April 8, 2026


እውነቱ ታደሰ
ለምርጫ ምዝገባ ከመጠናቀቁ ሁለት ቀናት በፊት መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በግምባር ቀደምትነት በአቶ ልደቱ አያሌው አስተባባሪነት የተቋቋመው የጋራ መድረክ የሕዝባዊ እምቢተኝነትን ተልዕኮ ያነገበ ዘመኑ በአመቻቸው ቴክኖሎጂ የበይነ መረብ ትዕይንተ ሕዝብ ቀርቧል። በዚህ ፕሮግራም ለንግግር አድራጊነት የተጋበዙ 21 ሲሆኑ፥ውክልናቸው በግል እና ከዘጠኝ በውስጣቸው 50 የሚደርሱ የተለያዩ የፖለቲካ እና ማሕበራዊ ድርጅቶችን የሚያቅፉ ስለመሆናቸውም ተገልጿል። በተጨማሪም፥ ትዕይንቱ በ30 የማሕበራዊ ማሰራጫ ዘዴዎች መተላለፉ ተግልጿል። ይህም ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እና ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ባልሳሳት ይህ ዓይነቱ ፕሮግራም በዚህ የጋራ መድረኩ ለሁለተኛ ጊዜ በሌላ ተመሳሳይ መድረክ ደግሞ እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ የተከናወነ ነው። የዚህ ዝግጅት ቅድመ ማስተዋዋቁ ሥራም ከበፊቱ የላቀ በመሆኑ አዘጋጆችን ያስመሰግናል።
የበፊቱን ሆነ የአሁኑን በአንክሮት ተከታትየዋለሁ። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው በመቆርቆር በተናጠል እና በቡድን ብሎም በትላልቅ ስብስቦች ለአለፉት ግማሽ ምዕት ዓመታት ያህል ያደረጉት እና እያደረጉት ያለው ሰላማዊ ሰልፎች፥ መግለጫዎችና ክርክሮች የዜግነት ግዴታቸው ቢሆንም ከጊዚ እና ከተለያዩ ተግዳሮቶች አንጻር እሰየ የሚያሰኝ እና እጅጉን የሚያስመሰግናቸው ነው። ዛሬም ቢሆን ለአገራችን ደንታ የሌላቸው የእናት ጡት ነካሾችን በተለይም ይህን አስከፊ የግፍ አገዛዝ በከርሳቸው ለውጠው ከጎኑ የተሰለፉትን ስናስብ በየትኛውም ደረጃ እና መመዘኛ በተጠቀሱት የበይነ መረብ ትዕይንቶች እና በተለያዩ መደረኮች የሚሳተፉትን አለማድነቅ እና አለማመስገን ከንፉግነት የባሰ ፖለቲካዊ ስህተት ይሆናል።
ወደአሁኑ በይነ መረብ ትይንተ ሕዝብ እንመልስ። ይህን ትዕይንት የምንቃኘው በሚዛናዊነት እንጂ አንዱንና ሌላውን ለማስደሰት ወይም ለማስቀየም፥ ለመንቀፍ ወይም ለማሞገስ፥ ለመደገፍ ወይም ለመቃወም በሚል እሳቤ አይደለም። በበይነ ትዕይንተ ሕዝቡ ላይ ለማድረግ የተሞከረው ቅኝት ዋና ዓላማ ጠናካራና ደካማ ጎኖችን በማውጣት ለቀጣዩ ዘርፈ ብዙ እና እልህ አስጨራሽ ትግል ትምህርት ለመቅሰም ያስችላናል በሚል እሳቤ ነው። አገራችን ከተዘፈቀችበት አስክፊ ችግር እና አደጋ ልትወጣ የምትችለው በግልጽነት እና በድፍረት እውነትን በማንገስ ከስህተት ስንማር እና ከግል ጥቅም ይልቅ የአገርንና የሕዝብን ፍላጎት ስናስቀድም ብቻ ነው። ዳሰሳውም ይህን መሠረታዊ ግንዛቤ ያማከለ ነው።
ጠንካራ ጎን፥- በመጀመሪያ ደረጃ ለአገር እና ለወገን በመቆርቆር ይህን መሰሉ ዝግጅት መድረጉ አዘጋጆችን እና ንግግር አድራጊዎችን የሚያስመሰግን የጥንካሪው መሠረት ነው። የዝግጀቱ ተልዕኮ ትኩረቶች ማለትም በመግቢያ እና በንግግሮች መካከል የተላለፉት 19 መሪ ቃሎች ወይም መፈክሮች በአጠቃላይ ትክክለኛ እና ጊዜውን የዋጁ መልዕክቶች ናቸው። ንግግር አድራጊዎችም መልዕክቶቻቸውን በሚገባ ነው ያቀረቡት። ሁሉም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የመወገድን እና የሽግግር መንግሥት መቋቋምን አስፈላጊነት የሚያምኑ መሆናቸው የትግሉን ዓላማና አቅጣጫ ቀያሽነት ያመላክታል።

