ነፃ አስተያየት

April 3, 2026

Updated: April 3, 2026

ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group

  ኮብራዉ ከኦሮሚያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ  ለብዙ  ሺህ  ዓመታት ሁሉንም ልጆቿን ያለምንም አድልኦና መግፋት አቅፋና ደግፋ በመያዝ በአንድነት እንዲኖሩ ያደረገች እናት ነበረቸ፡፡ ይህ በመሆኑም ጉራጌዉ፤ ትግሬዉ፤አማራዉ ወላይታዉና ሲዳማዉ ዉዘተ በንግድ፤ በመንግሥት ሥራና በመሳሰሉት ላይ በመሰማራትና አበረዉ  በመኖር አገራቸዉን ሲያበለጽጉና ሲያሳድጉ ኖራዋል፡፡ ይህ ሲሆንም  በገዥዎች ዓይን ይሆናል እንጂ  በሕዝቡ መካከል የበታችነትና የበላይነት ሳይኖር በእኩልነት፤ በወንድም አማችነትና በአንድነት ኖረዋል፡፡  ኃብታምነትና ድህነትም ቢሆን በራስ ታታሪነት፤ቅልጥፍናና አዋቂነት ላይ የተመረኮዘ እንጂ እንደዛሬዉ መንግሥት ለአንዱ መልካም ዕድል ፈጥሮ ኃብታም እያደረገ ሌላን ወደ ድህነት አዘቅት እንዲገባ የተደረገበት ወቅትም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ይሁን እንጂ በአለፉት ስምንት ዓመታት የኦሮሞን የበላይነት አረጋግጣለሁ በሚል ዕሳቤ በፌደራል ደረጃም ሆነ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅና ያልተፈጸመ ድርጊት   ተፈጽሟል፤ በመፈጸም ላይም  ይገኛል፡፡

ከአንድ አገር መንግሥት ከሚጠበቁ ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶች መካከል አንዱና ዋነኛዉ የአገሪቱን ዜጎች  በእኩልነት፣በግልጸኝነትና በታማኝነት ማገልገል ነዉ፡፡ በታደሉና ዴሞክራሲን በተላበሱ አገራት አንድ መንግሥት በምርጫ ወደ ሥልጣን ለመዉጣት በሚያደርገዉ ሩጫ ለመራጩ ሕዝብ ከሚገባቸዉ ቃላት አንዱና ዋነኛዉ ይህ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ የጊዜዉ የብልጽግና መንግሥት የኦሮሞን የበላይነት ለማረጋገጥ በሚል ተገቢ ባልሆነና በማያዋጣ መንገድ በቀየሰዉ ስትራተጅ ምክንያት ከኦሮሞ ዉጭ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ማለትም በአማራዉ፤ በትግሬዉ፣በጉራጌዉ፤በስልጤዉና ወላይታዉ ወዘተ ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ፍትህ የጎደለዉ ስትራተጅ የተነሳም በኦሮምያ ክልል ዉስጥ በሁሉም ዞኖች፤ወረዳዎችና ከተሞች የሚኖረዉ ከኦሮሞ ዉጭ የሆነዉ የሕዝብ ክፍል እነርሱ ’’መጤ ’’ የሚል ስያሜ ሰጥተዉታል በኢኮኖሚዉ፤ በፖለቲካዉና በማሀበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ባይታወር ሆኖና መድረሻ አጥቶ በአልሞት ባይ ትጋዳይነት ላይ ይገኛል፡፡  

