Ahmedin Jebel-አሕመዲን ጀበል ·Follow
የአክሱም ሙስሊሞችና የጽዮን ማርያም ቆይታዬ
በአሕመዲን ጀበል
ከ16 ዓመታት በፊት በአክሱም ከተማ ያደረግኩትን ጉብኝት መሠረት በማድረግ ትዝብቴን በሚያዚያ 2002 ዓ.ል በ “የሙስሊሞች ጉዳይ” መጽሔት ላይ የጉዞ ማስታወሻዬን አስነብቤ ነበር።
ዛሬ በአክሱም ከተማ በሙስሊም አክሱማውያን ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የሃይማኖት ጭቆናና የመብት ረገጣ፤ በጥቅሉ በመዋቅር የተደገፈው አፓርታይዳዊ መገለልና መድሎ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። የዛሬ 16 ዓመቱ ትዝብቴ በጉዳዩ ላይ ለግንዛቤ ይረዳል ብዬ ስላመንኩ በድጋሚ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
በወቅቱ በአክሱም ሙዚየም ውስጥ ያየኋቸው የነገሥታቱ ድንቅ ቅርሶች አስደምመውኝ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሙስሊሞች ላይ የሚፈጸመው የተቀነባበረ አፓርታይዳዊ ጭቆና እንዳይጋለጥ የክልሉ የደህንነት መዋቅር መረጃ እንዳይወጣ የሚያደርገውን ከፍተኛ ጥረት ታዝቤያለሁ።
የጉዞ ማስታወሻዬ ረጅም በመሆኑ፣ በአክሱም የነበረኝን ቆይታ የሚገልጸውን ክፍል በ2002 እንደታተመው ያለምንም እርማት እንደሚከተለው አጋርቻችኋለሁ።
መልካም ንባብ!
መልዕክቱ ለሁሉም እንዲሰርስ በሁሉም መንገድ ያጋሩ (Share)። የፌስቡክ ገጼ ቋሚ ተከታይ ያልሆናችሁ Follow በማድረግና በጽሁፉ ላይ ያለዎትን አስተያየት በ Like እና በ Comment ያጋሩ።
ጉዞ ወደ ትግራ

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ቁጥር 100 ወደ መቀሌ ለመብረር አውሮፕላኑ ውስጥ ተቀምጫለሁ፡፡የመብረሪያው ጊዜ 12፡30 ደረሰና ቀበቶ እንድናስር ተመከርን፡፡ስለበረራ ደህንነት ምክርም ተሰጠን፡፡፡አብራሪው በአንድ ሰዓት ውስጥ መቀሌ እንደምገባ ነገረን፡፡‹ቁርስ እዚያ እንበላለን› ሲል በአንድ ሰዓት ውስጥ መቀሌ እንደምገባ ነገረን፡፡ቁርስ እዚያ እንበላለን ብለን አስበናል፡፡ ሆኖም በረራ ሳንጀምር ተጨማሪ 15 ደቂቃ ቆየን፡፡
አብራሪው ከክፍሉ ሆኖ አውሮፕላኑ ችግር ስለገጠመው ከይቅርታ ጋር እንድንወርድ ነገረን፡፡ወረድን፡፡ሰዉ እያጉረመረመና እየተናደደ አንድ የአየር መንገዱን ሠራተኛ ምን ማድረግ እንዳለበት በጋራ ጠየቀ፡፡“አሁን ይሠራል ጠብቁ!” ሲል በትህትና መለሰ፡፡ ለአንድ ሰዓት ጠበቅን፡፡መቀሌ የተነየተው ቁርስ እዚሁ ሊሆን ግድ ሆነ፡፡ አንድ ኬክና ለሰላሳ በመብላት ጥበቃችንን ቀጠልን።
