

ክፍል አራት
ኢትዮጵያን ልንታደጋት የምንችለው አንድ ስንሆን ብቻ ነው። አንድ ለመሆን ራሳችንን ከከፋፋዩ የዘርና የብሄር ፖለቲካ ማጽዳት አለብን። የዐብይ አሀመድ አምባገነንት፤ የብሄር ጽንፈኛነት፤ እ-ፍትሃዊነት እና ጎሳዊነትና ኢትዮጵያዊነት አብረው እንደማይጓዙ ማመን አለብን። ማመን በቂ አይደለም። መተግበር አለብን።
እነዚህ እሴቶችና ባህሎች ሁከት ፈጣሪ፤ ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለልማት ማነቆ መሆናቸውን ባለፉት አምሳ አመታት አይተናል። ይህንን አገር አፍራሽ ሁኔታ የዐብይ አህመድ አሊ ፓርቲና መንግሥት አባብሰውታል። አገር ሲፈርስ የሞራል ልእልናም አብሮ ይናዳል።
እኔን የሚያሰጋኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ የወጣቱ ትውልድ የሞራል ልእልና ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ መዝቀጡ ነው። ይህ ሁኔታ የሚያንጸባርቀው የኢትዮጵያን ባለሥልጣናት ራስ ወዳድነት የበከለው የሞራል ውድቀት ነው ብል አልሳሳትም። ለሰብእነት እና ለአገር ዘላቂ ጥቅም የሚያስብ አመራር የለም። ሃሰት መናገር፤ መዋሸት፤ መካድ፤ ማገት፤ የዘር ጥላቻ፤ ሌብነት፤ ሙሰኛነት፤ አጭበርባሪነት የተለመደ ሆኗል።

ሰላምና እርጋታ ብርቅ በሆኑባት ኢትዮጵያ ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉድ የሚል መንግሥትን ምን ይሉታል? የማንን ሥልጣን ለማራዘም? ማን በልቶ እንዲያድር? ማን እንዲራብ? ማን እንዲሰደድ?
የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት መርህ “እኛና እነሱ” የሚል የጎሳ መለያ ነው። ወጣቱ ትውልድ ብልሽልጩን ነገር እንደ ተአምራዊ ስኬት አድርጎ ያወራዋል፤ ይቀበለዋል። ዐብይ አህመድ በመላው ዓለም ያሰማራውና የሚከፍለው የሳይበር ሜድያ ጦር ሰራዊት ውሸቱን እንደ እውነት እንዲሰብና እንዲያስራጭ አድርጎታል። ገዝቶታል፤’ አሳምኖታል።
በዚህ ግዙፍ ሰራዊት የማይናገር ሃቅ ግን ሊካድ አይችልም። ምርጫ ተካሂዶ ዐብይ ሲያሸንፍም ሁኔታው ይባባል እንጅ አይሻሻልም። ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ አሁንም የሚኖረው በጭቃ፤ በጠለላ ቤት መሆኑን ረስቶታል።
ስር የሰደደው ድህነትና የብልጭልጭ ልማት (The façade of glitz as development) ማህበረሰባዊ ቀውሱን አይሸፍኑትም።
– Advertisement –

በመንገዶች ዙሪያ የኤሌክትሪክ መብራት ስለተከለ የብልጽግና መንግሥት በልማት ስኬተኛ ነኝ ብሎ ሲፎክር፤ ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል ምን አድርገህ? ብለን ብንጠይቅ መልስ የለም። ስኬት ተብሎ ሊነገር የሚችለው የአማራውን ሕዝብ ስላመከነውና ኢትዮጵያን ኦሮማይዝ (ኦሮምያዊ) ስላደርግናት ነው ቢባል አይገርመኝም። በቅርቡ አዲስ አበባ ፊንፊኔ ተብላ ብትጠራ አልገረምም። ከዚያ ቀጥሎ ምርጫውንን የኦህዴድ ብልጽግና ካሸነፈ የኢትዮጵያን ስም ወደ ኦሮሞያ ቢቀይረው አልገረምም።
ሁለቱም ክስተቶች ሰፊውን የኦሮሞን ሕዝብ ይወክላሉ የሚል እምነት የለኝም። ስጋቴ ግን ኢትዮጵያን ያፈርሳታል። ትግራይ ነጻ ሃገር የመሆን እዷሏ ከፍ ይላል። የሶማሌ ክልል ራሱን ከኢትዮጵያ ቢያስወጣስ? አማራው የራሱን ሃገረ መንግሥት ሊመሰርት ይችል ይሆን? አስቡት። የወደፊቱ ብሩህ ገጽታ አያሳይም።
ገና በመጠናከርና ከአማራው ክልል ወጥቶ ወደ ሌላው ክፍል ለመጓዝ ብዙ ተራራዎችን ማለፍ ያለበት የአማራ ፋኖ ብሂራዊ ንቅናቄ በመሬት ላይ ተቋሙን ለማጠናከር ጊዜ የሚወስድበት መሆኑን ብገነዘብም ቅሉ፤ የሃገረ መንግሥት ግንባታ አቋሙና የፖለትካ ፕሮግራሙ ከኦህዴድ ብልጽግና ተጻራሪ ነው። የተለየ የሚያደርገው ሁሉን አቀፍና ለፍትህ የቆመ ስለሆነ ነው።
ኦህዴድ ብልጽግና የጎሳ ድርጅት ስለሆነ የሚመሰርተው መንግሥት የአንድ ጎሳን የበላይነት የሚያንጸባርቅ መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ለሰላምና እርጋታ ዋና መሰናክል እንደሚሆን አልጠጣጠርም። ድህነት እንደሚባባስም አልጠጣጠርም። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ለመኖር ወደማይችሉበት ደረጃ እንድሚሸጋገሩም አልጠጣጠርም።
ምርጫው ቢካሄድ ችግሩን አጉልቶ ያወጣዋል እንጅ መሰረታዊ የሆነትን ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮች ሊፈታቸው አይችልም። ብልጽግና የፋይናንስ ሙሰኛ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሙሰኛም ነው። አሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው እንዲሉ፤ ስርዓቱ የገማው ከላይ ጀምሮ ነው። አማራጭ የሚያስፈልግበትም መሰረታዊ ምክንያት ራሱን ለማደስ ስለማይችል ነው።
እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ፤ አፋብን የሚታገለው ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለሰላም፤ ለርጋታ፤ ለብሄራዊ ጥቅም፤ ለዲሞክራሲ ስለሆነ፤ ይህ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ አማራጭ ኃይል ነው እላለሁ፡፡ አማራጭነቱ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ግን ከሌሎች ተመሳሳይ አላማ ካላቸው ባለድርሻዎች ጋር ሲተባበር ነው።
በተመሳሳይ፤ አማራ ያልሆኑ ለመሰረታዊ ለውጥ የተዘጋጁ አካላት ከአፋብን ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ጥሪ አደርጋለህ። ኢትዮጵያን ከመፈራረስ የምንታደጋት ባንድ ላይ ስንቆም ነው። የዝግ ችሎት የሚያካሂደው የኦህዴድ ብልጽግና ፓርቲና መንግሥት የፖለቲካና የማህበራዊ ምህዳሩን ሙሉ በሙሉ ዘግቶታል። ይህ መፈናፈኛ የሌለበት ሁኔታ (Suffocating political, social and spiritual environment) የሚያሳየው የፖለቲካ ውድድር የማይቻል መሆኑን ነው፡:
ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ አማራጭ ለማቅረብ ደግሞ የምንጋራቸው እሴቶች መኖር አለባቸው፤ ለምሳሌ፤ ሰብአዊነት፤ የዜግነት መብት፤ ኢትዮጵያዊያነት።
የምንጋራው ብሄራዊ እሴት ኢትዮጵያዊነት (National identity) ነው። በጎሳ ልዩነቶች ላይ እኮ የከፈልነው የኢኮኖሚ፤ የማህበረሰባዊ ካፒታል፤ የመንፈስ ስነ ልቦና መናጋት ዋጋ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። በዓለም ደረጃ ዝቅ አድርጎናል። ዝቅ ያደረገንን ፓርቲ መልሰን እንምረጥ ብንል የሚከፈለው ዋጋ ካለፈው የባሰ እንደሚሆን አትጠራጠሩ።
የሉሲ አገር ሆነን እንዴት ጎሰኞችን እንመርጣለን? የአፍሪካ አንድነት መዲና ሆነን እንዴት ጎሰኛነትን እንመርጣለን? የአድዋን ልምድ፤ ባህልና ተምሳሌትነት ተረክበን እንዴት ጎሰኞች እንዲገዙንና እንዲያፈርሱን እንፈቅዳለን?