መጤ እየተባለ የሚጠራዉ ክፍል በኢኮኖሚዉ ዉስጥ ያለዉን ተሳትፎ ብንመለከት በመጀመሪያ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ የመንግሥት ሥራ እድል የሚሰጠዉ የኦሮሞኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ ስሙ እስከ አያቱ ድረስ  ተመርምሮ  ሲሆን የቤት መሥሪያ ቦታን ጨምሮ ማንኛዉም ጥቅማ ጥቀም የሚሰጠዉ በቢሮ ደረጃ ተደራጅቶ ስለሆነ ይህ ክፍል በኢኮኖሚዉ ላይ ምንም ዓይነት የመሳተፍ ዕድል የለዉም፡፡  በየከተማዉ፣ በየዞኑና በየወረዳዉ  ዉስጥ ምን እየተካሔደ እንዳለ እንኳ የማወቅም ሆነ የመሳተፍ ዕድል አጥቶ በመገፋት ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በየዓመቱ 35000 (ሰላሳ አምስት ሺህ) የኦሮሞ ባለኃበቶችን  እንፈጥራለን በሚል የተሳሳተ ዘይቤ የስንቄ  ባንክና የኦሮምያ ካፒታል የፋይናንስ አቅራቢ፤ የየከተማዉ፤ ዞንና ወረዳ መስተዳድር የመሥሪያ ቦታን ጨምሮ አስፈላጊ የሆነዉን ኃብት፤የመሬት፤የማደራጀትና የምክር አገልግሎት  አቀራቢ በመሆን ስለሚሰራና ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዉጭ ያለዉ ኢትዮጵያዊ በዚህ ዕድል የመሳተፍ ዕድል ስለሌዉ  በግልጽ የተገለለና የተገፋ ሆኖ በጻረ ሞት ላይ ይገኛል፡፡ የኦሮሞን የበላይነት ለማረጋገጥ  የሌላዉን መብት መግፈፍ፤ መደፍጠጥና በተለያየ መንገድ ማደህየት በሰፊዉ አየተሰራበት ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ከኦሮሞ ዉጭ ያለዉን ኢተዮጵያዊ በግብር፤ በቢሮክራሲ፤ በቫት ደረሰኝ አልቆረጠክም በሚልና በመሳሰሉት ምክንያቶች በማሳደድና መከራ በማብላት  ተማሮ  ድርጅቱን እንዲዘጋና ክልሉን ጥሎ እንዲወጣ ያደርጉትና፤ ፋይናንስ በማዘጋጀት የራሳቸዉ ሰዎች ንብረቱን እንዲገዙት ሁኔታዉን ያመቻቹላቸዋል፡፡   ይህን በመሰለ እኩይ ተግባር የተማረረ ኢትዮጵያዊ ኦሮሚያን ሲገልጽ ‘’I feel more comfort in Kenya than living in Oromia’’  የአማርኛ ትረጉሙም በኦሮሚያ ዉስጥ ከመኖር ይልቅ በኬንያ መኖር የበለጠ ምቶት ይሰጠኛል በሚል ይገለጸዋል፡፡ 

ከላይ እንደተገለጸዉ ከአንድ መንግሥት ከሚጠበቁ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች አንዱና ዋናኛዉ የአገሪቱ ጥሪትና ኃብት ለአገሪቱ ዜጎች  በእኩልነት፤ በፍትህና በግልጸኝነት እንዲዳረስ/እንዲከፋፈል ማድረገ ቢሆንም ቅሉ የጊዜዉ የብልጽግና መንግሥት ግን በኦሮምያ ዉስጥ ያለ ኃብት (Resources) ለኦሮሞ ብቻ ነዉ በሚል እየተከተለ ያለዉ ኋላ ቀር መርህ ግን በጣም አደገኛና የማያዛልቅ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ዘመን ተሻጋሪ ባለኃብት ለማፍራት መሞከር እንጂ ያለድካም፤ ያለጥበብ፤ በዕዉቀት ላይ ያለተመረኮዘ ኃብት በማንነቱ ብቻ አግባብ በሌለዉ መንገድ ለማበልጸግ መሞከሩ አደገኛ  አሰራር ነዉና ነዉ፡፡ ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረገጥ በደርግ መንግሥት የተወረሱና በክልሉ ዉስጥ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ኦሮሞ ባልሆኑ ማለትም አማራዉ፤ትግሬዉ፤ጉራጌዉ፤ዉላይታዉ ወዘተ በሆቴልነት፤ በሱቅ፤ በካፌና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ላይ አየሰሩባቸዉ እያለ ከዕነርሱ በመንጠቅ ያለምንም ጨረታና ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ ለተመረጡ የራሳቸዉ ሰዎች እንዲሰጥ አያደረጉት ይገኛል፡፡