ወደ አውሮፕላኑ “ግቡ” ተባልንና ወደ አውሮፕላኑ ተቃረብን፡፡አንድ ሌላ ቴክኒሻን ነው መሰል መጥቶ “ተመለሱ ተሰርቶ አላለቀም” አለን፡፡ሰው ይበልጥ ተናደደ፡፡ግለሰቡን በቁጣ ብዙዎች ተናገሩት፡፡ህንዳውያኑ ግለሰቡ ላይ ይበልጥ ተናደው ፕሮግራማቸው እንደተስተጓበላባቸው ተናገሩ።
ሌሎች ደግሞ “በዚህ አውሮፕላንስ አንሄድም” አሉ፡፡አስራ አንድ ቱርካውያን ወንዶችና ሴቶች “ይቅርብን” ብለው ተመለሱ፡፡ ቁጭ ብለን ስንጠብቅ የተዋወቅሁትን አንደኛውን ቱርካዊ ጠየቅሁት፡፡“እቅዳችን የነጃሺን ቀብር ልንጎበኝ ነበር፡፡ጠዋት ሁለት ሰዓት መቀሌ ገብተን፣ወደ ውቅሮ በመሄድ ነጃሺን ጎብኝተን በ11 ሰዓቱ በረራ ወደ አዲስ አበባ ልንመለስ ነበር፡፡ ከዚያም ዛሬውኑ ማታ በ5 ሰዓት ላይ ደግሞ ወደ ሀገራችን ልንበር ነበር እቅዳችን፡፡ባለመዘየሬ አዝናለሁ፡፡” አለኝ፡፡ነፃ ህክምና ሊሰጡ እንደመጡም ነገረኝ፡፡
የነጃሺን ቀብር ሳይዘይር ወደ ሀገሩ ሊመለስ በመሆኑ ከፊቱ ላይ ያየሁትን ሀዘን እና የፕሮግራም አያያዛቸው እያስገረመኝ ጥበቃዬን ቀጠልኩ፡፡እነርሱ ትተው ሄደዋል፡፡ለአራት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ላይ ተጠርተን በአውሮፕላኑ ውስጥ ገባን፡፡ ተበላሽቶ የነበረው አውሮፕላን ራሱ በመሆኑ ሰው ዱዓ ሲያደርግ(ሲፀልይ) ይስተዋላል፡፡ሆኖም ያለምንም ችግር በረራ ጀመርን፡፡በአውሮፕላን ውስጥ ሞባይል መዝጋት ግዴታ እንደሆነ ተነግሮን ነበር፡፡ነገር ግን ብዙም ሳንርቅ የአንዲት ወይዘሮ ሞባይል ጮኾ፡፡ ሴትየዋ “ተነስተናል” ብለው በመናገራቸው ሆስቴሴቹ ሮጠው አስዘጓቸው፡፡የውጭ ዜጎች ተቆጡ፡፡ምክንያቱም ሞባይል ከአውሮፕላኑ የበረራ ሥርዓት ላይ ችግር ሊፈጠር ስለሚችል ነበር፡፡
በ5 ሰዓት ላይ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ደረስን፡፡ወረድን፡፡ንፋሱ ጠንከር ያለ ነበር፡፡አልጋ ያዝኩ፡፡መቀሌን ዞርዞር ብዬ መጎብኘት ጀመርኩ።
ጉዞ ወደ አክሱም

(በመቀሌና ነጋሽ መንደር ለቀናት ካሳለፍኩ በኋላ ወደ አክሱም ጉዞ ጀመርኩ።)

ከመቀሌ መናሐሪያ ሌሊት መኪና በመሳፈር ጉዞዬን ወደ አክሱም ቀጠልኩ፡፡250 ኪሎ ሜትሩን በምን ያህል ጊዜ እንደምደርስ እያሰብኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ መንገዱ ተራራ ይበዘዋል፡፡ ግራና ቀኙም ገደልና ተራራ ብቻ ነው፡፡አዲግራት ገባን፡፡ቁርስ በልተን ቀጠልን፡፡ ለአከባቢ አዲስ ስለ ነበርኩ አብረውኝ የተቀመጡትን የየቦታ ስም እየጠየቅኩ አሰላቸኋቸው፡፡