በእርግጥ የቀረቡ ሀሳቦች ቀድም ሲል የዕለቱ ተናጋሪዎች ሆኑ ሌሎች በተለያዩ መድረኮች ካስተላለፏቸው የተለዩና አዲስና ናቸው ባይባሉም እስከ መጨረሻ ሀቅን ይዞ መገኘት አንደኛው የትግል ጥንካሬ ማሳያ ነው። ሁሉም ተናጋሪዎች ስለግፍ አገዛዙ አንገፍጋፊነት፥ ስለሰላም መስፈን እና በአንድነት የመታገልን ፋይዳ አጽንኦት መስጠታቸው የከፋፋዮችን እና የግፍ አገዛዝ ደጋፊዎችን አቅል እንዲመልስ የተለመደ ተስፋን ያስጭራል።
የፖለቲካ ትግል ጥንካሬን ብቻ ይዞ ይጓዛል ማለት አይቻልም። ድክመቶችን ይዞ መገኘቱ ያለና አይቀሬ ነው። ትልቁ ቁም ነገር ጥንካሬን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠልና ድክመቶችንም ነቅሶ በማውጣት ለቀጣይ ትግል አርሞና አስተካክሎ መገኝት ነው። በመሆኑም ይህ ከዚህ በታች የቀረበው የደካማ ጎን ሀሳቦች ለተጠቀሰው ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በአገራችን የለውጥ ትግል ለሚሳተፉ ሁሉ የሚያገለግል ነው።
ደካማ ጎን፥- የዚህ ዝግጅት አዘጋጅዎች ይህን በይነ ትዕይንተ ሕዝብ እንደልዩ እና የመጨረሻውና ብቸኛ ግብ ማስገኛ ከፍተኛ ጅማሮ እንደሆነ አድርጎ መቁጠሩ ባልከፋ። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነውና ይሁን ግዴየለም እንዳንል ችግርን እያወቁ ለችግር መራዘም ምክንያት ይሆናልና አይ! ማለቱ ደግሞ አይከፋም። ከዚህ ቀደም ሆነ ጎን ለጎን የተደረጉትን ትግሎች አሳንሶ የማየት አንደኛው የችግራችን አባዜ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህን ዝግጀት ከልክ በላይ ማጋነን በ2010 ዓ.ም አዲሱና እስከእሁን የዘለቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ እና በአሜሪካ ባደረጉት ያሻግራችኋሁ ኢትዮጵያዊነት ዲስኩሮች ያቀመሱንን “የቀበሮ ደስታ” መድገም እንዳይሆንብን ያስፈራል።
በመሠረቱ ይህን መድረክ ከሌሎች መሰል የትግል ዘዴዎች እንደአንደኛው አድርጎ ማየት ሲገባ አጋኖ መገኘት እስካሁን የተደረጉትንና እየተደረጉ ያሉትን ትግሎች ማንኳስስ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በውጭና በውስጥ ያለን የትግል ደረጃ ያለመረዳት ነው። የሚያስቀው ደግሞ ከአንድ በሳልና ከእርሱ ከማይጠበቅ ጋዜጠኛ የምላስ ድጠት ሳይሆን አይቀርም ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰልፈኞች የእናንተን “የሽግግር መንግሥትን” ጥያቄ አነሱ ማለታቸው ነው። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ የሚያጃጅል እና የትግል ጉዞ አደናቃፊ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰላማዊ ትግል አልፎ በትጥቅ ትግል በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ይህን መድረክ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሩን መከራውን አሳዋቂ እና ብቸኛ የመፍትሄ አቅጣጫ ሰጪ ሆኖ መቅረቡ የበሽታዎች ሁሉ በሽታ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህን ሕዝብ ምን ነካው? እንዴት የአዲስ አበባ ሕዝብ፡ ወጣት ዝም ይላል? ወዘተ የሚሉት የተለመዱ የውጭ ወገኖቻችን ቁጭት ነጸብራቅ እራሱን ችሎ ቢቀርብ ይመረጣል።

