April 16, 2026

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ “በደንብ የሚገባቸው አይመስለኝም” ሲሉ ተናገሩ። እርሳቸው የሚያስቧትን የበለጸገች ኢትዮጵያ “እንደሚያዩ” “ጥርጥር እንደሌላቸው” የገለጹት አብይ፤ ነገር ግን በተሟላ ደረጃ የስራቸውን ትሩፋት “የሚቋደሱ” እና “የሚዝናኑባት” ላይሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን አጋርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ እና ግምታቸውን የገለጹት፤ ከብሔራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት እና ላለፉት ሁለት ቀናት በተላለፈ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ነው። በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ሁኔታ ላይ ባተኮረው በዚህ ቃለ ምልልስ ማገባደጃ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ራዕይ በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። 

አብይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በሚቀጥለው 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ “አውራ ሀገር” እንደምትሆን “ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል። “እኔ የምናስባትን ኢትዮጵያ እንደማይ ጥርጥር የለኝም። አያታለሁ። ልጆቼ ደግሞ ይኖሯታል” ያሉት አብይ፤ የእርሳቸው “የህይወት ጉዞ” ለዚህ “መሰረት መጣል” እንደሆነ አስረድተዋል። 

“የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እና ልፋቶቻችን፣ ሪፎርሞቻችን፣ ስራዎቻችን respond እንዲያደርጉ ማድረግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ በደንብ እገነዘባለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የየዕለቱ ስራቸውን የሚያከናውኑት ይህንኑ “አምነው እና “አስበው” እንደሆነ አስገንዝበዋል። እርሳቸው ይህ እምነት ቢኖራቸውም “ብዙ ሰዎች” ግን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ “በደንብ የሚገባቸው አይመስለኝም” ሲሉም ተደምጠዋል። 

“ዝም ብሎ ሲናገሩ ስሰማ፤ እየተጓዝን ያለንበት ሩጫ ፍጥነት ውጤት የሚገባቸው አይመስለኝም” ሲሉም አብይ አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መሰል ሃሳቦች ሲያንጸባርቁ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራት ስብስብ አባል በሆነችበት ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን “ድል”፣ “ኢንቨስትመንት” እና “ለውጥ”፤ “ኢትዮጵያውያን በውል ባይረዱትም አለም በደንብ ተገንዝቦት recognize እያደረገ ይገኛል” ማለታቸው የሚታወስ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)