አድዋ ከተማ ገባን፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ የተወለደበትና ያደገበት እዚህ ጋር ነው” ብለው አሳዩኝ፡፡የአድዋ ጦርነት የተካሄደበትን ስፍራ አሳዩኝ፡፡መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ መንገዱ ከአድዋ አክሱም አስፋልት አይደለም፡፡ግና ከአዲግራት እየተሰራ አድዋ መድረሱን አይቻለሁ፡፡ምናልባትም ይህኛው በቅርቡ እንደሚሰራ እያሰብኩ ኮረኮንቹ እያዘለለን ጉዟችን ቀጠልን፡፡አክሱም ገባን።
በ4ኪሌ ጊቢ አብሮኝ የተማረውንና አሁን በአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህር ወደሆነው ወዳጄ ደወልኩ፡፡አገኘሁት እርሱ ጋር አረፍኩ፡፡ሻወር ወሰድኩና ለመጎብኘት ተነሣሁ፡፡የአክሱም ሐውልት አየሁት፡፡ከጣሊያን የተመለሰውንም፣ ውድቅ የተሰባበረውን ተዟዙሬ ጎበ።
አሕመዲን ጀበል በአክሱም ጽዮን ማርያም

አስጎብኚው አቶ ሹሜ ብርሃነ ገለፃ አደረጉልኝ፡፡ሙዚያሙንም ከሚገባ ተመለከትኩ፡፡ከአክሱም ሀውልት አጠገብ “ታሪካዊቷ” የፅዩን ማርያም ቤተክርስቲያን ትገኛለች፡፡
አላህ ለነቢ ሙሳ የሰጠው “ታቡት” (የእነርሱ የሙሴ ጽላት የሚሉት) በዚህ ቤተክርስቲያን ይገኛል ብላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትናገራለች፡፡ ግና በርካታ ሙሁራንን ማሳመን ቢሳናትም ቅሉ፡፡ለመኖሩም “አለ” እንጂ ገብቶ ያየ የለም፡፡ ግና ቤተክርስቲያኒቷን መጎብኘት አለብኝ ብዬ ወደ ግቢው ዘለቅሁ፡፡
ለመጎብኘት ኢትዮጵያዊ 20 ብር ይከፍላል፡፡የውጭ ዜጋ ደግሞ መቶ ሀያ ብር፡፡በአስጎብኚው መዘምር ኮከብ ሳዶአቅ ገለፃ ተጀመረ፡፡
ቤተክርስቲያኑ በታሪካዊ እንደሆነ፤ረጅም እድሜ እንዳላት በዮዲት ጉዲት እና አህመድ ግራኝ እንደተቃጠለ ተረከልኝ፡፡ኢማም አህመድ(ግራኝ) አቃጠለው የሚባለውን አሳየኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አሁን ጽላቱ ያለበት በአፄ ፋሲለደስ እንደተሠራ ሴቶች መግባት እንደማይፈቀድላቸው አብራራልኝ፡፡ወደ ቤተክርስቲያኗ ሙዚየም ገባን፡፡በር ላይ በኤሌክትሮኒክ መሳሪያ ተፈተሽኩ፡፡ ውስጥ የተለያዩ አፄዎች ያሰሯቸው በርካታ የወርቅ መስቀሎች ይገኛሉ፡፡