ይህ የበይነ ትዕይንተ ሕዝብ በሰላም ጥሪ ስም የአገር ውስጥን ትግል የሚያደበዝዝ ሆኖ ነው የተገኘው። ከዛሬው ትዕይንተ መረብ ቀጥሎ በዋሽንግቶን እና በሎንዶን ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉና በመቀጠልም በአገር ውስጥ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን የሚያቀጣጥል ሆኖ ነው የቀረበው። የሚገርመው እና የሚያሳዝነው በአገር ውስጥ የትጥቅ ትግል ተፋፍሞ አንድ ግዙፍ ክልል ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ መሆኑ፥ ሰላምና ደህንነት በመላ አገሪቱ የጠፋ መሆኑ እና ለዚህ ተጋድሎ የሚያድርጉትን በአጋዥነት በድጋፍ ሰጭነት ለውይይት ጎልቶ አለመቅረቡ ነው። መስዋዕትነት ከከፈለና እየከፈለ ካለ አካል ጎን ለመሰለፍ ፍላጎትን ያላሳየ እራሱ በአደራጀጀቱ ግልጽ ያልሆነ እና አሰላለፉ ሰላማዊ መሆንን ብቻ ግልጽ ያደረገ መድረክ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከማዶ ወደ አገር ውስጥ መንግሥትን እለውጣለሁ ማለቱ ‘እኔው አሻግራችኋለሁ’ ከሚለው የተሻለ አይሆንም። በሌላ ነገር የትግል ስልቱን ካላስተካከላ እና ውድ ሕይወታቸውን ለአገራቸው እና ለወገናቸው ከሚዋደቁት ጎን ካልቆመ ታላቁ በይነ መረብ ከቁራ ጭሆት ያለፈ አይሆንም።
በሚኖሩብት ታላቅ የዲሞክራሲ አገር አሜሪካ ቀደም ሲል በበርካታ ከተሞችና በሰሞኑ ደግሞ ከ3100 ከተሞች በላይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እየተናጠች ውጤቱ ምን እንደሚሆን የአሜሪካ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም ግራ በተጋቡበት ወቅት የአገር ውስጥን የህልውና የትጥቅ ትግል ደግፎ ያለመውጣት ግራ አጋቢ ነው። ከወያኔ – ኦሆዴድ ተቀጣጥሎ የቀጠለውን ጎሳዊ አምባገነን መንግሥት በሰላማዊ እንቅስቃሴ እናስወግደዋለን የሚል ተስፋ በአገር ውስጥ ያለውን የትጥቅ ትግል ለማደብዘዝ እና በተዘዋዋሪ መልኩ ለአምባገነኑ መንግሥት ፋታ የሚሰጥ አደገኛ አካሄድ ነው። ሰላማዊ ትግልን ማንም አይጠላም። ሳይወድ ተገዶ ጦር ያነሳንና ለድል የቀረበ ድርጅትን በሰላማዊ ሕዝብ ትግል ማገዝ ወሳኝ የትግል ዘዴ ነው። በደፈናው ግን መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለን ትግል ማንሳት የተጠየፈ በደፈናው በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ስም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰን የሕዝብ የትጥቅ ትግል በምን መልኩ ልንረዳ ይገባል? የሚል አጀንዳ አለመቅረቡ በቅን ልቡና የቀረቡ ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ተናጋሪዎችን ሳይሆን የአዘጋጆችን ውስጣዊ ተልዕኮ እና ምንነት መመርመር የግድ ይላል። በፖለቲካ ትግል አንዱ ትልቅ ነቀርሳ ጥቂቶች ከራሳቸው ውጭ ሌላ ኃይል ለአመራር እንዲበቃ ያለመፈለግ ለእኔ ካልሆን ጭሬ ልበትነው እንደምትለዋ እንስሳ የሚያስቡ የሌላው ትግል ጎልቶ መውጣት የሚጎመዝዛቸው እንዲያም ብሎ በተቃዋሚ ስም ለመንግሥት የውስጥ ሠሪ ሆኖ መገኘት ነው።
በመፈክር ደረጃ ይሁን በንግግር ተደጋግሞ የተነሳው ጉዳይ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት የሚባለው አባባል ነው። ይህ ሁሉን አቀፍ አባባል በቀላሉ የሚታይ አይደልም። ሁሉን አቀፍ በመንግሥትነት ማቀፍ የሽግግር መንግሥትን አሰስ ገሰሱን ማለትም ከፋፋዩን፥ ጸረ -አንድነትን፡ ጸር- ዲሞክራሲን ማካተት ማለት አይደለም። ከሆነ ደግሞ የሽግግር መንግሥትን ወደባሰ ችግር መዳረግ ነው። ትግላችን ለሥልጣን ሳይሆን ለህልውናችን ነው የሚለው አባባልም አዘናጊ ነው። የሕዝብን ሀልውና ለማስጠበቅ የሚታገል ኃይል በቅድሚያ የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ ግድ ያላል። ቁም ነገሩ ሥልጣን እንዴት እና በምን ሁኔታ የሚለው ሲፈተሸ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት እዚህ ላይ ይነሳል። ታዲያ በተጠቀሰው አባባል የህልውና ትግል በማድረግ ለሥልጣን የሚገሰግስ ፋኖን ያነጣጠረ ከሆን ትክክል አይደለም።
