
ከ 1 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
ጄነራል ታደሰ ወረደ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ አቅንተው ለፌደራል መንግሥቱ ሪፖርት ከማቅረባቸው እና ሥልጣናቸው ከተራዘመ በኋላ ህወሓት “ሥልጣን እንዳትቀበል” ብሏቸው እንደነበር ተናገሩ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ይህንን ያሉት ማክሰኞ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ይህንን የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎ እስካሁን ድረስ ህወሓት ምንም ያለው ነገር የለም።
ጄኔራል ታደሰ ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሥልጣን ዘመናቸው ለአንድ ዓመት ከተራዘመላቸው በኋላ መግለጫ የሰጡት ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ሚያዚያ 6 2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት በጠቅላይ ሚኒሰተር ዐቢይ ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ህወሓት ስለተቃወመው የሥልጣን ዘመናቸው በሰጡት አስተያየት “ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ” የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ በመጥቀስ ለድርጅቱ አመራሮች ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን እና ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ጄነራል ታደሰ ወረደ ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ የፕሪቶሪያ ውል ፈራሚ ከሆነው ህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር “በመመካካርና በመስማማት ነው” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት መራዘሙ ይፋ ከተደረገ በኋላ ህወሓት “የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ” ውሳኔ ነው በሚል ተቃውሞታል።
ህወሓት የጄነራል ታደሰ የሥልጣን መራዘምን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ማራዘም የሁለትዮሽ የፖለቲካ ውይይት ሳይደረግ እና የህወሓት እውቅና እና ተሳትፎ ሳይኖር የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የሰጠው ውሳኔ” መሆኑን ገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻ ወደ አዲስ አበባ ከመጠራታቸው በፊት በህወሓት የቀረበ ማንም ተተኪ ሰው ወይም ሀሳብ እንዳልነበር ተናግረዋል። አዲስ አበባ ተጉዘው ሥልጣናቸው እንደተራዘመ ከተሰማ በኋላ ግን ህወሓት የሥልጣኑን መራዘም እንደማይቀበል እና ጄነራል ታደሰ ወረደም ኃላፊነቱን እንዳይቀበሉ እንደነገሯቸው ገልፀዋል።
“ሥልጣን ግን እንዳትቀበል” መባላቸውን የተናገሩት ጊዜያዊ አስተዳዳሪው፤ ይህ “ተቀባይነት እንደሌለው” ተናግረዋል።
” ‘ሥልጣን አልፈልግም፤ እምቢ’ ማለት መብት ነው፤ ነገር ግን አንተም ‘እምቢ በል ሥልጣን እንዳትቀበል’ ብሎ ማለት ልክ አይደለም፤ እኔም ይህንን ሃሳብ አልቀበለውም” ሲሉ ጄነራል ታደሰ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
“በመወራጨትና በመዝለፍ የሚፈጠር ነገር የለም” ያሉት ፕሬዚዳንት ታደሰ ከቀያቻው የተፈናቀሉትን ለመመለስና የትግራይን ክልል ሕገ መንግሥታዊ ግዛት ለማስከበር ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ “የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መመለስ እና የትግራይ ክልልን ግዛት አንድነት ማስጠበቅ ከመፈክር ያለፈ መሆን አለበት” ብለዋል።
ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በአዲስ አበባ ለፌደራል መንግሥት ያቀረቡት ሪፖርት የክልሉ መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈጻጸምን መሠረት ያደረገ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ የፌዴራል መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘ ያወጧቸወን ዘገባዎች በሚመለከት ሲናገሩም፤ “እውነታዎቹ ሊታፈኑ አይችሉም እና በሪፖርቱ ውስጥ የቀረቡት ምስሎች የቅርብ ጊዜ ናቸው” ብለዋል፣ ነገር ግን የቀረቡ ችግሮቹን ሪፖርት አለመደረጋቸው የሚዲያዎቹ ክፍተት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጄነራል ታደሰ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በነበራቸው ውይይት እና ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስና የትግራይ ክልልን ግዛት እንዲከበር ማድረግ፣ በጦርነት የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ በትምህርትና ጤና ዘርፍ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ የበጀት መቋረጥን ተከትሎ የተከሰተው የመድኃኒት እጥረት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ በክልሉ ውስጥ ያለውን የበጀት፣ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና በሌሎች መሠረታዊ እቃዎች ላይ ያለው እጥረት ሲያብራሩም “ትግራይ እጇን እና እግሯን አጣጥፋ አልተቀመጠችም” በማለት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥቱ በጀት ስላልተላከለት ላለፉት ወራት ለሠራተኞ ደሞዝ መክፈል አለመቻላቸውን ሲናገሩ ነበር።
ፕሬዝዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ ፌደራል መንግሥቱ ለትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ፣ ለመንገድ ግንባታ፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለሌሎች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚውል የተወሠነ በጀት መላኩን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ የክልሉን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በተመለከተ ግን ቀጣይነት ያለው ውይይት ያስፈልገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የጄነራል ታደሰ ለፌዴራል ካቢኔ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ላይ በመመስረት፣ የሚዲያ ዘገባዎች ሰፊ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች፣ የመልሶ ግንባታ እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ስኬታማ ዓመት እንደነበር ገልጸውታል።
ጊዜያዊ አስተዳዳሪው በመግለጫቸው “በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አለመጥቀሳቸው የሚዲያዎች ክፍተት ነው” ብለዋል፣ ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃኑ በእርሳቸው ሪፖርት ላይ ተመስርተው ያቀረቡት ዘገባ ስህተት ነው በማለት አላስተባበሉም።
በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ተፈናቃዮች ወደ ቀያቻው የመመለስ ጉዳይ እና የትግራይ የግዛት አንድነት ማረጋገጥ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አሁንም የማያግባቡ ነጥቦች ሆነው ቀጥለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መስራታቸውን ጠንክረው እንደሚቀጥሉ እና በምንም መልኩ ወደ ጦርነት ላለመምራት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።