የንግስት የዘውዲቱ የወርቅ ልብስና የወርቅ ዘውድ፣የአቡነ ሰላማ የወርቅ ዘውድ፣የራስ ስዩም መንገሻ የወርቅ ፀናጽል፣ የአፄ ሐይለስላሴ የወርቅ ጋሻና ጦር፣የአልማዝ ዘውድ፣የወርቅ ጫማ እና የወርቅ ጥላ ይገኛል፡፡የነገስታቱ የወርቅ ኮርቻ፣የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ በወርቅ የተለበጠ መጽሐፍ ቅዱስ፤የአፄ ዮሐንስ የወርቅ ልብስና ዘውድ ፣እንዲሁም ባለ 13 ኪሎ ግራም የወርቅ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሌሎችም በርካታ የቤተክህነትና የነገስታት መገልገያዎችን አየሁ።
አስጎብኚዬ “በደንብ ነው ያስጎበኘሁህ” አይነት ንግግር እየደጋገመ ጉርሻ የመፈለግ አዝማሚያ ደጋገመ፡፡ ትልቁ የወርቅ መስቀል ጋር ስንደርስ ‹‹… ተባርከህ እንድትሄድ ለበረከቱ ትንሽ ያዝ፤የወርቅ መስቀሉን በመያዝህ እድለኛነህ፡፡አየህ ወርቅ ነው፡፡ከባድ ነው፡፡” አለኝ፡፡የሳይኮሎጂ ጫወታ መሆኑ ነው፡፡ ሙስሊም መሆኔን አላወቅ መሰል “አልነካም ብልስ…” ብዬ አሰብኩ፡፡ በውስጤ ‹‹አኡዙ ቢላሂ ሚነሸይጧኒ ረጂም›› ብዩ ነካሁት፡፡
“”የሙሴ ጽላት”ን አንተ አይተኻል?”

የውስጥ ጉብኝቴን ጨርሼ ወደ ጊቢው ወጣሁ፡፡ አስጎብኚው ቀጠሎና “ማርያም ጽዮን ገዳም ሴቶች አይገቡም፡፡ አፄ ሐይለ ስላሴ ለወንድና ለሴት ብለው በ1957 ይህን አሰሩ፡፡” ብሎ በዚያው በጊቢ ውስጥ የተሠራውን ሌላ ቤተክርስቲያን ጠቆመኝ፡፡
“አንድ ሞኒክሴ ብቻ ነው የሚገባው፤ማንም ሰው አይገባም፤ጳጳስ እንኳ አይገባም፡፡ሞነክሴው የበቃ ሰው ነው፡፡ እስከ እድሜው ልክ እዚያው ፀሎት ያደርጋል፡፡ ወደዚህ አይወጣም፡፡በቀን አንዴ ለምግብ ብቻ በዚያ አጥር ውስጥ ብቅ ይላል” እያለ ገለፃውን ቀጠለ፡፡
ጥያቄ አለኝ አልኩና “ይህ በጽዮን ማርያም ሴቶች እንዳይገቡ የያዛችሁት ህግ ከቀኖና መፃህፍት ነው ወይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ?” ስል ጠየቅሁ፡፡ “ምክንያቱም ሙሴ ብቻ ነው ጽላቱን የተቀበለው፡፡ በደብረሲና ገዳም፡፡
ሙሴ ብቻ ስለተቀበለው ገባዳም በተባለ ሁሉ ከዚያ ተይዞ የባህታውያን ቦታ ስለሆነ ከጄነሬሽን ጄነሬሽን (ሴቶች አይገቡም) ከሙሴ የመጣ ነው፡፡” ብሎ መለሰልኝ፡፡ “ምሁራን ይህ የሙሴ ጽላት እዚህ ናት የሚለውን አባባል አይቀበሉም፤ አለ ብቻ በማለት ለሚያነሱት ጥያቄ እንዴት ምላሽ መስጠት ይቻላል?” ስል ጠየቅሁት፡፡
እንደዚህ ሲል መለሰ “መልሳችን የሙሴ ፅላት በኢትዮጵያ ራሷ ፈቅዳ ነው የመጣችው፡፡እዚህ አክሱም ነው የምትገኘው፡፡ ምክንያቱም ዝናብ ከጠፋ የአክሱም ህዝብ ተሰብስቦ ፀሎት ሲደረግ ዝናብ ወዲያው ይመጣል፣ጦርነት ወዲያው ይቀዘቅዛል፡፡ብዙ ተዓምራት እያደረገ እዚህ ነው ያለው፡፡” አለኝ፡፡
የሙሴ ጽላትን ጠባቂ ናቸው የሚባሉትን መነኩሴ ማግኘት እችላለሁን?