ሌላው ክፍተት በስመ ሰላማዊ አቋምና በምርጫ ካልተሳተፍን ፈቃዳችን ይነጠቃል በሚል ተራ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ በትልቅ የቅስቀሳ እና የመልዕክት መድረክ መሆን በተገባ ነበር። በደፈናው ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግሥት መፈክርን ይዞ መውጣት በቂ አይደለም። ለምነ ፓርቲዎች መሳተፍ እንደሌለባቸው እና በአጭር ሆን በረጅም ጊዜ መዘዙ ምን ሊሆን እንድሚችል? አገራዊ ፋይዳው ምን እንደሚሆን የንግግሮች ትኩርት ቢሆን የተሻለ ነበር። መድረኩ ፋኖ ለወሰደው ትክክለኛ የአቋም መግለጫ በተጠናከረ ሁኔታ አጋዥ ሆኖ መቅረብ ነበረበት። ቢያንስ ለዚህም ጥሪ ፋኖ የወሰደውን አቋም ማስተጋባት በተገባ ነበር።
በአጠቃላይ አደራጀጀቱ ግልጽ ባይሆንም፥ ታላቁ የበይነ መረብ የተቃውሞ ትዕይነተ ሕዝብ በጎ ጎኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በተሻለ እና በተቀናጀ መልኮ ፍሪያማ እንዲሆን አንዳንድ አስኳል ነጥቦችን ማቅረቡ ይበጃል። በፐሮግራሙ ከተሳተፉት መካከል ዶ/ር እስማኤል በአንክሮ ያነሱት የትግል የፍኖተ ካርታ አስፈላጊነት ሊሰመርበት ይገባል። ከዚህ አኳያ ለሁሉም ቀጣይ የትግል እንቅስቃሴ የሕዝብን ሚና የማያኮስስ ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘብ እንዲሆን የሽግግር መንግሥትን ምንነትና አስፈላጊነት ማንሳት ያስፈልጋል።
የሽግግር መንግሥት ምንነት እና አስፈላጊነት
የሽግግር መንግሥት ጽንሰ ሀሳብ ለአገራችን አዲስ ነገር አይደለም። ሀገራችን በረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪኳ ውስጥ ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላ መንግሥት ከአንድ ሥርዓት ወደሌላው ሥርዓት ሲሸጋገር ሁሌም በተደላደለ ሁኔታ ነበረ ለማለት ከቶ አይቻልም። ለውጥ አነሰ በዛ ግጭ ግው አለው። በቀላሉ የተደላደለ መንግሥት መመሥረት አይቻልም። በማናቸውም ጊዜ በተቃዋሚነት አዲስ ወይም ተተኪ መንግሥት ሲቋቋም ይፋዊ የሽግግር መንግሥት ባይልም እንደየወቅቱ እና ሁኔታው የሕዝብን ተሳትፎ ያካተተ ወይም ያላካተተ የጊዜያዊ መንግሥት አደረጃጀት ባህሪይ መኖር የግድ ነው። ይሁንና በጉልህና በዘመናዊ አረዳድ ጥያቄው ጎልቶ የወጣው በሕዝባዊ አመጽ በወታደሩ መሪነት ዘውዳዊው መንግሥት ተገልብጦ ሥልጣኑ በወታደራዊ ደርግ ሙሉ ቁጥጥር በተደረገበት ጊዜ ነበር። የሥልጣን በትረ መንግሥቱን የጨበጠው ወታደራዊ ኃይል እራሱን ጊዜያዊ አስተዳደር አድርጎ ለቋሚ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም የተስፋ ጭረትን ለኩሶ ነበር።
በዚያን ወቅት በመጀመሪያ ደረጃ የሕዝባዊ መንግሥትን መመሥረት ዋንኛ ዓላማ አድርጎ ለሽግግር መንግሥት መመሥረት ግንባር ቀደም ትግል ያደረገው ኢሕአፓ ነበር። በሕዝባዊ መንግሥትነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በሚያራምደው የሕብረተሰባዊነት ፍልስፍና እና በሌሎች ምክንያቶች ተግዳሮቱ ቀጥሎ በቀዝቃዛው ጦርነት መወገድ ታጅቦ ሕውሐት የኢሕዲሪን መንግሥት አስወግዶ ሥልጣን ያዘ። ለሁለተኛ ጊዜ የሽግግር መንግሥት ተሽሞንሙና መጣች። ወያኔ በራሱ ስልት ያዋቀረውን አሕአዴግ ይፋ አድርጎ እና በፖለቲካዊ ስሌቱ የጎሳ ጥንቅሩን በድርጅቶችና በግለሰቦች አሰባስቦ የሽግግር ቻርተርን አውጥቶ ጊዜያዊ መሰል አስተዳደርን መሠረተ። ሕውሐት ከጊዜያዊነት ወደ ኢፌዲሪ መንግሥትነት ቢቀየርም የሕዝብን የቆየ የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄን ለመመለስ የቻለ ሁኖ አልተገኘም።