አፋብን ከኦህዴድ ብልጽግና በምን ይለያል?
ገና ብዙ ድክመቶች ያሉበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ አፋብን አማራጭ የሚሆንበት መሰረታዊ ምክንያት ከብሄር ነጻ አውጭ ግንባሮች የተለየ ብሄራዊ ግብ ስላለው ነው። ኢትዮጵያን ያፈቅራል፤ የሁሉን ዜጎች መብት ያከብራል። ግቡ ፍትህ፤ የሁሉም ዜጎች እኩልነት፤ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ መሆኑ፤ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ሕዝቡ መሆኑ፤ ኢትዮጵያ ከሁሉም የጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም፤ በመከባበር፤ በመልካም ጉርብትና ለመኖር የምትፈልግ አገር መሆኗን የሚያስተጋባ መሆኑ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ከሚያክበሩ ከመላው የዓለም መንግሥታት ጋር መልካም ግንኙነት የመመስረት ታሪክ ያላት አገር መሆኗን የምትጠብቅ መሆኗን የሚያስተጋባ መሆኑ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት የማያሻማ አቋም እንዳላት እና የአፍሪካ መዲና መሆኗን ለመቀጠል እንደምተፈልግ የሚያንጸባርቅ አቋም የያዘ መሆኑ ጠንካራ ጎኑ ናቸው።
ደካማ ጎኖቹ ብዙ ናቸው። አፋብን አሁንም በጎጥ ልዩነቶች የተበከለ መሆኑ፤ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ገና ጥራት ባለው መልክ አለመቅረቡ፤ ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች የአስተዳደር መዋቅር ሰርቶ ነዋሪው ህዝብ የለውጡ ባለቤት እንዲሆን አለማድረጉ፤ ውህደት ከመሰረተ በኋላ ውህደቱን የሚያንጸባርቅ የጋራ ትግል ለማድረግ መቸገሩ (ጎንደር ምሳሌ ነው)፤ ከአማራው ክልል ውጭ ለመንቀሳቀስ አለመቻሉ፤ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ትብብር አለመፍጠሩ፤ ግዙፉን ወጣት ትውልድ የትግሉ ተሳታፊ በማድረግ የህዝብ እምቢተኛነት ለማዋቀር አለማቻሉ ወዘተ።
ሮም ባንድ ቀን አልተሰራችም እንዲሉ፤ እንቅስቃሴው ባንድ ሌሊት ድል ሊቀዳጅ እንደማይችል አውቃለሁ። ግን ጥራት ያለው መስመር ያስፈልገዋል። ከተሞችን ከመያዙ በፊት ዝግጅት ያስፈልገዋል። ሕዝቡ የሚቀበለው የሚያየውን እንጅ ላም አለኝ በሰማይን አይደለም።
የህዝብ ትግል ሕዝብን ያማከለ መሆን አለበት።
የአማራ ፋኖ ጦርነት መሰረቱ በአማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ መንግሥት መር የሆነ እልቂት፤ እንግልት፤ እስራት፤ ረሃብተኛነት፤ መፈናቀልና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ስለተካተካሄዱበትና አሁንም ስለሚካሄዱበት ነው።
በጦርነት በኩል ለድል የሚያበቁት ግብዓቶች የቁሳቁስና ሎጅስቲክስ አቅም እና በመሬት ላይ የሚታየው ውጤት መሆኑን ልዩ ልዩ ጥናቶችና ምርምሮች ይናገራሉ። ለሕዝቡ ያለው አለኝታ የሚታየው ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች በሚሰራቸው ተግባሮች ላይ ነው። በተጨማሪ፤ በአካባቢው በሚታየው የኃይል አሰላለፍ ሁኔታ ነው፤ ለምሳሌ የውጭ መንግሥታት እውቅና መኖሩ። ከጎረቤት አገሮች ጋር የውስጥ ውይይት የማድረግ ሃላፊነት አለበት። በታዛዢነት ሳይሆን በራስ እና በአገር ጥቅም ላይ በማተኮር። አፋብን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንደሚያስከብር አልጠጣጠርም። ቀይ መስመሮቹን ግን በተደጋጋሚ ግልጽ ማድረግ አለበት። ቀይ መስመሩ ከከሃዲው ኦህዴድ ብልጽግና ፓርቲና መንግሥት ይለየዋል። ለምሳሌ የአዲስ አበባን የወደፊት እጣ ፋንታ በሚመለከት፤ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያን ጉዳይ በሚመለከት፤ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ወዘተ።
በዚህ ትንታኔ ላይ ለአፋን የበላይ መሪዎች ለመጠቆም የምፈልገው የአማራ ፋኖ በሕዝብ በኩል ያለው ተቀባይነት (ቅቡልነት/Legitimacy) ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው። ሕዝቡ አፋብን ሲያሸንፍ ህየወቴ፤ ኑሮየ ይሻሻላል ብሎ ካመነበት የሚከፈለውን መስዋእት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስመስክሯል;
ስለሆነም፤ የአፋብን አመራር ስንት ሰራዊት እንደ ገደለ ከመናገር ይልቅ፤ ስንት የዐብይ አህመድ አሊ ሰራዊት እንደማረከና ስንት ስራዊት የዐብይን አመራር ንቆት ወደ አፋብን እንደተቀላቅለ ቢነገር የተሻለ ይሆናል። ይህ መረጃ የኦህዴድ ብልጽግና ሰራዊት የሚፈርስ አረመኔ መሆኑን ያሳያል። ሕዝቡን ይስባል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደው መንግሥት መር ጦርነት ባህሪዎች ምን ይመስላሉ? ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። የሕዝብ ጦርነቶች ታሪክ ሶስት ክስተቶችን ያስተምረናል፤ እነዚህም፤