“ውስጥ ያለውን ሞነክሴ ለምግብ ሲወጣ ጠብቄ ኢንተርቪው ላድርግለት ይፈቀዳልን?” ስል ጠየቅሁት፡፡ “አይቻልም” አለኝ፡፡ “እዚህ ስለመኖሩ በተናገርከው ላይ የሰጠኸኝ ማስረጃ ያው ‹‹አለ ነው››፡፡ ግና ይህ ንግግር ምሁራኑን ማሳመን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ግን አንተ ራስህ አይተሃል?” ስል ጠየቅሁት፡፡ እንዳላየ ነገረኝ፡፡
እየገረመኝ አመሰገንኩና ልወጣ ስል ቆም ብሎ ሳንቲም ጠየቀኝ፡፡ “ለመግቢያ ከፍያለሁ፡፡ ላንተ ነገ እመለሳለሁ፡፡” ብዬ ልወጣ ስል ተናደደ፡፡ እኔም ይህን ያህል ቅርስ ባለበት ጊቢ እንዴት አንድም መሳሪያ የያዘ ጠባቂ ይጠፋል? ፈታሹም መፈተሻ እንጂ መሳሪያ አልያዘም፡፡ገረመኝ፡፡እያንዳንዱን የአስጎብኞዎቹን ንግግር በመቅረፀ ድምጼ አስቀርቼ የአስጎብኚው ነገር እየገረመኝ ጉብኝቴን ጨርሼ ወጣሁ፡፡
ጭቁኖቹ የአክሱም ሙስሊሞች

በየጊዜው የምሰማውን የሙስሊሞችን ሮሮ ምን እንደሚመስል ለመታዘብ እየጓጓሁ ወደ ሙስሊሞች መስገጃ ሥፍራዎች ሄድኩ፡፡በከተማ መስጊድ መስራት እንደተከለከሉ ይናገራሉ፡፡ “የማርያም ሀገር ነች፣የሙሴ ጽላት አለባት፣ ታሪካዊቷ የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ስላለበት” መስጊድ መስራት እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ከተራ ሙስሊሞች አንስቶ እስከ የዞኑ መጅሊስ መሪዎች ገለፃ አደረጉልኝ፡፡
በከተማው ትናንሽ ወቅፍ የተደረጉ መስገጃዎች 13 አካባቢ ይደርሳሉ፡፡እነዚህም ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው አንዱን አልያም ሱቃቸው አንዱን ክፍል በመስገጃነት ሰጥተው ይሰገድባቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በሺህ መሀመድ ሀጎስ ወቅፍ የተሰጠው መስገጃ ነው፡፡ሀያ ሰው አካባቢ ታሰግዳለች፡፡በራሳቸው ጊቤ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ሌላኛው ጁመዓ የሚሰገድበት “ሱቅ መስጊድ” የሚሉት ነው፡፡አንድ ግለሰብ እንዲሰገድበት ወቅፍ ሰጥተው ነው የሚሰገድበት፡፡ ቢበዛ 60 ሰዎችን ብታስተናግድ ነው።
ስለምትሞላ በበረንዳዋና በሱቆች መካከል ባለ ቦታ በኮሪደር ላይ ይሰገድባታል፡፡ አሰጋጅዋ ወጣት ሼህ ሙመድ አወል ያቀራል፣ ያሰግዳል፡፡ከአሊፍ እስከ ኪታቦች ያቀራል፡፡ ጠዋት ከሱብሂ በኋላና መግሪብና ኢሻ መሀል ጥቂት ሰዎችን ኪታብ ያቀራል፡፡ጠዋትና ከሰዓት ህፃናትን ቁርአን ያቀራል፡፡ ከአስር በኋላ ሴቶችን ያቀራል፡፡ የጀመዓ ሰላትንም የሚያሰግደው ራሱ ነው፡፡