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አካል ካለመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ በነበረው እና በቀጠለው የጎሳዊ ሥርዓት ሕገ መንግሥት ላይ ተመሥርቶ ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያሳምርም የሚለውን ብሂል በራሱ የኢሕአዴግ አባላት የአመራር ለውጥ ተደረገ። ዋናው የመንግሥት መሪ ሕውሐት ከአሕአዴግ ራሱን በማግለሉ እና ያወጣውን ሕገ መንግሥት በመሻር ራሱን ከኢሕአዴግ አገለለ። በዚህም የተነሳ በይዘት ሆነ በቅርጽ ከኢሕአዴግ ያልተለየ ብልጽግና በአዲስ የድርጅት ስያሜ የመሪነት ሚናውን ወሰደ።
ብልጽግና የመሪነት ሚናውን ሲይዝ የሕዝብ ተስፋ የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓትን የሚያመጣ ለሕዝባዊ መንግሥት መደላደል አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ተስፋ በማድረግ ነበር። በመሆኑም፥ የሽግግር መንግሥት እንዲፈጠር የሕዝብ ጥያቄ ለሦስተኛ ጊዜ ጎልቶ መጣ። ብልጽግና የሽግግር መንግሥት መመሥረትን ከራሱ መርህ እና አቋም አንጻር የሕዝብን ጥያቄ ወደጎን አደረገ። የሕዝብን አጀንዳ አሽቀንጥሮ ጣለ። እነሆ አሁንም የሽግግር መንግሥት የሕዝብ ዋንኛ የፖለቲካ አንጀዳ ሆኖ ይገኛል። የበይነ ትንቢተ ሕዝብ የመልዕክት አስኳል የሽግግር መንግሥት ይመሥረት መሆኑ ተገቢ ነው።
የሽግግር መንግሥት ለምን?
ለመሆኑ የሽግግር መንግሥት ምንድን ነው? ለምንስ ያስፈልጋል የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱ ወደዚህ ጽሑፍ ዓላማ ጥሩ መንደርደሪያ ስለሆነ ወደዚሁ እናምራ። የሽግግር መንግሥት ወደቋሚና ዘላቂ ሕጋዊ እና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለማቋቋም ከአገራችን ተጨባጭ አኳያ የምርጫ ሂደቶችን ለማዘጋጀት፥ ከፋፋይ እና ጸረ-አንድነት የሆነን ጎሳዊ ሕገመንግሥት በሌላ ፍትሃዊ አገራዊ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅ ለማድረግ፥ ከሙስና የጸዱ ተቋማትን እንደገና መልሶ የማደራጀት ሥርኣዎችን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ጊዜያዊ ከፍተኛ የአስተዳደር አካል ነው። ለዚህም በሂደቱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፥ የሃይማኖት ተቋማትን፡ የአገር ሽማግሌዎችን፥ ግለሰቦችን በማሳተፍ አገራዊ ራዕይ የሚሰፍንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ግድ ይለዋል። በሂደቱ ከቂም በቀል አካሄድ የጸዳ፡ የማናቸውንም የቡድን በላይነት በማስቀረት የፖለቲካ ሥልጣን ድልድልን በመርህ ፥ በርትዕ እና በፍትሃዊነት መከወን ነው። ለዚህም የሽግግር መንግሥት የአስተዳደር ሕግና ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ነው።
የሽግግር መንግሥት አሳታፊነትን የያዘ ሁሉን አቀፍን በአግባቡ የተረዳ ሆኖ ለሽግግር መንግሥት ተሳትፎነት ቢያንስ የሚከተሉትን ሊይዝ ይገባል።
ለሽግግር መንግሥት ምሥረታ በድርጅት እና በግለሰብ ደርጃ ከሚያስፈልጉት መስፈርቶች መካካል –
- በሥልጣን ያለው መንግሥት በሕዝብ ቅቡልነት የሌለው መሆኑን እና መወገድ አስፈላጊነትን ያመነ
- በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን
- ለዘላቂ መንግሥት ምሥረታ ለተሻለ ሕገ መንግሥትና የሥርዓት መዋቅር ለውጥ የሚተጋ
- ከበቀልና ከቂም በቀልነት የነጻ
- ታማኝነትን ለግለሰብ ሳይሆን ለአገር እና ለሕዝብ ያደረገ
- ለአገር ሰላምና ደህንነት የሚቆም