አንድ፤ ተፋላሚው ኃይል፤ ለምሳሌ ፋኖ የጠላትን ምሽግ እያመከነ አቅሙን የሚያጠናክርበት ሁኔታ እንደሚፈጥር። የአማራ ፋኖ ይህንን በሚገባ አስመስክሯል። የታጠቀው መሳሪያ ሁሉ የማረከው ነው፤ የማረከው ደግሞ ከዐብይ ሰራዊት ነው።
ሁለት፤ ተፋላሚው ኃይል የጠላትን ደካማና ጠንካራ ጎን እየገመገመና እየለየ በጠላቱ ላይ ብዢታዎችን ፈጥሮ የጠላቱ ኃይል ቅቡልነቱን እንዲያጣ ያደርጋል። የጠንካራ ጎኑን ለይቶ በማጤን ራስን ከጥቃት መከላከል። ለምሳሌ በድሮን የሚደረገውን ጥቃት በሚመለከት ህዝቡ ለአደጋ እንዳይጋለጥ በድሮን ከመጨፍጨፉ በፊት መረጃ እንዲያገኝ መደረግ አለበት (Early warning system).
ሶስት፤ በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ህዝቡ የትግሉ አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ሁልጊዚ ማስተጋባት። ለምሳሌ፤ የኦህዴድ ብልጽግና የኦሮሞውን ሕዝብ የማይወክል መሆኑንና የአማራ ፋኖ ከሕዝቡ ጋር ምንም አይነት ቅራኔ እንደሌለው ማስተጋባት፤ ማሳመን።
ክሁሉም ቁልፉ የመጨረሻው ነው። ሕዝቡና ባለሥልጣናቱ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ እና ሕዝቡ በመንግሥት የማስተዳደር አቅም ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረግ ይገኙበታል። በፕሮፓጋንዳ በኩል ኦህዴድ ብልጽግና ለራሱ ሥልጣንና ዝና በማሰብ በየቀኑ ልጆችህን እያስገደላቸው ነው፤ ወንድም ወንድሙን እንዲገድል መፍቀድ የለባችሁም የሚል በተደጋጋሚ ቢነገር ይጥቅማል። ይህንን የሚያደርግ ጨካኝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ብቃት የለውም። የራስህን ኃብትና ንብረት እየተጠቀመ የጦር መሳሪያም ቢኖረውም እንኳን፤ የሕዝብ ቅቡልነት የሌለው መንግሥት እድሜ አጭር እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ። ሕዝቡ ወሳኝ ነው። ይህንን ዘዴ ሳይሰለቹ ማስተጋባት ወሳኝ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ አገር ወዳድ፤ ተቆርቋሪና ሃላፊነት የሚሰማው ኃይል ያስፈልጋታል።
ሕዝቡ በአማራ ፋኖ ላይ እምነት እንዲኖረው አመራሩ ተግቶ በቅንነት መስራት አለበት። ቅቡልነት እንዲሰፍንና አገር አቀፍ እምቢተኛነት እንዲቀስቀስ ከተፈለገ አፋብን ብቻውን ሊስራ አይችልም። አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። አገር አቀፍ እንዲሆን ደግሞ ከሌሎች አጋር ኃይሎች ጋር ስልታዊ ቁርኝት (Strategic alliance)መፍጠር ወሳኝ ነው፤ ለምሳሌ ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ሰራዊት አመራር ጋር። ከወጣቱ ትውልድ ጋር። ከሴቶች ጋር። ከአስተማሪዎች ጋር። ከባለሞያዎች ጋር፤ ከዲያስፖራው ጋር፤ ከእምነት አባቶችና ተከታዮች ጋር፤ ውስጥ ለውስጥ ዐብይ ካልተዋጠላቸውና አደጋውን ከተገነዘቡ የብልጽግና መንግሥት ሃላፊዎች ጋር። ወዳጅ ማፍራትና ማብዛት ወሳኝ ሂደት ነው፤ ብልህነት ነው።
ቁም ነገሩ በመሬት ላይ የሚደረገው ጦርነት ብቻውን ወይንም በተናጥል ወደ ድል አያሸጋግርም። ዋናው ትኩረት ሕዝቡ በኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ የተማረረ መሆኑን እና በገዢው ፓርቲና መንግሥት እምነት የሌለው መሆኑን ሳይሰለቹ ማስተጋባት ነው። ይህ የሚጠይቀው የአመለካከት ለውጥ ነው። ህዝቡ በአማራ ፋኖና አጋሮቹ ላይ እምነት ኖሮት እንዳማራጭ ኃይል እንዲቀበላቸው ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ሕዝቡ ተስፋ ብቻ ሳይሆን አማራጭ ኃይል የተዘጋጀ መሆኑን ለማስተናገድ ወደሚችልበት ደረጃ እንሸጋገራለን። ዐብይ ቢወገድ ክፍተት ይከሰታል የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ዐብይን የፈጠረው እኮ ኢህአዴግ ነው። ማንም ሰምቶት የማያውቀውን ተራ ወታደር ክፍ ያደረግነው እኛው ነን። አያሞገስን!!
የአፋን የአገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲ አማራጮች በሚገባ መሰራጨት አለባቸው። እነዚህን የፖሊሲ አቋሞቹን ለመላው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ለማስታወቅ የተዘጋጀ አማራጭ ኃይል መሆኑን እቀበላለሁ። ከላይ ድክመቶቹን በሚመለከት እንዳሳሰብኩት፤ እንከን የለውም አልልም። አፋብን እነዚህንና ተዛማጅ ፖሊሶዎችን የሚተገብር አማርጭ የፖለቲካ ኃይል መሆኑን በመሬት ላይ እንዲያሳይ ጥሪ አደርጋለሁ።
አፋብን ሊገጥመው የሚችለው ተግዳሮት ምንድን ነው?