Advertise here _ borkena

ከዚህ በተጨማሪም ኦሮሞዎቸን ከገጠር አፍልሶ ወደ ከተማ በማስገባት የከተማ ቦታ ባለቤት ለማድረግ በተያዘዉ እቅድ መሠረት በአገር ደረጃ በሕግ በማይታወቅ ‘’ማሸጋሸግ’’ በሚል ስም ከተወሰነ ካሬ ሜተር በላይ የያዘዉን አማርኛ ተናጋሪ በመቀማት ለኦሮሞዎች በማዉረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ላይ በሕግ ተሰጥቶኝ እየገበርኩበት ያለ ቦታዬን ለምን ከሕግ አግባብ ዉጭ እነጠቃለሁ የሚል አቤቱታ የሚያቀርብ ግለሰብ እንኳን ለዚህ ለቀረዉም ዋስትና የለህም እስከአሁን የበላሀዉ ይበቃሀል በሚል እንዲኮረኮም ይደረጋል፡፡ 

ዛሬ በኦሮምያ ዉስጥ ሕግ ፤ ፍትሀና  መልካም አስተዳድር ጠፍቶ ሙስና ተንሰራፍቶ ናሪዎቿ በከፍተኛ ስቃይና መከራ ዉስጥ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየወረዳ፤ ዞን ወይም የከተማ ኗሪዎች በኢትዮጵያዊነታቸዉ ሳይሆን በኦሮሞ ባለሥልጣናት በጎ ፈቃድና ችሮታ እንደሚኖሩ በግልጽ ይነገራቸዋል፡፡  

አንድ ዜጋ በአገሩ ዉስጥ በነጻነትና በሰላም  ሰርቶ እንዳይኖር የሚከለከልና የሚገፋ ከሆነ ኢትዮጵያዊነቱ የት ላይ ነዉ? ነገሮቹ ሁሉ በዚህ ከቀጠሉና የዜጎች ሰባዊ መብት እንደዚሀ በከፋ ሁኔታ የሚገፈፍ ከሆነ አገር አለኝ ማለትና የወደፊት በሰላም አብሮ የመኖር  ተስፋስ እንዴት ሊቀጥል ይችል ይሆን? ዛሬ በኦሮሚያ ዉስጥ ምስቅልቅል ያለ ሕይወት እንዲኖር በኃይል በማፈናቀል፤ አመጽና ሁከት በመፍጠር ማሳደድ፤ ማፈንና ማባረር የተለመደና የቀን ከቀን ዕጣ ፋንታ ሆኖ ይገኛል

በኦሮሚያ ዉስጥ ከፍተኛ መከራና ስቃይ እየተቀበለ ያለዉ ደግሞ ኢትዮጵያ አገሬ ናትና በአገሬ ዉስጥ በየትኛዉም ቦታ በመዘዋወር ሰርቸ በሰላም የመኖር መብት አለኝ በሚል የትዉልድ ቀየዉን በመተዉ በኦሮሚያ ዉስጥ በንግድ፤ በኢንቨስትመንት፤ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘዉ አማራዉ፤ ትገሬዉና ጉራጌዉ ወዘተ ነዉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ይህ የሕዝብ ክፍል ኃብት የማፍራት ነጻነትና ለአፈራዉ ኃብትም ቢሆን ምንም ዓይነት ዋስትና (Guaranty) የለዉም፡፡

Advertise here _ borkena

በተመድ ቻርተር ላይ ማንኛዉም ግለሰብ ሲዳኝና ሲታከም በሚያዉቀዉ ቋንቋ መሆን እንዳለበት በመግለጽ ይህ ካለሆነ ግን የዚያ ሰዉ ሰባዊ መብት እንደተገፈፈ ይቆጠራል ይላል፡፡  ይሁን እንጂ በኦሮሚያ ዉስጥ ይህ ኃሳብ አይታወቅም፤ አይሰራምም፡፡ በየቢሮዉ ሄደህ ኦሮሞኛ መናገር  የማትችል ከሆነ ህጋዊ የሆነ አገልግሎትና ፍትህ ማግኘት አትቸልም፡፡ ይህ ደግሞ ሕግና ፍትህን የሚያዉቁ ባለሙያዎች በሚገኙበት በፍትህ አካላት መ/ቤቶች የባሰ ሆኖ ይገኛል፡፡ 