- በተለዋዋጭ የአቋም መለዋወጥ አገሩንና ሕዝቡን ለአደጋ ያልጣለ ወይም በሕዝብ ላይ በአቋሙ በጥርጣሪ የማይታይ
- ከአገር ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ መስክ ከወንጅልና እና ሙስና የጸዳ
- ከጎሰኝነት የተላቀቀ
- በስውር ሆነ በገሃድ አገሩንና ሕዝቡን ያልጎዳ ወ.ዘ.ተ
በአጭሩና በጥቅሉ አንድ የሽግግር መንግሥት የተዋጣለት ወይም ስኬታማ የሚያሰኘው ከበርካታ መስፈርቶች መካከል እንደስሙ የጊዜ ገደብ ሲኖረው፥ አሳታፊነቱ በውል ሲረጋገጥ፥ ሰላምና ደህንነት ሲያረጋግጥ፥ እምነት የተጣለባቸውን አመራሮች እንደልምዳቸውና ክህሎታቸው አድርጎ መገኝት ሲችልና ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎች ተግባራዊ አድርጎ ሲገኝ ነው::
የግልጽነት አስፈላጊነት
ከዚህ መሠረታዊ ሀሳብ ተነስተን የአገራችንን የሽግግር ሂደት እንዴት ሊቃኝ ይገባዋል ? የሚለውን መዳሰስ ተገቢ ነው። የሽግግር መንግሥት አተገባበር በተለያዩ መንገዶች ሊሆኑ እንደሚችል ከአገራችን እና ከዓለም አቀፉ ልምድ ዋነኞችን ማንሳት ይቻላል።
እነዚህም፥-
- ሥልጣንን በሕዝባዊ የትጥቅ ትግል ወይም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ግልበጣ ወይም በሰላማዊ እንቅስቃሴ ድል ተቀዳጅቶ ቅቡልነትን ለማግኘት የማዘናጊያ ጊዚያዊ ስያሜን ለተወሰነ ጊዜ ይዞ ለአገዛዙ አስተማማኝ መስሎ ሲያገኘው ጊዜያዊነትን አፍርሶ እራሱን በቋምነት መቀየር፡
- ሥልጣን የያዘው ኃይል በገባው ቃል መሠረት ምርጫን አካሂዶ እራሱን ከምርጫ አውጥቶ ወይንም የምርጫው ተካፋይ አድርጎ ሥልጠንን የምርጫ ውጤት አድርጎ መገኘት፥
- የመንግሥት አስተዳደሩን ደካማነትና የሕዝብ ቅቡልነት አምኖ ለምርጫ እራሱን በማግለል ወይም አብሮ በመሳተፍ የምርጫን ውጤት የሚቀበል መንግሥት ሆኖ ሲገኝ እና
- በምንም አይነት ሥልጣኔን አለቅም ሲል በሕዝብ ሰላማዊ ወይም የትጥቅ ትግል ወይም በመፈንቅለ መንግሥት ሲወድቅ ነው።
ከላይ የቀረቡት ተመክሮዎች የሚያረጋግጡልን ለሽግግር መንግሥት ምሥርታ ተወደደም ተጠላም አንድ የተደራጀ ኃይል መኖር የግድ ነው። በዘፈቀደና ባልተመረጠ ወይንም ለአገሩና ለሕዝቡ የቆመ የፖለቲካ ድርጅት በሌለበት ሁኔታ የሽግግር መንግሥት መመሥረት አይቻልም። ከዚህ መለስ የሚጠበቀው የጥቂት ቆራጥ ወገኖች የመንግሥት ግልበጣን አካሂደው የሽግግር መንግሥትን በአፋጣኝ መፈጠር መመኘት ነው። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ቅቡልነትን የሚያሳጣ ፈታኝ እና አደገኛ መሆኑ ግልጽ ነው።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመና በፖለቲካዊ ሆነ በኃይል አደረጃጀቱ ለኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት በእጃችን ያለው ተጨባጭ ዋስትናችን ፋኖ መሆኑን በሚገባ መቀበል ከጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ አይሆንም። በዚህ ላይ ግልጽ አቋም ሳይያዝ ያለውን ዕድል መጠቀም ትተን በሰላማዊ የበይነ መርብ ትዕይንት ሕዝብ አጀንዳ ሕዝብን ማደናገር ተገቢ አይደለም።
ከአገር ውጭ ያሉ ኃይላት ሊያድርጉ የሚገባቸው ትግል እንዴት እና በምን ሁኔታ ፋኖ ድልን ይቀዳጅ? በምን መልኩ እንርዳ? ፋኖስ የጎሰኛ መንግሥትን ለማፈራረስ እንዴት እና በምን ሁኔታ የሽግግር መንግሥትን ማቋቋም ይኖርበታል? ፋኖ የውጭ መንግሥታትን ድጋፍ እንዲያገኝ ምን መደረግ ይኖርበታል? በሚሉትና በመሳሰሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ሊተኮር ይገባል። ለመስዋዕትነት ዋጋ መክፈልና አገርን ማዳን ከዚህ ይጀምራል።
