀቅ ከመካከላችን የዲሲፕሊን ቅጣት የደረሰበት አንድ ሰው ብቻ ነበር። እሱም፣ አማረ እራሱ በመጽሐፉ (ገፅ 293-4) ላይ እንዳሰፈረው ሌላ ክፍል ለሚገኙ እስረኞች እንዲያደርስለት ብሎ በራሱ ፈቃድ የጻፈውንና ያዘጋጀውን የተጣጠፈ ትንሽ ወረቀት ሙሉጌታ አስማማው ለሚባል ጓደኛችን የሰጠ ጊዜ ነው። ሙሉጌታ ይህቺን የተጣጠፈች ወረቀት ወደ ሌላ ክፍል ሲወረውር ይያዝና ከበድ ያለ ወታደራዊ ቅጣት ይደርስበታል። እኛ እስከምናውቀው ድረስ፣ በጋራም ሆነ በግል ከሙሉጌታ ሌላ ከመካከላችን ማንም የዲሲፕሊን ቅጣት ሲቀጣ አይተን አናውቅም። 

ይልቁንስ የሚገርመው አማረ እንደሚከተለው የተረከው ፈጠራ ነው፤

“….በዚያን ጊዜ ሙሉጌታንና ግርማ መድኃኔን የወታደር ቅጣት በመቅጣት፣ በሲሚንቶና አሸዋ ላይ እያንበረከኩና እያንፏቀቁ ቢቀጥዋቸውም፣ የኔ የጤንነት ሁኔታ ይህንን የመሰለ ቅጣት መቀበል የሚያስችል ባለሞኾኑ፣ በዚያን በክረምት ወቅት ከእስር ቤት ወጪ ግድግዳ ሥር ቀን ተለሊት ዝናብ እየወረደብኝ እንድቀጣ ተወሰነብኝ። ይህ ውሳኔ ለተረኛ ዘብ አለቆች ተላልፎ ብርድ ልብስ ብቻ ላዬ ላይ ተጥሎልኝ አንድ ቀን ያህል እዚያው ዋልኩ። ምሽቱ ላይ እስረኞች ተቆጥረው ርክክብ ከተደረገና ከተቆለፋባቸው ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ከሌሎች የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ዐልፎ ዐልፎ አዛኝነት ይታይበት የነበረው ዋና ኃላፊ ሻለቃ ገብሩ ተደርጎ የማይታወቀውን በምሽት የእስር ክፍሉን አስከፍቶ፣ ወደ እስር ክፍሉ እንድመለስና ከሌሎች እስረኞች ርቀቴን ጠብቄ ከበሩ ስር ፍራሼ ተዘርግቶ እንድተኛ ፈቅዶልኛል” 

የጤንነቱ ሁኔታ እንደ ልቡ የማያንቀሳቅሰው አማረ፣ አንድ ቀን አንዲት ብርድ ልብስ ብቻ ደርቦ ሲሚንቶ ላይ ተኝቶ መዋል እንዴት ቻለ? ሀቁ፣ አማረ የሚለው ቅጣት በፍጹም አልደረሰበትም። በትክክል የሆነውና ሁላችንም የምናስታውሰው፣ የእስር ቤቱ ኃላፊ ሻለቃ ገብሩ በቁጣ ገብቶ “ምነው አማረ፣ አሁንም አታርፍም? በአንተ ገመድ እኛንም ልታስገባን ትፈልጋለህ?” ብሎ እንደጮኽበትና በመጣበት አኳኋን ተመልሶ መውጣቱንና ከዚህም ጋር በተያያዘ ለምርመራ ወደ ደርግ ጽ/ቤት ምርመራ ክፍል መሄዱን ነው። በምርመራ ክፍሉ ተካሂዷል ብሎ የፃፈውን በተመለከተ፣ እኛ በቦታው ያልነበርን እንደመሆኑ የምንለው እንደማይኖረን ግልፅ  ነው።