1/ የቁሳቁስ አቅም፤ ሎጂስቲክስ፤ ስንቅ። ሁሉም በየፊናውና ጎጡ የሚያደርገው ድጋፍ ሁኔታ።
2/ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አቅም። ጠንካራ ስራ አለመስራታችን የዐብይ መንግሥት ለሚከተለው የፋኖ ማራከስ ክስ ምክንያት ሆኗል። እንደ ወያኔና ብልጽግና ደጋፊዎች መስራት ለምን ተሳነን? አንድ ወጥ የሆነ የዓቅም ግንባታ ፕላትፎርም የስፈልጋል (Umbrella organization).
3/ የሕዝብ ግንኙነት አቅም። መግለጫዎች በተደጋጋሚና በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የዓለም ትኩረት መሳብ አለባችው። ይህ ክፍተት ትግሉን ጎድቶታል።
4/ የሜድያ አቅም፤ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ለአማራው ህልውና ለመታገል አለመቻል፤ አንድ አምብሬላ የሜድያ አማካሪ ቡድን ለምን አይመሰረትም?
5/ የጥናትና ምርምር አቅምን አጠናክሮ በሁሉም ዘርፍ ለአማራ ፋኖ የሚጠቅሙ ሰነዶችን ማቅረብ፤ ለምሳሌ በቀጠናው የኃይል አሰላለፍ።
6/ የአስተዳደር አቅም። የአማራ ፋኖ መንግሥትን የሚተካ የአስተዳደር መርህ ያስፈልገዋል፤ ግብአት እንስጥ።
አንዱ አፋብን ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች የሚለይበት ማንም የውጭ መንግሥት ወይንም ኃይል ሳይረዳው በራሱ አቅም፤ በሕዝብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ኃይል መሆኑ ነው። ሕዝባዊ መሆኑ ቅቡልነቱን ያጠናክረዋል፤ ከላይ በገጽ ሶስት ያቀርብኩትን ሶስተኛውን ትምህርታዊ ልምድ ይመለከታል።
አብዛኛው አፋብን የታጠቀው መሳሪያ ከዐብይ ጦር ሰራዊት የተማረከ ነው። ይህ ታይቶ የማይታወቅ ጀግንነት ጥበብ ያሳያል። ተአምራዊ ነው እላለሁ። ግን የውጭ መንግሥታት የተገነዘቡት አይመስለኝም።
ሰፊው የአማራ ዲያስፖራ በአንድነት ሆኖ ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች የመተግበር ግዴታ አለበት። ድጋፍ የሚሰጠው ለአንድ ወጥ ድርጅት እንደ አንድ ድርጅት አመራር ለተቋቋመው ለአፋብን እና ለአማራው ሕዝብ ነው። ይህ በመርህ መተግበር አለበት። የአማራው ዲያስፖራ ይህንን መርህ ማስተጋባት አለበት።
እርስ በእርሱ የሚጋጭ የአማራ ዲያስፖራ ትግሉን ጎድቶታል። እኔ የምመክረው ልዩነቶችን አቻችላችሁ አፋብን በዘላቂነት ደግፉ። አለያ የአማራውን የህልውና ትግል ይጎዳል፤ ተራው የአማራ ሕዝብ ይታዘበናል።
የተማረከ ኃብት ተጠቃሚው ማነው?
እንደማንኛውም ታጣቂ ኃይል የአፋብን የበላይ አመራር መጠንቀቅ ያለበት አካባቢዎችን ነጻ ባወጣ ቁጥር የሚያገኛቸው ጥሪቶች አሉ፤ ለምስሌ ማዳበሪያ። የማረከውን ጥሪት እንዴት ይጠቀምበታል? የሚለው ጥያቄ ገና አልተመለሰም።
በተመራማሪው ኮንስታንቲኖ ፒሸዳ በተደረገ Conflict Among Rebels—why insurgent groups fight each other” በተሰኘ መጽሃፍ ለነጻነት/ፍትህ የሚታገሉ ኃይሎች የሚጣሉት የማረኩት ኃብት “ለኔ ብቻ ይገባኛል” በሚል ነው ይላል። ለጋራ ዓላማ እየተዋጉ ለኔ ብቻ የሚለው ወደ ግጭት ያመራል የሚል ትምህርት ይሰጠናል።
ይህንን ተግዳሮት ለመወጣት የሚቻለው ለሕዝብ መድረስ ያለበትን የተማረከ ኃብት ለሕዝብ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። የገንዘብ ኃብት ከሆነ ደግሞ ፍታሃዊ በሆነ ደረጃ ለባለድርሻዎች ማካፈል ነው። ዋናው መስፈርት የሕዝብን ተአመኔታ መሰፈርት መተግበር የሚለው ነው።
ለሕዝብ የሚዋጋ ኃይል ሁልጌዜ የሕዝብን መብት ማክበር አለበት። ማዳበሪያ የሕዝብ ኃብት ነው። ትምህርት ቤት፤ የጤና ጣቢያ፤ መንገድ፤ ኤሌክትሪክ፤ ባንክ፤ ወዘተ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ እንጅ የፖለቲከኞች አይደሉም።
በሌላ አነጋገር አፍብን ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ሁሉ ሕዝብን የሥልጣኑ ባለቤት በማድረግ፤ አቅሙን በመገንባት፤ እየሰሩ ተምሳሌት በመሆን፤ ስነ ምግባሩ ከኦህዴድ ብልጽግና የተለየ መሆኑን የማሳየት ግዴታ አለበት። ዐብይ አህመድ ሁሉም ነገር የኔ ነው ከሚለው የሚለየው በመሬት ላይ በሚተገበረው ስነ ምግባር እና ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት መሆኑን በማሳየቱ ላይ ነው።
አንዱ የአማራ ፋኖን የማደንቅበት ምክንያት የማረካቸውን ወገኖቹን በትህትና ሲያስተናግዳቸው ማየቴ ነው። ይህ ስነ ምግባር ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትጵያ ሕዝብ አብሮነት፤ ኢትዮጵያዊነት፤ ዜግነት ተምሳሌት ነው።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሄረሰቦችና እምነቶች አገር ናት። ስለሆነም፤ በዚህ ስብሰባ የማቀርበው ሃሳብ የአማራ ፋኖ ብቻውን ኢትዮጵያን ሊታደጋት አይችልም የሚል ነው። ፍላጎቱም፤ ርእየቱም፤ ዓላማውም የአማራ የበላይነት አይደለም። ዓላማው የአማራው ሕዝብ ፍትህና እኩልነት ነው። ፍትህ ጎሳ ወይንም እምነት፤ ጾታ ወይንም ኃብት አይለይም።
በተጻራሪው፤ የዐብይ ፓርቲና መንግሥት ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ቢልም የአብይ ብልጽግና ግብ የአንድ ጎሳ የበላይነት ሲሆን፤ የአፍብን ግብ ግን በፍትህ ላይ የተመሰረተ ህብረብሄራዊነት እና የዜጎች እኩልነት ነው። የአማራውን የበላይነት ለመያዝ የሚለው ትርክት የኦህዴድ ጽንፈኞችና ብሄርተኞች የሚያደርጉት የፈጠራ ወሬ ነው።