የፋኖ እንቅስቃሴ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት በአገር ውስጥ እና በውጭው ዓለም በተለያየ ፈርጅ የሚገኙ አንዳንድ የተለያዩ ፖለቲከኞች፡ አንቂዎች፥ ጋዜጠኞችና ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማውቅ፡ ሆን ተብሎም ሆነ አልሆነ ለረጅም ጊዜ የፋኖን እንቅስቃሴ የሚያደበዝዝ የሰላም ትግል ብቻ እና ብቻ እያሉ ሲያናፍሱ መቆየታቸው እና እያናፈሱም እንደሆነ ይታወቃል። የአገርን እና የወገንን ክቡር ዓላማ ያነገበ ንጹህ አይምሮ ያለው ሰው ወይም ድርጅት የግድ ካልሆነ በስተቀር ራሱን ሆነ አብሮ የሚሰለፉትን ለመስዋዕትነት የሚጋብዝ የለም። ይሁንና ፋኖ የምሬት የጭቆና የቁጭት ውልድ መሆኑ እየታወቀ ዓላማውንና መስዋዕትነቱን ለማጠልሸት በሰላማዊ ትግል ስም ብዙ ተደክሟል። እየተደከመም ነው። “ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚለውን መጽሐፍ ያስታውሰኛል።
ያም ሆኖ፥ የፋኖ እንቅስቃሴ እየጎለበተና የአንድነት ፖለቲካዊ ትስስሩ አየተጠናከረ ሲመጣ፥ ፋኖ ለህልውናው ትግል ማድረጉን ዕውቅና እንሰጣለን በማለት ሸብረክ ተደርጎ አሁንም በሰላማዊ ትግል እንጂ በጦርነት አናምንም ህሳቤ የፋኖን ትግል ለማሳነስ ሙከራው አልቀረም። እንዲያም ሆኖ፥ አሁን የመንግሥት ለውጥ አይቀሬ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የታመነበት ደረጃ ላይ በመደረሱ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ አድማሱ እየሰፋ መጥቷል። ፖለቲከኞች፥ ምሁራንና የሰላም አቀንቃኞች ለሕዝብ መብት መጠበቅ የሚታገሉ በአጀንዳነት ይዘው እየተወያዩበት ነው። ይህም እሰየ የሚያሰኝ ሲሆን፥ በአገር ውስጥ ግን ይህን አጀንዳ ማንሳት ፈጽሞ አለመቻሉ አሳዛኝ ነው። ሆኖም፥ የትጥቅ ትግል አድራጊዎች ይህን አጀንዳ ለቆሙለት የሕዝብ ልዕልና የሰላማዊ ትግልን ከአፎሙዙ እንዳለዩት ይታመናል። ፋኖ ከትግሉ መፋፋም ጀምሮ “መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵ”ያ ሲል የሽግግር መንግሥትን ምሥረታ ለአንድ አፍታ የሚረሳ እንዳልሆነ እሙን ነው።
ይሁንና አሁንም የሽግግር መንግሥት ምሥረታን በተመለከተ የሚነገሩት የውይይት ሀሳቦች ድፍረትን ያልተላበሱ፡ እውነታን ለመሸፈን የሚሞክሩ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለአገራችን ችግር መፍትሄ አቅጣጫ ሰጭነት ግልጽነት ይጎላል። ድፍረት ማጣት ከእውነት መሸሽ ጋር የተቆራኘ ነው። መተኪያ የሌለውን ውድ ህይወታቸውን በመስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን ዕውቅና ያለመስጠት ችግር ይንጸባረቃሉ። በሰላማዊ ትግል አባባል እዚህ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰን ትግል ለማደብዘዝ ጥረቶች አሉ። አሰናካይ ቀልብ ሰራቂ ሀሳቦች በማይሆን እርባና ቢስ ዘዴዎች እየፈተለኩ ይገኛሉ።
በሌላ መልኩ በበርካታ ገንቢ ውይይቶች የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት አሌ የማይባል ሀቅነት እየቀረበ ነው። ከመርህ አንጻር የሚነሱ ባሕሪያትም አከራካሪ አይደሉም። የጎደለው ሀቅን አውጥቶ መነጋገሩ ላይ ነው። አንድ የሽግግር መንግሥት እውን የሚሆነው ባለው መንግሥት አስገዳጅ ፈቃደኝነት ላይ ሲመሠረት ወይንም ያለውን መንግሥት በኃይል ለመገርሰስ በተዘጋጀ እና በሕዝብ ቅቡልነት ባለው ታጋይ ኃይል ነው። በምንም ሁኔታ ካለመሪ ድርጅት የሽግግር መንግሥት ሊከናወን አይችልም። ከዚህ አኳያ የሽግግር መንግሥትን አስፈላጊነት እና ተግባራዊነት ለዚህ ዓላማ መሳካት ኃላፊነት ሊወስድ የተቃረበን ነቅሶ ማውጣት ተገቢ ነው። በመሆኑም፥ንግግራችን፥ ውይይታችን በአዙሪሽ እና በአግድሞሽ ሳይሆን በቀጥታና በግልጽነት ለሥልጣን የተቃረበውን የፋኖ ድርጅት በማንሳት ሊሆን ይገባል።