ቅጥፈት ሁለት፡ የካሣሁን ብርሃኑ እና የዘካርያስ ኃይሉ መደባደብ

“ .. በተለይ ኃይሌ ፊዳ ከተገደለ በኋላ ባንዳንድ ከወለጋ ክፍለ ሀገር ከመጡ ወጣት የመኢሶን ካድሬዎች መካከል የኦሮሞ ብሄርተኝነት ዝንባሌ ብቅ ብቅ ከማለት አልፎ አንዳንድ ጓዶችን በአማራ ነፍጠኝነትና ተስፋፊነት መጎንተልና መተንኮስ ተጀምሮ ነበር። በዚሁ ሰበብም በዘካርያስ ኃይሉና ካሳሁን ብርሃኑ መካከል እስከ መደባደብ የተደረሰበት አጋጣሚ ትዝ ይለኛል።” (ገጽ 315)

አማረ “ትዝ ይለኛል” የሚለው “ድብድብ” እንደ ተለመደው በአማረ ምናብ ውስጥ ብቻ የነበረ ቅዠት ነው። ማንኛችንም ይህን ድብድብ አላየንም። የእስር ቤቱ ጥበት እና ገላጣነት ደግሞ እንኳን ድብድብን መሰዳደብንም የሚደብቅ አልነበረም። ካሣሁን በሕይወት ኖሮ የአማረን ርካሽ ውሸት ለማጋለጥ ባይታደልም፤ ዛሬ በሕይወት ያለው ዘካርያስ ኃይሉ ይኽ በፍጹም እንዳልተፈፀመ ይመሰክራል።

አማረ ከላይ በቀረበው ጥቅስ ውስጥ ከወለጋ ክፍለ ሀገር የመጡ የመኢሶን ወጣት ካድሬዎች የሚላቸው፣ በአማራ ነፍጠኝነትና ተስፋፊነት ማንንም ጎንትለው አያውቁም። እነዚህ ወጣቶች ከሌሎች ጋር በአንድነት አማረን ከሚተኛበት ፍራሽ ላይ አንስተው እንዲፀዳዳ ይረዱት እና ሰውነቱንም ያጥቡት የነበሩ መሆናቸውን ሊረሳው አይችልም። ጥሩ ህሊና ቢኖረው፣ እነዚሁ ወጣቶች እሱን ከመርዳት አልፈው ሌሎች ቀደም ሲል የታሰሩና በእድሜያቸው የገፉ አዛውንቶችን እንዴት ይረዱ እንደነበረ በፃፈ ነበር። 

ቅጥፈት ሦስት፡ የተካልኝ ጥርስ ህመምና የአሥር አለቃ ጥላሁን መልስ

“..ከጎጃም ክፍለ አገር ተይዞ አብሮን ታስሮ የነበረ፣ ስሙን በትክክል ካስታወስኩት፣ ተካልኝ የሚባል የትግራይ ተወላጅ ጓድ የጥርስ ህመም አጋጥሞት አሥር አለቃው በሌላ ክፍል የታሰረ ህመምተኛ ለማየት ሲያልፍ አይቶት የጥርስ ህመሙን አስመልክቶ” ይህው ባንደኛው መንጋጋዬ በኩል እብጠትና ህመሙ ስላሰቃየኝ መብላት አልቻልኩም” ሲለው፣ “በሌላኛው መንጋጋ መብላት ትችላለህ” ብሎ ቀልዶበታል። ተካልኝም “የቀረውም አንደኛው መንጋጋዬ እንደ እብጠት ብጤ እየሞከረው ነው“ ሲለው፣ እንደገና መልሶ በፊት ጥርሶችህ መብላት ትችላለህ” ብሎ እንዴት በፊት ጥርሱ ማኘክ እንደሚችል ቆም ብሎ በሹፈት እያሳየው አላግጦበት አልፏል። ተካልኝ አንድ አይና ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የአይኑን ህመም አስመልክቶ ያለው አንድ ዓይን እንደ ሆነና ሕክምና በአስቸኳይ እንዲፈቀድለት ቢጠይቀው ”ለምን ሌላውም አይንህ ድርግም አይልም” ብሎ መልሶለታል።” (ገፅ 290)