የሚገርመው ሙሉ ቀን እንደዚያ እየታገለ አካባቢው ሙስሊም አዋጥተው በወር ሦስት መቶ ብር ነው የሚከፍሉት፡፡
ዳዕዋ የተጠሙ አክሱማውያን ሙስሊሞች

ዳዕዋ ማድረግ እንደምፈልግ ፈቃድ ጠይቄ ጥቂት አደረግሁ፡፡ ሰው የዳዕዋ ጥማት እንዳለው ይታያል፡፡ ኢስላምን ሲወዱ ለጉድ ነው፡፡ አንድ አባት እያለቀሱ መጥተው እጄን ሳሙኝ፡፡ “ህዝቡ ጃሂል ነው ምን ያውቃል እባካችሁ ኑና አስተምሩን! ከቻልክ በመግሪብና ኢሻም መሀል ድገም” አሉኝ፡፡
ሰው በሰልፍ እጄን ሊስም ተሰባሰበ፡፡ሳላስበው ለዝየራ መከበቤ አስገረመኝም አስደነገጠኝም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞኝም አያውቅም፡፡
በመግሪብና ኢሻ መሀልም ዳዕዋ አደረግኩ፡፡ ከቅድሙ ሰው ሞልቷል፡፡ ከዩኒቨርስቲ ጥቂት ተማሪዎችም ነበሩ፡፡ከሶላት በኋላ ስላሉበት አስደንጋጭና አሳዛኝ ሁኔታ ሲነግሩኝ ወላሂ ሆዴን በላኝ፡፡
ከሱብሂ በኋላ በሼህ መሀመድ ሀጎስ ወቅፍ ወደተደረገው መስጊድ አመራሁ አምስት ሰዎች ኪታብ ይቀራሉ፡፡ሽማግሌዎች ደግሞ ዱዓ ያደርጋሉ፡፡ የዞኑ መጅሊስ ፀሐፊ ሼህ መሀመድ ሀሰንም ከዚህ አሉ፡፡ስለ አክሱም ሙስሊሞች አሳዛኝና አሳማሚ ችግር ተረኩልኝ፡፡ በሀገሪቷ ህገመንግስት ቢኖርም መብት ብሎ ነገር ማግኘት እንዳልቻሉ ነገሩኝ፡፡ቤተክህነት ብዙ ጫና እንደምታስደርግባቸው ተረኩልኝ፡፡
የአክሱም ከተማ ሙስሊም ብዛቱ አስራ አምስት ሺ እንደሚደርስ ነገሩኝ፡፡እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2005 የስታክስቲክስ ባለስልጣን ያወጣው መጽሐፍ የአክሱም ህዝብ 47,320 እንደሆነ ይተርካል፡፡ከዚህ ውስጥ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሆነው 75% (35,490) እንደሆነ ይናገራል፡፡በደጋ ሀሙስ ሰፈር ወይዘሮ ሸምሲያ ሼህ ሷሊህ የኢቢዩ ሕጻናትን ቁርአን እንደሚያቀሩ ወዳጄ ተረከልኝ፡፡
ከ120 በላይ ሕጻናትን ቁርአን እንደሚያቀሩና ተማሪዎቹ በወይዘሮዋ(ዑስታዝዋ) ቤት ዉስጥ የራሳቸውን ቁርአንንና ወንበር ይዘው እንደሚመጡ ሰማሁ፡፡ ከደርግ ዘመን በፊት ሙስሊሙ መሬት መያዝ እንደማይችልና ቤት እንደሌለው ሽማግዎች ተረኩልኝ፡፡
ደርግና የየአክሱም ሙስሊሞች