የብሄራዊ ተቋማት ወሳኝነት።
ዐብይ አህመድ ከሚተችባቸው መካከል አንዱ ብሄራዊ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ማፍረሱ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ለመቀጠል የምትችለው ተቋማቷ ሁሉ- ለምሳሌ መከላከያ፤ ደህንነት፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የውጭ ጉዳይ፤ የገንዘብ፤ የመገናኛ ብዙሃን ወዘተ አገራዊ/ብሄራዊ፤ ሁሉን ዜጎቿን የሚወክሉ ሲሆኑ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የፖለቲካ ልሂቃን፤ ምሁራንና ሌሎች ስብስብስቦች እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩ መተማመንና የሚጋሯቸውን ብሄራዊ፤ አገራዊ ተቋማት መደገፍ አለባቸው። የጋራ የሆኑ ተቋማት የሌለው አገር አንድ ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥሩ ምሳሌ ነው።
በሌላ በኩል አማራውን ጽንፈኛ፤ ብሄርተኛ፤ የብሄር ትምክህተኛ የሚለው ትርክት ለጋራ አገር፤ ለጋራ ተቋማት ግንባታ መሰናክል ሆኗል። አማራው በማንኛውም የኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ ብቻውን ገዝቶ የሚያውቅበት ጊዜ ፈልጌ አላገኘሁም። የአማራውን ጥበበኛነት የማደንቅበት ምክንያት አለ። ይኼውም፤ ከሌላው ወገኑ ጋር በጋራ የመኖር ባህሉ ነው። ለአማራው ህዝብ አብሮነትን ማስተማር አይቻልም። ከደሙ ጋር የተሳሰረ ባህል ነው። ይህ ወርቃማ ባህል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት እና ለብሄራዊ፤ አገራዊ ተቋማት ግንባታ ወሳኝ ነው።
ለዚህ ነው፤ የኦህዴድ ብልጽግና ጸረ አማራነትና ጸረ ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው የምለው።
ዐብይ አህመድ ከሰራቸው የማይረሱ ስህተቶች መካከል በመንግሥት ደረጃ በአማራው ሕዝብ ላይ የእልቂት አዋጅና ጦርነት ማካሄዱ ነው፡፡ ይህ የጦር ወንጀለኛ አድርጎታል፡፡ ሌላው ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖረው ክስተት ብሄራዊ/አገራዊ ተቋማትን ጎሳዊ ማድረጉ ነው። “እኛና እነሱ” የሚለው ብሂል እኮ ጎሰኛነት፤ የብሄር ጽንፈኛነት፤ አግላይነትና የግሳ የበላይነት ነው። እኛና እነሱ የሚለው የሥልጣን መርህ እኮ እልቂትን ተቀባይነት ያደርገዋል። እነሱ ወንጀለኞች ስለሆኑ መጨፍጨፍ አለባቸው የሚል ስልት ነው። እነሱ መቀጣት ስላለባቸው ልጆቻቸው አይማሩም የሚል ነው።
የራሱን ሕዝብ በድሮን የሚጨፈጭፍ መንግሥት ምን ይባላል?
በ February 2026, ብቻ በደብረ ታቦር፤ በወረታ፤ በሸዋ ልዩ ልዩ ከተሞች፤ የዐብይ ጦርድ ሰራዊት ከሰባ በላይ የድሮን ጥቃቶች አካሂዷል፡፡ በደብረ ታቦር ማህል ከተማ ብቻ አስራ አንድ የድሮን ቦምቢንግ ተካሂዷል። ዐብይ አህመድ በደብረ ታቦር ከተማ ተከታታይ የድሮን ጭፍጨፋ አካሂዶ ህጻናትን ገድሏል፤ መሰረተ ልማት አውድሟል።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከቤት ወጥቶ መግባት ብርቅ ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሕግ አይከበርም። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሰውን አፍኖ ወስዶ ካሳ ማስከፈል የተለመደ ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የዐብይ ጦር ሰራዊት የትም አካባቢ ሲዋጋ የሚያገኛቸውን ሴቶች መድፈር፤ ንብረታቸውን መቀማት የተለመደ ነው። ቤትን ማቃጠል፤ ክምርን ማቃጠል፤ እንስሳዎችን መግደል የተለመደ ሆኗል። ይህ ሁኔታ የተባባሰበት ክልል ደግሞ የአማራው ክልል ነው። ከዚህ ክልል የባሰ ሁኔታ የሚታየው በጎንድር ነው፤ ከዚያም ደቡብ ጎንደር።
በጥቅሉ ስገመግመው በራሱ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ ያካሄደ ብችኛ መሪ ዓብይ አህመድ ነው። በራሱ ሕዝብ ላይ በጀት፤ በድሮን፤ በሞርታት፤ በታንክ ጭፍጨጋ ያካሄደው ጦር ሰራዊ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሚመራው የዐብይ አህመድ ጦር ሰራዊት ነው። ብርሃኑ ጁላና ዐብይ አህመድ እንደተለመደው፤ በተገላቢጦሽ የአማራ ፋኖን ተወቃሽ አድርጎውታል፡፡ እንደተለመደው የአማራ ፋኖም የጥቂት ግለሰቦች፤ “ወንበዴዎች፤ ሺፍቶች” እንቅስቃሴ ነው ይሉናል። ከዚያም አልፎ የአማራ ፋኖን “ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ይሰራል” የሚል ክስ ያቀርባሉ። የአማራ ፋኖ የታጠቀው መሳሪያ ሁሉ ከዐብይ ጦር ሰራዊት የማረከው መሆኑን ግን አንድ ቀንም ተቀብለው አያውቁም። “አሸነፍን” እንጅ “ተሸነፍን” የሚሉበት ምክንያት ግልጽ ነው።
ለማንኛውም፤ ትብብር በአማራው ላይ በአማራው ክልል እና በአሩሲ ኦሮሞያ የሚካሄደውን የቅርብ እልቂት እና ውድመት ሊያወግዝ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ በትግራይም፤ በኦሮምያም የሚካሄድውን ጭካንኔ የተሞላበት መንግሥት መር እልቂትና ውድመት ማውገዝ ያስፈልጋል።