አማረ ተግባሩ፣ አምልጦት የተነፈሰው ዕውነት ካለ፣ “በትክከል ካስታወስኩት” ብሎ ያሰፈረው የጓዳችን ስም ብቻ ነው። አዎን የወንድማችን ስም ተካልኝ ነው። ግን ተካልኝ የአይን እንጂ የጥርስ ህክምና እንዲደረግለት ጠይቆ አያውቅም። ዛሬም፤ ጥርሱን ታመመ የተባለው ተካልኝ “ታምሜ የማላውቀው ነገር ቢኖር ጥርሴን ነበር፣ ምነው አማረ በዚህ ደግሞ ባይመጣብኝ!” ይላል። የሚገርመው፤ እንደ አማረ አገላለፅ ሳይሆን፤ ተካልኝ ላቀረበው የአይን ህክምና ጥያቄው እድሉ ቀንቶት ፍፁም ከዚህ በፊት ባልታየ ፍጥነት በማግስቱ በጎ ምላሽ አግኝቶ ራሱ አሥር አለቃ ጥላሁን ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ወስዶት ተገቢ ሕክምና ማግኘቱን ስለሚመሰክር፤ የአማረ ሐተታ ያው የለመደበት ሱሱ ያመነጨው ፍሬቢስ ትርክት መሆኑን ያረጋግጣል።  

አማረ፣ እስርቤት የነበረውን የሕክምና ችግር፣ ምንም ሳይጨምር መተረክ ይችል ነበር። ነገር ግን በተደጋግሚ እንደሚታየው፣ የአማረ ብዕር እውነቱን ብቻ መጻፍ ያዳግታታል። 

ቅጥፈት አራት፡ ኃይሌ ፊዳ፣ መኢሶን የትግል ስልት የለውጥ እርምጃ ሲወስድ፣ የድርጅቱን አባላትን በታትኖ ወደ ተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የማስወጣት ውሳኔን ስለመቃወሙ

“…ከኃይሌ ፊዳ ጋር 4ኛ ክ/ጦር ታስረን በነበርንበት ዘመን ይህንኑ “የትግል ስልት ለውጥ” ተግባራዊ ለማድረግ የድርጅቱን አባላት በታትኖ ወደ ተለያየ የገጠር አካባቢ የማስወጣቱን ውሳኔ ተቃውሞ እንደነበር ጉዳዩ ለመወያያ በተነሳ ቁጥር ይነግረን ነበር።  ውሳኔው በተወሰደበት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ስብሰባ ላይ የሰጠውም ምክንያት በዚህ አይነት ኃይልን በታትኖ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ብናስወጣ፣ ለጠላት በቀላሉ እያንዳንዳችን እየነጠለ ለመምታት ያመቸዋል። ይልቁንስ ኃይላችንን አንድ ላይ አሰባስበን፣ ጠላት ሊያጠቃን ቢመጣ በጋራ ለመከላከልና ካቅማችን በላይ ከሆነ በቀላሉ ወደኋላ በማፈግፈግ ወደ ጎረቤት አገር መጠጊያ ለመጠየቅ እንድንችል መምረጥ ያለብን ወደ ኬንያና ጅቡቲ ድንበር አካባቢ መሆን አለበት ብሎ ሓሳብ ቢያቀርብም በአብላጫ ድምፅ ውድቅ እንደተደረገ አጫውቶኛል…” [ስርዝ የተጨመረ] (ገፅ 334- የግርጌ ማስታወሻ ስርዝ የተጨመረ)

አማረ፣ ከላይ በተጠቀሰው ፅሑፉ የሚያቀርበው፣ ኃይሌ አባላትን በታትኖ ወደ ውጪ ማስወጣትን በድርጅቱ አመራር ስብሰባ ላይ ተቃውሞ እንደነበረና፣ ይህንንም 4ኛ ክ/ጦር እስርቤት ለነበርነው በተደጋጋሚ ይነገረን እንደነበረ ነው። 