በአክሱም መስሊሙ ቤት ሊይዝ የታቻለው በደርግ ዘመን እንደሆነ አብራሩልኝ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ሙስሊሙ መሬትም ቤትም እንዳይኖረው ይቃወሙ የነበሩትን የቤተክህነት ቀሳውስትን በወቅቱ ይፈራ የነበረው የደርጉ መሪ አፈወርቅ አለምሰገድ ጠራቸው፡፡
ለሙስሊሙ የቤት መስሪያ ቦታ ቢሰጣቸው ይቃወሙ እንደሆነ ጠየቃቸው፡፡ በጣም ይፈራ ስለነበር እንደማይቃወሙ ገለጹለት፡፡ “ብትቃወሙ ኖሮ በአደባባይ ነበር የምሰቅላችሁ” ሲል ተናገራቸው፡፡ከዚያም ሙስሊሙ በ30 ብር መሬት መራላቸው፡፡ ከዚያም መሬት መያዝ ቻሉ፡፡ የንግድ ቦታውን ደግሞ ጣሊያን ነበር ለሙስሊሞች የሰጠው፡፡
መረጃ እንዲወጣ ስለማይፈልጉ ይይዙሃል
ቶሎ ከአክሱም ዉ

አሳዛኙን የአክሱም አሳዛኝ ቅኝቴን ጨረስኩ፡፡በአንድ መስገጃ ቦታ ሳለሁ አንድ አባት መጡና “ቶሎ ከአክሱም ውጣ፣በኋላ ይይዙሃል፣መረጃ እንድታወጣ አይፈልጉም” አሉኝ፡፡
የበረራ ሰዓቴ ስለደረሰ ወደ አፄ ዩሐንስ 4ኛ አየር ማረፊያ በባጃጅ አመራሁ፡፡አውሮፕላኑ የሚነሳው 2፡50 ነበር፡፡እቃዎቼን አስፈትሽ ጀመር፡፡ሁሉንም ከፍተው አዩ፡፡ወክማንና ካሴቶች አየችና ፈታሽዋ፡፡ ወክማኑን አወጣች፡፡ “ምንድ ነው?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ለጉብኝት እንደመጣሁ ነገርኳት፡፡ ወክማኑን ከፈተችው፡፡በሁሉም ቦታ ስጎበኝ በወክማን እየቀዳሁ ነበርና እንዳጋጣሚ ሆኖ የአክሱም ሀውልት ጉብኝቴ ግዚ የተቀዳው ሆነ፡፡ገባሁና መጠበቅ ጀመርኩ፡፡
በአየር ማረፊያው የሚሸጠው በጠቅላላ የቤተክርስቲያን መገልገያዎች ናቸው፡፡በአንድ ጎን ላይ ተምርና ማር አየሁ፡፡ ተምሩ የደረቀ ነው የታሸገውን በ10 ብር ገዛሁ፡፡ ማሩ ግን በጣም ነጭና ወተት የመስለ ነበር፡፡ ኪሎወን በ70 ብር ገዛሁና ጥበቃዬን ቀጠልኩ፡፡
2፡50 አለፈ፡፡
አንድ የአየር ማረፊያው ደህንነት መጣና ‹‹ውስጥ ትፈለጋለህ!›› አለኝ፡፡ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ውስጥ ያለው ሀላፊ “በኤክስረይ ስናየው ሻንጣህን ደግመን መፈተሸ እንዳለብን ስለተሰማን ነው፡፡ይቅርታ፡፡ሻንጣህን ክፈት” አለኝ፡፡
ግርም አለኝና ያቺ ወክማን ደግሞ ልትደመጥ ነው ብዬ በልቤ አሰብኩ፡፡ሁሉንም አወጡና በጥንቃቄ ፈተሹ፡፡አመስግነው መለሱኝ፡፡
አዲስ አበባ እንደርስበት የነበረው ሰዓት ሁላ አለፈ፡፡አንዲት ትንሽ አውሮፕላን መጣች፡፡ጥቂት ሰዎች ተጠርተው ገቡ፡፡የኛ ቦይንጉ ስለሆነ እንድንጠብቅ ተነገረን፡፡ ለ5 እስር ጉዳይ ላይ መጣ፡፡ግማሽ ሰዎችን ከጎንደር ጭኗል፡፡በረራ ወደ አዲስ አበባ ጀመርን።