እልቂትና ውድመት በራሱ ሊያስተባብረን ይገባል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን እንተባበር ስንል ዋናው ትኩረታችን፤ ጨካኙን፤ አረመኔውን፤ አገራችንን የከዳውን፤ $10 ቢሊየን ኢንቨስትመንት ለለገሰው ለኤምሪስት መንግሥት ታዛዢና አገልጋይ የሆነውን፤ ሙሰኛውን፤ ጠባብ ብሄርተኛውን፤ አስመሳዩን፤ የኦሮሙማ አጀንዳ አንቀሳቃሹን፤ የስብአዊ ፍጥረት ጠሉን፤ የጦረነት ሱስ የበከለውን የኦህዴድ ብልጽግናን አገዛዝ መቃወም፤ ማምከንና የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥን ዲሞክራሳዊ መንግሥት መመስረት ነው። ማንኝውንም ዘዴ ብንጠቀም ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን ማስተጋባት አለብን፤ አለያ ለውጥ ፋይዳቢስ ይሆናል።
የጠላትን ኃይል መናቅ ያስበላል።
ሆኖም፤ ይህንን አፋኝና አምባገነናዊ አገዛዝ ለመጣል ቀላል አይደለም። በዚህ እንስማማ፡፡ ዋናው ምክንያት የብልጽግና አባላት ቁጥር ከአስራ ስድስት ሚሊየን በላይ መሆኑ ነው። ልክ እንደ ኢሰፓ፤ አባላቱ መኖር የሚችሉት በብልጽግና መንግሥት ደሞዝና አበል ስለሆነ። ይህ ፓሪቲ ለዐብይ አሕመድ ተአመኔታ (Party loyalty) ፈጥሮለታል፡፡ አገዛዙ “ከፋፍለህ ግዛው፤ በለው፤ ብላውና አሳምነው” የሚል ጸረ-ሰላም፤ ጸረ-እርጋታ፤ ጸረ ሕዝብ ስልት ስለሚጠቀም፤ ህብረተሰቡን የሚመራው ሮቦቶች (Robots) እንደሚያደርጉት ነው፡፡ ለአገዛዙ፤ እርህራሄ፤ ፍትህ፤ የሕግ የበላይነት፤ አርቆ አስተዋይነት ለሃገርና ሕዝብ መቆም ወዘተ ቦታ የላቸውም፡፡
ይህ ለግል ጥቅም ተገዢነትና ተአመኔታ አፋሩንም፣ አኟኩንም፤ ወላይታውንም፤ ጉራጌውንም፤ ሶማሌውንም፤ አማራውንም፤ ኦሮሞውንም ወዘተ የአገዛዙ ተሳታፊ አድርጎታል፡፡
ላይ ላዩን ብቻ ካየነው፤ የህብረብሄራዊ ወይንም ኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሚመስል ሆኗል፡፡ አዛዡና ወሳኙ ግን የአንድ ጎሳ ኢሊት ነው፡፡
የጥቅም ትስስር ስለሆነ የአዲስ ተጥቃሚ መደብ የበላይነት የያዘበት የኢኮኖሚ ጉዳይ ሆኗል ማለት ነው (Political, Economic and Financial Capture of State and Government).
ለዚህ ነው፤ ዐብይ አህመድ የኦሮሞውን ሕዝብ በማባበል የያዝነውን የኢኮኖሚ፤ የፋይናንስ፤ የባህል፤ የፖለቲካ፤ የእምነት፤ የውጭ ግንኙነት የበላይነትና ሥልጣን እንዳንነጠቅ በሁሉም ሴክተር ቀን ከሌት መስራት አለብን እያለ ወንድም ክወንድሙ ጋር እንዲገዳደል የሚሰራው።
ማን ደልቶት ይኖራል?
ባጭሩ ብልጽግና አዲስ ተጠቃሚ መደብ መስርቷል። የካቢኔ፤ የስለላና ደህንነት፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የዐብይ ጦር ሰራዊት የበላይ መኮንኖች፤ የሜድያ ሃላፊዎች፤ የክልል መሪዎች፤ የልዩ ልዩ ተቋማት ሃላፊዎች የጥቅሙ አካል ሆነዋል፡፡ በአብዛኛው ዲያስፖራውም የዚህ መደብ አካል ሆኗል፡፡
የዐብይ አህመድ ዋና ትኩረት ሥልጣኑን ማራዘም ነው፡፡ ግቡን ስኬታማ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል በመላው ዓለም የዲጅታል ሰራዊት አሰማርቷል፡፡ ብዙ ሚሊየን ዶላር ፈሰስ እያደረገ የተሳሳተ መረጃ እንዲያሰራጩ ያደርጋል፤ ስኬታማም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፤ የአማራ ፍኖን ለመከፋፈል፤ ይህ ታሪክ ፈጣሪ እንቅስቃሴ በሕዝብ እንዲጠላ ለማድርግ የሚያድርገው ጥረት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ዐብይ አህመድ ለህዝቡ ኑሮ ደንታ የለውም፡፡ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ደንታ የለውም፡፡ ባንድ ወቅት ዐብይ ዐሕመድ “ለአሜሪካ እቀላለሁ” ብሏል፡፡ ለአሜሪካ የሚቀላ ከሆነ ግዙፉ ኢንቬስትመንት ለምታደርገው፤ በገፍ እንደ ድሮን ያለ መሳሪያ ለምትለግሰው ለኤምሬትስ እስዋለሁ ቢል አልደነቅም፡፡ በሱዳን ለሚካሄደው የውክልና ጦርነት ለኤምሪትስ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማሰልጠኛ የሰጠበት ምክንያት ለኢትዮጵያ ስጋት አይደለም? በኔ ግምገማ አደጋ ነው።
ትብብርና ሌሎች በጋራ ሆነው የኤምሬትስ መንግሥት የሚለግሰውን ድሮንና ሌላ ከባድ መሳሪያ እንዲያቆም፤ በቀጠናው ጣልቃ እየገባ የሚሰራውን ተንኮል እንዲያቆም ዓለም አቀፍ ፔቲሽን ይጀምሩ፡፡ እኤምሬትስን እናጋልጥ፡፡ ግልጽ ላድርገው። ኤምሬትስ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከዐብይ ጋር ተመሳጥሮ የጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎን ፈጣን ኃይል በመደገፍ የሚሰጠው ሥልጠና ኢትዮጵያን ወደ ውክልናው ጦርነት አስገብቷታል። ይህንን ጣልቃ ገብነት መቃወም አለብን።
ባጭሩም ቢሆን የገመገምኩት የአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሰላልፍና አደጋው ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚሄድ እገምታለሁ።
የአሜሪካና የኤስራኤል መንግሥታት በጋራ በኢራን ላይ የጀመሩት ጦርነት መላውን የመካከለኛው ምስራቅ አናግቶታታል። በተዛማጅ፤ የዓለምን ኢክኖሚ አናግቶታል። የቀይ ባህርንንና የአፍሪካ ቀንድንም የኃይል አሰላለፍ ሊቀይረው ይችላል። ይህንን አስኳል ጉዳይ በጥቅሉ ከማቅረብ ውጭ የወቅቱ ትኩረቴ አይደለም፡፡
ኢራን ያላትን ባልስቲክ ሚሳየልንና ድሮን በተከታታይ ተጠቅማ የገልፍ አገሮችን የፔትሮሊየምና ጋዝ መሰረተ፤ የውሃ ማጽጃ (Desalination infrastructure) መሰረተ ልማት ብታጋየው የሚኖረው አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው?