አማረ፣ “ጉዳዩ በተነሳ ቁጥር [ኃይሌ] ይነግረን”  ነበር እያለ የሚተርከው፣ የኃይሌ ህቡዕ የመግባት ተግባራዊ አፈፃፀም ተቃውሞ፣ አማረ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ተንሰራፍቶ የተቀመጠ ቅዠት ነው። ሀቁ፤ ኃይሌ በፍጹም በአመራሩ ውስጥ እንዲህ አይነት መከፋፈል እንደነበረና እሱም እንደተቃወመ ለማንኛችንም በግልም ሆነ በጋራ አንስቶብን አያውቅም። አንደኛችንም፤ እንደዚህ ያለ ነገር ከኃይሌ አንደበት አልሰማንም። አማረ፤ ኃይሌ በተደጋጋሚ አነሳው የሚለው ነገር የሁላችንንም  ሕይወት የሚመለከትና ብዙ ጓዶቻችንን ያጣንበት አብይ ጉዳይ ስለነበረ አማረ ብቻውን “የሚያስታውሰው” እኛ ሁላችንም  “የረሳነው” ጉዳይ ሊሆን አይችልም። 

ኃይሌ፣ ምን ያህል ቁጥብና ጠንቃቃ ሰው እንደነበረ የሚያውቁ ሁሉ፤ በአጠቃላይ አመራሩ ውስጥ ስለነበሩ ክርክሮችና ስለራሱ አቋም ቀርቶ በአባላት ዘንድ በሰፊው በሚታወቁ የውስጥ ልዩነቶችና ክርክሮች ላይ ማን ምን እንዳለ፣ በየስብሰባው የተባለውንና የተወሰነውን የሚዘረግፍ ሰው አልነበረም። 

በተጨማሪም፣ ኃይሌ ከመታሰሩ ጥቂት ወራት በፊት የሞቱትን የትግል ጓዶቹን፣ እነ ከበደ መንገሻን፣ ዳንኤል ታደሰ፣ ተረፈ ወልደፃድቅና ከድር መሃመድን በአደባባይ  የሚያሳጣ ራስ ወዳድ ሰው አልነበረም። 

ሁለተኛ፣ ዛሬ በሕይወት የሌለውና እማኝነት ሊጠራ የማይችለው ኃይሌ ለሌሎቻችን ሳይናገር ለርሱ ብቻ “…በአብላጫ ድምፅ ውድቅ እንደተደረገ ነግሮኛል” ሲል የጨመረው አባባል ደግሞ ቀደም ሲል ያሰፈረውን ውሸት በሌላ ቅጥፈት ለማጠናከር የሸነቀረው ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? 

ማጠቃለያ

ውሸትም ቢሆን መልክ አለው። ለዋሾው የሚጠቅሙና የማይጠቅሙ ውሸቶች አሉ። የሚጠቅሙ ውሸቶች፣ የራስን ሚና በማጋነን፣ የዘመኑ የፖለቲካ ገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ የሚያስገኙ ሸቀጦች ለማምረት ሊያገለግሉ ይችላሉ።
የማይጠቅሙ ውሸቶች ግን፣ ለምን እንደሚዋሹ ማወቅ ያስቸግራል። ሱሰኛ ውሸታም እራሱም ሲዋሽ አይታወቀውም ይባላል። አማረንም ይኽ የውሸት ሱስ ክፉኛ  ተፀናውቶታል። 
ለማንኛውም፣ ከማይጠቅሙት ዉሸቶቹ ጥቂቶቹን አሳይተናል። የሚጠቅሙት ዉሸቶቹን በሚመለክት የሚያውቁት እየሳቁበት እንደሆነ ተረድቶ፣ የማያውቁት የሚያነጥፉለት ቁርበት ላይ ሸለብ ይበል። 

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

Ethiopian NewsBorkena English

ኤክስ ፡ @zborkena