 አማርኛ ተናጋሪዉ ማህበረሰብ ሰርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የትዉልድ ቀየዉን ጥሎ በሚሔድበት ወቅት ኦረቶዶክሱ ቤተ ክርስቲያኑን፤ ሙሰሊሙ ደግሞ መስጊዱን በማስከተል  የመንፈሳዊ ሕይወቱን በማርካት ይኖር ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም  ይህ የህብረተሰብ ክፍል በኦሮሚያ ክልል በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አብያተ ክርሰቲያናትንና መስጊዶችን በመሥራት መንፈሳዊ አገልግሎትን በማግኘት ላይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒሰትር አቢይ አህመድ ሥልጣን ከጨበጡበት ቀን ጀምሮ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በታጠቁ ኃይሎች ይፈናቀላሉ፤ይታረዳሉ፤ አብያተ ክርሰቲናትም እንዲቃጠሉ  ተደረገ፡፡  በዚህ ላይ እኩይ ተግባራቸዉን ሲጀምሩም፡- 

1ኛ/ የቤተ ክርሰቲያን በዓላት በሚከበሩበት ወቅት የማከበሪያና የክብር መገለጫ የሆነዉ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ የሆነዉ የኢትዮጵያ ባንዲራና መሠረቱን ይህን ያደረገዉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ አርማ በቤተ ክርሰቲያኒቱ ቅጽር ግቢ ዉስጥ በመስቀል ማዉለብለብ የተለመደ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የአገሪቱ ባንዲራ በምንምና በማንኛዉም ሁኔታ በክልሉ እንዳይታይ ባልተጻፈ ህግ ተከለከለ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ክልከላም በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም እዉቅ በሆኑ ቦታዎች ይዞ መገኘትም የተከለከለ ነዉ፡፡ ለምሳሌ በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ዉስጥ በሚገኙ የቅርሳቅርስ መሸጫ ዉስጥ የነገስታት ፎቶዎች፤ የቤተ ክርሰቲያኒቱ መገለጫ የሆኑት ስዕሎች፣መንፈሳዊ መጻህፍትና ማንኛዉም ኢተዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸት ዕቃ (ቅርሳቅርስ) እንዳይሸጥ ቁጥርና ቀን በያዘ ደብዳቤ ተከልክሏል፤ ሲሸጥ የተገኘ ባለሱቅም በዕስርና በገንዘብ እንደሚቀጣም በደብዳቤዉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

2ኛ/ በኦሮሚያ ዉስጥ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኦሮምኛ ካልሆነ በሌላ ቋንቋ የቅዳሴ ሥርዓት አይካሔድም በሚል በመከልከል አማርኛ ተናጋሪዉን ከገነባዉና ከሰራዉ ቤተ ክርስቲያን አባረሩት 

3ኛ/ ከዚህ በመቀጠልም ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑን በማንነቱ የተነሳ መግደል፤ ማሳደድና  ቤተክርሰቲያኑንም ማቃጠል በመፈጸሙና ሕዝቡም ቅየዉን ጥሎ እንዲሰደድ በመደረጉ ምክንያት በአርሲ ብቻ 67 አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ ይህም የሚያሳየን ምን ያህል ሕዝብ የተፈናቀለና የተሰደደ መሆኑን ነዉ፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ታሪክ ሰራዥና ደላዥ ደርጊቶች እየተፈጸሙ ባለበት በአሁኑ ወቅትም በአማራዉ ስም ሥልጣን ላይ የተቀመዉ የቀድሞ ብአዴንና የአሁኑ የአማራ ብልጽግና ባለሥልጣናት እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮች እንደሚፈጸሙ እያወቁ ምንም ሊሉ አለመቻላቸዉ ደግሞ የአማራን ኃዘን ሁለት እጅ (double) አድርጎበታል፡፡   