አንድ፤ በፔትሮ ዶላር ገቢ የሚመኩት የገልፍ አገሮች ይሰቅያሉ፤
ሁለት፤ 20 በመቶ የሚሆነው የዘይትና ጋዝ ለውጭ ገበያ አይላክም። አራት የኤዢያ አገሮች በሳምንት አምስት ቀን ይሰራ የነበረውን ወደ አራት ቀናት የለወጡበት ዋና ምክንያት ሆርሙዝ በመዘጋቱ ነው። የኑሮ ውድነት በሚያሰጋ ሁኔታ በመላው ዓለም ንሯል።
ትዝብት
እስካሁን ድረስ የታዘብኩት ክስተት በኢትዮጵያዊነት ዙሪያና በሁሉም ዜጎች መብት የምናምነው በአንድነት ቆመን አቤቱታ ለማሰማት አለመቻላችንን ነው፡፡ ይህ ክፍተት ሃቅ ነው፡፡ የአማራ እልቂት ምሳሌ ነው። በአንድ በኩል፤ ይህ የሚያሳየው የዘውግ የማንነት መለያችን ስር መስደዱን ነው፡፡ ለምሳሌ፤ እኔ የትግራይ ወገኖቻችን እልቂት መካሄዱን ተቀብየ ለዚህ ድርጊት በሃላፊነት መጠየቅ ያለባቸው ባለሥልጣናት በሰብአዊ እልቂት፤ በጦር ወንጀል እንዲከሰሱ ብየ በተደጋጋሚ ድምጼን አሰምቻለሁ።
በማይካድራ በተደጋጋሚ በኦሮምያ ወለጋና ሌሎች ቦታዎች፤ በጉራ ፈርዳ፤ በአማራው ክልል ወዘተ በአማራው ላይ በተደጋጋሚ በተካሄደው መንግሥት መርና መንግሥት መር ባልሆኑ የአማራ እልቂቶች ላይ ግን ተመሳሳይ ድምጽ አልሰማሁም። አማራ ያልሆኑ ልሂቃን ይህንን ለምን ወደ ጎን ተውት?
የሰው ህይዎት ተመሳሳይ ነው ካልን በአማራው ላይ የሚካሄድውን ግፍ፤ በደልና ጭካኔ አቻ ለአቻ መተቸትና ማውገዝ ግዴታችን ነው። የአማራውን የባሰ የሚያደርገው በይፋ የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት የሚያካሂደው መሆኑ ነው። ዐብይ አህመድ “አማራውን አጠፋዋለሁ” ሲል መንግሥት መር እልቂት ማለቱ ነው። ለሁሉም ዜጎች ህይወትና መብት ድምጽ ካላሰማን አገዛዙ ክፍተቱን ተጠቅሞ ጭፍጨፋውን ይቀጥላል፤ (Normalize) ያደርገዋል። በተለይ መገንዘብ ያለብን፤ ይህንንን የሚያደርገው “እኛና እነሱ”የሚለውን መርህ ተከትሎ እኛን በመከፋፈል እና እርስ በርሳችን እንዳንተማመን በማድረግ ነው።
በተለይ ወጣቱን ትውልድ የጦርነት የፖሮፓጋንዳ ሰለባ በማድረግ ነው። ዲያስፖራውም የፖሮፓጋንዳው አካል በማድረግ ነው። ለምሳሌ፤ የኮሪዶር ልማቱን በተናጥል እያዩ አዲስ አበባ ዱባይን ሆናለች የሚሉት ሂደው ከተማዋን ብቻ የጎበኙት እንደሆኑ እገምታለሁ። ሰማንያ በመቶ የሚገመተው ሕዝብ በእስራ ቤት፤ በጠለላ የሚኖር መሆኑን እረስተውታል። ሰባ ስድስት በመቶ የሚገመተው ሕዝብ በድህነት እንደሚሰቃይ ዘንግተውታል፡፡
እኔን የሚያሳስበኝ የወጣቱ ትውልድ እጣ ፋንታ ጭምር ነው።
ኦህዴድ ብልጽግና የወጣት አገር ይዞ ወጣት አምካኝ አገዛዝ ነው።
በ February 23, 2026, የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት አጃፓል ባንጋ በብሉምበርግ “How to Create Jobs for 1.2 Billion New Workers” የሚል ምክረ ሃሳብ የያዘ ኤዲቶሪያል አቅርበዋል፡፡ እኔን የሳቡኝን ሃሳቦች ላቅርብ፡፡
“መላውን ዓለም የሚያንቀሳቅሱ በጣም ፈጣንና አዝግመው የሚሄዱ ኃይሎች አሉ” በሚል ዘገባ፤
በመጀመሪያው እንደ AI ያሉ ቴክኖሎጅዎች፤ ጦርነት፤ የገበያ ቀውስ ፈጣሪዎች (Volatile markets) ይገኙበታል፡፡ ጦርነት መላውን የዓለም ኢኰኖሚ እንደሚያናጋ በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ የሚካሄደው የአካባቢ ጦርነት ብቻ ይመሰክራል። የሄርሙዝ የውቅያኖስ መገናኛ በር ስለተዘጋ የፔትሮሊየም ዋጋ በፍጥነት እየጨመረ ነው። የምግብ ዋጋም መጨመሩ አይቀርም። ይህ ማነቆ በፍጥነት ካልተከፈተ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ፐትሮሊየም ለሚገዙ አገሮች የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብሰው እገምታለሁ።
በሁለተኛው እርከን እያዘገሙ የሚከሰቱት የሕዝብ ብዛት፤ የውሃና ምግብ አቅርቦት ፍላጎት፤ የአየር ጠባይ ለውጥ ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ መካከል ትኩረት የሰጡት ከሕዝብ ብዛት ጋር እየጨመረ ለሚሄደው ወጣት ትውልድ የስራ እድል ነው። የስራ እድል ፈጠራ ቀላል አይደለም፤ ቅድመ ሁኔታዎቹ አመች መሆን አለባቸው፡፡
ቴክኖሎጅም ቢኖር ወጣቱ ትውልድ የትምህርት እድል ከሌለው፤ ሥልጠና ካልተሰጠው፤ ጤናማ ካልሆነ፤ የአቅም ግንባታ ግብአቶች ካላገኘ፤ ብሄራዊ ተቋማት ጠንካራ ካልሆኑ፤ ሰላምና እርጋታ ከሌለ ለወጣቱ ትውልድ በተፈለገው መጠን በሃገሩ ስራ የማግኘት እድሉ የተወሰነ ይሆናል፡፡
በጦርነት የተበከሉ አገሮች፟—ሱዳን፤ የመን፤ ሶሪያ፤ ፓሌስታይን፤ ምያንማር፤ ኢትዮጵያ–የመንግሥት ትኩረታቸው ክህልውናቸው ጋር ስለሆነ ለወጣቱ ትውልድ የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ፤ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት የንትርክ ስለሆነ በጋራ ጥቅሞች ላይ ከመስራት ይልቅ የሚከተሉት ፖሊሲ ለመልካም ጉርብትናና ለብሄራዊ መረጋጋት ጠንቅ ሆኗል፡፡
