📌የመረጃ አፈናን የሚሰብር የሳተላይት ሚዲያ ጥምረት አስፈላጊነት!

በዲጂታል ዓለም ብቻ ተወስኖ መቆየት የራስን የኅልውና ዕድል በጠላት እጅ እንደመስጠት ይቆጠራል። በአሁኑ ወቅት መረጃን የማግኘትና የማስተላለፍ መብት በኢንተርኔት መቆራረጥና በማኅበራዊ ሚዲያ ተፀዕኖና ዕገዳዎች ሥር በወደቀበት ሁኔታ፣ የኅልውና ትግሉን ድምፅ በዲጂታል አማራጮች ብቻ ለማሰማት መሞከር ውጤቱ ውስንና ለአደጋ የተጋለጠ ነው።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለሕዝባዊ ንቅናቄው እጅግ አስፈላጊና አጣዳፊ የሆነው እርምጃ፣ የኢንተርኔት አፈና የማይገታውን የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ዕውን ማድረግ ነው። ይህ ወርቃማ ሐሳብ ከመዝገብ ቤት ወጥቶ ወደ ተግባራዊ ፕሮጀክት እንዲቀየር የአማራ ሚዲያ ካውንስል፣ የአማራ ሚዲያ ባለቤቶች፣ የአማራ ማኅበራት፣ በውጭ የሚገኘው ዲያስፖራና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በጋራና በተቀናጀ ሁኔታ ሊረባረቡ ይገባል።

ዋናውና ትልቁ የቤት ሥራ በተበታተነ መልኩ የሚደመጡ ድምጾችን ወደ አንድ ወጥና ጠንካራ ስብስብ መቀየር ነው። የትግሉን ሒደት፣ የሕዝቡን በደልና ቀጣይ የጋራ የህልውና አደጋውን ሊቀለብሱ የሚችሉ አቅጣጫዎች በአንድ ማዕከላዊ አጀንዳ ስር ማሰባሰብ ካልተቻለ፣ በጠላት የሚፈበረኩ የሐሰት ወሬዎችን መመከትና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማሳመን አይቻልም።

በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት በዋናነት የአማራን ሕዝብ እውነተኛ ድምፅ የሚያስተጋባና የትግሉን ስኬት የሚያረጋግጥ ብርቱ የሚዲያ አጀንዳ መቅረጽ አለበት። ይህ አጀንዳ ደግሞ በሳተላይት አማካኝነት በየገጠሩና በየግንባሩ ላለው ሰፊ ሕዝብ ያለ አንዳች መቆራረጥ መድረስ ይኖርበታል።

ለዚህም ተግባራዊነት፣ በውጭ የሚገኘው ዲያስፖራና የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት የመደገፍ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው። በሌላ በኩል፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ከመሬት የሚመነጩ እውነተኛ መረጃዎችንና የትግሉን ወቅታዊ ገጽታ ለሚዲያው በግብዓትነት በማቅረብ ስርጭቱ ሁልጊዜም ትኩስና ተአማኒ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል።

ይህ ጥምረት በዲጂታል መድረኮች ብቻ የታጠረውን የመረጃ ፍሰት ወደ ሰፊው አየር በማሸጋገር፣ የኢንተርኔት መዘጋትን እንደ ስትራቴጂካዊ መሣሪያ ለሚጠቀመው የብልጽግና አገዛዝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ነው።

በአጠቃላይ ይህ ፕሮጀክት ተራ የሚዲያ ተቋም ማቋቋም ሳይሆን፣ የሕዝብን ኅልውና የመጠበቅና የሚዲያ የበላይነትን የመያዝ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። አፋብንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይህንን ዕድል ተጠቅመው መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ በመቁጠር፣ የአማራ ሕዝብ ሁሉንም አካታች የሆነ የራሱን ጠንካራ የሳተላይት ጣቢያ በአፋጣኝ ሥራ ላይ ማዋል አለበት።

በአንድ ወጥ አጀንዳ የሚመራ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና በሕዝባዊ መሠረት ላይ የቆመ የሳተላይት ቴሌቪዥን፣ የታፈነውን ድምፅ አውጥቶ ለእውነትና ለፍትሕ የሚቆም ታሪካዊ ተቋም ይሆናል።

ይህ የሳተላይት ፕሮጀክት አማራጭ መረጃ የማቅረብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብን ህልውና የማስጠበቅ እና የሚዲያ የበላይነትን የመያዝ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው። የአማራ ሚዲያ ካውንስል ይህንን ፕሮጀክት እውን በማድረግ፣ የትግሉን ድምጽ ወደማይገታበት እና ወደማይታፈንበት አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል።

ይህ የሳተላይት ፕሮጀክት እውን ሲሆን ሚዲያዎችን በአንድ ትልቅ ጥላ ስር የሚያሰባስብ እንጂ አንዱን በሌላው ስር የሚያደርግ አይደለም። በአንድነት መቆም፣ በነፃነት መሥራት” የሚለውን መርህ በመከተል፣ የሚዲያዎቹን ሉዓላዊነት ሳያዳክም የጋራ ተፅዕኗቸውን ግን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል።

ድል ለአማራ ሕዝብ!

Mulugeta Anberber Gebeyaw