የጅዉሾችንና የአማሮችን ያለፈም ሆነ የዛሬ  ታሪካቸዉን ስናጠናና ስንመለከት የተሳሰረና አንድ ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  አማራዉ በኦሮሚያ  ዉስጥ እንዳደረገዉ ሁሉ  ጂዉሾችም ከ1264 ዓ. ም ጀመሮ የንግድ ዕድሎችን ፍለጋ ወደ ሰሜን አዉሮፓ በመሔድና ከፍተኛ ኃብት በማፈራት በሰላምና በብልጽግና ኖረዋል፤ለየአገሮች የኢኮኖሚ ዕድገትም ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይህን የመሰለ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም ቅሉ ይህ ከግንዛቤ ሳይወሰድላቸዉ የተለያየ ስም በመስጠት አሳደዋቸዋል፤ገድለዋቸዋልም፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በአማሮች ላይ እየተፈጸመ እንዳለዉ ሁሉ ከ1933-39 ዓ.ም ድረስ የናዚ ተከታዮች ጅዉሾችን በማሳደድና፡ በመግደል በጀርመን ምድር መኖር በማይችሉበት ደረጃ ላይ አድርሰዋቸዉ ነበር፡፡ ዛሬ የአርሲ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች አማሮችን በሙሉ ለማጥፋት አየሞከሩ እንዳሉ ሁሉ የናዚዎች ዓላማም ጅዉሾችን ከገጸ ምድር ጠራርጎ ማጥፋት ነበር፡፡

ጅዉሾች በአዉሮፓ ዉስጥ በብዙ ፕሮፌሽኖች ላይ መሥራትን ይከለከሉ እንደነበረ ሁሉ ዛሬ በኦሮሚያ ምድርም ከዚህ በባሰ ሁኔታ አማርኛ ተናጋሪዎች በምንም ሁኔታ  ሥራ የማግኘት ዕድል እንዳይኖራቸዉ ተደርጓል፡፡

As it today is common in oromia region against the Amhara, the Nazis had drafted a law, which officially turned the Jews in to second class citizens with few rights than non-Jews.  As the Chauvinist Oromos did the same against the Amharas, the Nazis had organized pogroms all over Germany to kill the Jews and destroy their homes and businesses.

በኦሮሚያ ክልል አማሮች ለፍተዉና ደክመዉ ንብረት በመያዛቸዉ የተነሳ በዝባዦችና በኦሮሞ ወጭ የበለጸጉ ናቸዉ በሚል እንደሚከሷቸዉና እንደሚወቅሷቸዉ ሁሉ ጅዉሾችንም በ1918 ካፒታሊሰቶችና በሌሎች ወጭ የበለጸጉ  በሚል ይከሷቸዉ፤ ይወቅሷቸዉ ይገድሏዉ ነበር፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየን የጅዉሾችና የአማሮች የመከራ፤የመሳደድና የመገደል ምክንያትና ዕጣ ፋንታ አንድ ዓይነት መሆኑን ነዉ፡፡ ስለዚህ ይህን በመገንዘብ ለወደፊቱ እነዚህ ሁለት አካላት መተባበር፤መደጋገፍና መተጋገዝም አለባቸዉ ፡፡

ጅዉሾች ያነን ያህል የሰባዊ መብታቸዉ ተገፎ ሲሳደዱ፤ሲፈናቀሉና ሲገደሉ  ምንም መተንፈስ ያለቻለዉ የዓለም አቀፉ ማሀበረ ሰብዕና የሰባዊ መብት  ተቆርቋሪ ድርጅቶች ዛሬም በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን በኦሮሚያ ክልል በአማሮች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ እየደረሰ ያለዉን የሰባዊ መብት ጥሰትና በግፍ መገደል በዝምታ በመመልከት ላይ መሆኑ ታሪክ  እራሱን ደገመ ከመሆኑም በላይ በታሪክ የሚያስጠይቅ ነዉ፡፡   

በአገራችን በሰፈነዉ መጥፎ አስተዳድር (Bad governance)፤ ግጭት፤ ጦርነትና በመሳሰሉት ችግሮች የተነሳ  ሀብታሙ ወደ አሜሪካ፤ አዉሮፓና ዱባይ በመሰደድ ኑሮዉን በዚያ እየመሠረተ ሲሆን፤ የአገሪቱ አፍላ ወጣትም ወደ ስደት ሲሔድ ባሕር ዉስጥ እየሰጠመ በማለቅ ላይ ይገኛል፡

በአጠቃላይ አገሩን ይጠብቅ የነበረ ወታደር፤ የነገ አገር ተረካቢዎችን በትምህርት ያንጽ የነበረ አስተማሪና በአገሩ ላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ አገሩን ያበለጽግ የነበረ ኃብታም አገሩን ጥሎ ከተሰደደ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ምን በጃቸዉ??

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና  ሕዝቧን ይባርክ  

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 


ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

Ethiopian NewsBorkena English

ኤክስ ፡ @zborkena