ባንጋ የታዳጊ አገሮችን መሪዎች ሲመክሩ በሚቀጥሉት 10—15 ዓመታት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን አዲስ ስራ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወጣት አፍሪካዊ ነው፡፡ ይህንን ስኬታማ ለማድርግ ቅደም ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ ከላይ አቅርቢያለሁ፡፡
የማሰምርበት መልካም አስተዳደር፤ ሰላምና እርጋታ ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪ በመሰረተ ልማት ላይ የሚደረግ ትኩረታና ግዙፍ ኢንቬትመንት-Physical and Social በተለይ ትምህርት፤ ጤና፤ እውቀት፤ ኢንዱትስሪ፤ ቱሪዝም፤ ለዝቅተኛ አምራቾችና ስራ ፈጣሪዎች ብድር መስጠት ይገኙበታል።
ይህ ሊሆን የሚችለው የመንግሥት አመራርና አስተዳደር በሕግ እና በደንብ ሲመራ ነው፡፡ ጉቦና ሙስና በሕግ ሲከለከል ነው፡፡ በቴክኖሎጅ እናምናለን ማለትና ቴክኖልጅን የምንጠቀመው የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል፤ ወጣቱ ራሱን የመቻልና ሕብረተሰቡን ለማገልገል አቅሙን ለማጠናከር ነው፡፡ መዋእለ ንዋይ ለቅንጦት፤ ለወቅታዊ ፍጆት፤ ለድሮን፤ ለብልጭልጭ ፕሮጀክቶች ፈሰስ ከሆነ የዜጎች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ መሆኑ አይቀርም፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል በተፈለገው መጠን ለመፍጠር አይቻልም። ለማንኛውም ቴክኖሎጅ ሰውን ያገልግላል እንጅ ድሮን የመሰለ ቴክኖሎጅን ተጠቅሞ ሰውን እንዲጠቃ መሳሪያ መሆን የለበትም፡፡
ለማጠቃለል፤ የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት አጃፓል ባንጋ የሰጡትን ምክረ ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ለሳቸው የማቀርበው ጥያቄ፤ ይህንን ልዩ ትኩረት በኢትዮጵያ እንዲተገበር በማሰብ ዓለም ባንክ ለዐብይ አህመድ የሚሰጠውን ብድር ለምን ለቨሬጅ አያደርገውም?
በተባበሩት መንግሥታት የተደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች የሚነግሩን፤ በኢትዮጵያ የወጣቱ ትውልድ 65 % መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በያመቱ ቢያንስ ለዚህ ትውልድ ሁለት ሚሊየን የስራ እድል መፍጠር እንዳለባት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የማድረግ አቅም የለውም፡፡ የግል ክፍሉ ግን እምቅ አቅም አለው፡፡ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ቢያገኝ፤ የአስተዳደር ቅልጥፍና ቢኖር፤ ጉቦና ሙስና ባይኖር ወጣቱ ትውልድ የማመረትና አገልግሎት የመስጠት አቅሙ ከፍ ይላል፡፡ የምስራቅ ኤዢያ አገሮች አድርገውታል፡፡ ቦትስዋና፤ ጋና፤ ሞሮኮ፤ ናይጀሪያና ሌሎች የአፍሪካ እገሮች ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
አበዳሪ ድርጅቶች የማይናገሩት ብዙ ጉዳይ አለ፡፡ ክነዚህ መካከል የዐብይ መንግሥት የሚሰራው ከዚህ የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ስራ በመፍጠር እና በማመቻቸት ፋንታ፤ ወጣቱን በገፍ እየመለመለ ወንድም ወንድሙን እንዲገድል ያደርጋል፡፡ ዝነኛው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ዳር ከድንበሩን በማስከበር ፋንታ የገዢው ፓርቲ መሳሪያ ሆኖ ቤተ መንግሥት ይጠብቃል፤ የአንድ ሰው አገልጋይ ሆኗል፡፡
ሰራዊቱ ልክ እንደ ወራሪ ኃይል ወገኑን በታንክ፤ በሞርታር፤ በሄሊኮፕተር፤ በድሮን ይጨፈጭፋል፡፡ ይህ ግራዚያኒ ከፈጸመው ወንጀል በምን ይለያል?
በደብረ ታቦር ከተማ ብቻ እስካሁን ሃያ ስድስት ጊዜ የድሮን ጭፍጨፋ ተካሂዷል፡፡ ይህ ቁጥር ከህወሃት ጋር በተደረገው የተካሄደውን የድሮን ጥቃት ይበልጣል፡፡ ዐብይ አህመድ አስቸኳይ አዋጅ ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 300 የድሮን ጭፍጨፋ ተካሂዷል፡፡ ቱርኮች፤ ኤምሬቶችን፤ ኢራንንና ሌሎች ድሮን አቅራቢዎች የምተቻቸውና ለዐብይ አህመድ የሚለግሱትን ወይንም የሚሸጡትን ከባድ የጦር መሳሪያ ባስቸኳይ እንዲያቆሙ የማሳስበውም ለዚህ ነው።
አስቡት፤ በአማራ ክልል እንደዚህ ያለ የጦር ወንጀል ማካሄድ ኢትጵያንና የኢትዮጵን ሕዝብ ይመጥናል? ወንጀለኛነት አይደለም? በሕግ አያስጠይቅም?
ይህ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ካልቆመ፤ ሰላምና እርጋታ ህልም ነው። ይህ ሁኔታ “የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ኢትዮጵያን እያፈራረሳት ነው” የሚለውን አርእስቴን ይደግፈዋል። የአገዛዙ ጭፍን የጦርነት አባዜ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ሙሉ በሙሉ ይንዳቸዋል።
በዚህ ሁኔታ አገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ ማሰብ በራሱ ድንቁርና ነው። በታሪክ ያሳጠይቃል።
ይቀጥላል
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