ፋኖን ለዚህ ተልዕኮ ማዘጋጀት ድርጅቱን በሥነ ልቡና ማዘጋጀት እና የትግሉ አካል መሆን ነው። ይህን በከፍተኛ መስዋዕትነት እዚህ ደረጃ የደረሰን ዕውቅና መስጠት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሂደትን ጅማሮ ማሳመር ነው። ቀጣዩ እና የውይይቱ እምብርት ለሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ያበቃል ተብሎ የታመነ የፋኖ ድርጅት ሊያራምደው የሚገባን መርህ እና ለሽግግሩ በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ሊይዘው የሚገባን ስልታዊ ዘዴን በማቅረብ፡ አገሪቱን በሕጋዊነት ፥ በፍትህ እና በአንድነት ለማጠናከር ሊወስድ የሚገባቸውን እርምጃዎች አደራውንና ኃላፊነትን በአንክሮ በማቅረብ ቢሆን ይመረጣል። ይህ በማይሆንበት ሁኔታ የትግሉ አካል ሳይኮን አሁንም ፋኖ ሳይወድ በግዴታ የገባበትን የትጥቅ ትግል በሰላማዊ ትግል ሰበብ ለፍሬ የደረሰን ኃይል ድምጽ በሌለው ፈንጅ ለማጨናገፍ መሞከር የኢትዮጵያ የሽክርክሮሽ ችግርን እንዲያፋጥን ማገዝ ነው።
በአጭሩ የሽግግር መንግሥት መፈጠርን የሚሹ ኃይላት በተናጠል ሆነ በቡድን የሚያደርጉት ውይይት እና የሰላም ትግል አራማጆች የፋኖን አገራዊ ፋይዳ በመደገፍ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። ይህም ትግሉን ማፋጠን ኢትዮጵያን ከችግር አዙሪት ማውጣት እና የሕዝቧን አንድነት፡ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን ማበልጸግ ነው። ይህ ከሆነ የትግሉ ግስጋሲ ፍጥነት ይጨምራል። የሕዝቡ ተስፋ ይለመልማል። ውጤቱም የተፋጠነ ይሆናል። ስለዚህ፥ ጥላቻን አስወግዶ ጥርጣሬን እና አሉባልታን አስወግዶ የትግሉ አካል መሆን ከአንድ ኢትዮጵያዊ ራይ ካለው ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
ይችን ጽሑፍ ለማጠቃለል ለሽግግር መንግሥት መመሥረት መዘንጋት ከሌለባቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉትን ለማንሳት እወዳለሁ።
- ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ እየጠነከረ ያለው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ትግል ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
- የመንግሥት ሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ፋኖን የሚያግዝ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በቅድሚያ ጥራት ያለው የፖለቲካ አደረጃጀት ለፈጠር ይገባል።
- በጋራ ጠላት ላይ የተሰለፉ ኃይላት ልዩነታቸውን አጥበው በወሳኝ አገራዊ የፖለቲካ አቋም ላይ ተነጋግርው መግባባት ላይ እንዲደርሱ ጥረት ማድረግ፥
- ጸረ-አንድነት ኃይላትን በተናጠልና በጋራ መፋለም፥
- ለሽግግር መንግሥት መቋቋም እንቅፋት የሆኑትን ኃይላት መታገል፥
- የተቀናጀና የሰመረ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ማድረግ እና
- የሽግግር መንግሥት አመሠራረትን በተመለከተ ገንቢ ሀሳቦችን – ፍኖተ ካርታ ባማዘጋጀት ለሽግግር መንግሥት ምሥረታ ብቁ ለሆነው እና ዕውቅና ለሚሰጠው ኃይል በግልጽነት ለፋኖ ማቅረብ።
ቸር ይግጠመን። እግዚአብሔር አገራችንን ከመዓቱ ያውጣት።
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
