
ከ 4 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
በታንዛኒያ “ተፈጥሮአዊ ባልሆኑ ምክንያቶች” ምክንያት 518 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን እና ከእነዚህም ውስጥ 197 ሰዎች በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ጥቅምት ላይ የተደረገው አጠቃላይ ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለመመርመር የተቋቋመው ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ለግድያው ተጠያቂው ማን እንደሆነ ሳይገልጹ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድ መክረዋል።
የታንዛኒያ ባለሥልጣናት በአገራዊ ምርጫወ ወቅት ስንት ሰዎች እንደሞቱ የተናገሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ቀደም ሲል የጸጥታ ኃይሎች በፀረ-መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ ከስሰዋል።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ጥቅምት 29 በተካሄደው ምርጫ 98 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነው ተመረጠዋል። ዋና ተፎካካሪዎቻቸው ከምርጫው እንዲገለሉ በመደረጉ የዴሞክራሲ “ፌዝ” ሲሉ ተቃዋሚዎች ገልጸውታል።
ፕሬዚዳንቷ ምርጫው ፍትሃዊ እና ግልጽ እንደነበር በወቅቱ ገልጸው፤ ለአመጹ የውጭ ዜጎችን ተጠያቂ በማድረግ እሳቸውን ለመጣል የተጠነሰሰ ሴራ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
በጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በምርጫው ግልጽነት እጦት ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት እና የደቡብ አፍሪካ አገራት ጥምረት፣ ሳድክ ምርጫው ከዲሞክራሲያዊ ደረጃዎች በታች መሆኑን አስታውቀዋል።
ቢቢሲ በበኩሉ ፖሊስ ወደ ተቃዋሚዎች ቡድኖች ሲተኩስ የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች ትክክለኛነታቸውን አረጋግጧል። በበይነ መረብ ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሰልፈኞች በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ የፖሊስ አባላት ከመታገዳቸውም በላይ ህዝቡን ለመበተን የአስለቃሽ ጭስ ሲተኮሱ ታይተዋል። በብዙ ቪዲዮዎች ደግሞ የተኩስ ድምጽ የሚሰማ ሲሆን ሰዎች በተፈጠረው ትርምስ ውስጥ ሲሯሯጡ ይታያል።
ለስድስት አስርት ዓመታት ያህል የመረጋጋት፣ የመግባባት እና የሥርዓት ምሳሌነቷን ላዳበረች አገር የታንዛኒያ የምርጫ አመፅ አስደንጋጭ ነበር።

ሳሚያ የጥቃቱን ሪፖርት ከተቀበሉ በኋላ “አገራችንን አናውጦታል” ከማለት ባለፈ መንግሥትም ትምህርት እንደሚወስድበት ገልጸዋል።
የደህንነት ተቋማት እርምጃ አገሪቱ ወደ አለመረጋጋት እንዳትገባ አድርጓል በማለትም ተከላክላለዋል።
“ተምረናል። ኮሚሽኑ ሁሉም ጥቃቶች የተቀናጁ፣ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው እና ወንጀል ለመፈጸም በሰለጠኑ እና መሳሪያዎች በተሰጣቸው ሰዎች የታቀዱ መሆናቸውን ነግረውናል” ብለዋል።
የተሳተፉት ሰዎች ዓላማ “የአመራር ክፍተት መፍጠር” እና አገሪቱን “አስተዳደር አልባ” ለማድርግ እንደሆነ በመግለጽ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አክለዋል።
ፕሬዝዳንቷ ከምርጫ በኋላ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ለመመርመር የወንጀል ምርመራ አካል መቋቋሙንም አስታውቀዋል።
ሱቆችን ሰብረው የገቡ፣ ንብረት የዘረፉ፣ መሠረተ ልማትን ያወደሙ እና ግድያ የፈጸሙትን እንደሚለይ ተናግረዋል።
“የሕፃናትን ሞት ይመረምራል፣ የጠፉ አስከሬኖችን በተመለከተ ምላሽ ይሰጣል፤ እንዲሁም ከሁከቱ አካባቢዎች ውጭ ያሉ ጉዳዮችን ጨምሮ የጠለፋ ክሶችን ይመረምራል” ብለዋል።
ዋናው የተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው ሪፖርቱ “መሸፋፈን” እንደሆነ እና “የአገዛዙን ወንጀሎች ለማጥራት የተደረገ ሙከራ” ሲል ገልጾታል።
ከ518ቱ ሟቾች መካከል 490 ወንዶች፣ 21 ልጆች እና 16 የደህንነት ተቋማት ባልደረቦች መሆናቸውን ኦትማን ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት ሳይነገራቸው አንዳንድ ሟቾች የተቀበሩ በመሆናቸው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስረድተዋል።
120 የደህንነት ተቋም ባልደረቦችን ጨምሮ ከ2,000 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
ተቃዋሚዎች እና የሃይማኖት ተቋማት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ተናግረዋል። አስከሬኖች ከሆስፒታሎች እንደተወሰዱ እና አንዳንዶቹ በጅምላ መቃብር እንደተቀበሩም ተዘግቧል።
ኦትማን እንዳሉት የጅምላ መቃብር አለ የሚባለው “ሊረጋገጥ አልቻለም” ከማለት ባለፈ አንዳንድ ምስሎችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ለማዛባት ጥቅም ላይ ውሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ለአመፅ መነሻ የሆኑ በርካታ ምክንያቶችን ለይቷል፤ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳዮችን በመጥቀስም የፖለቲካ ማሻሻያዎች፣ የሥራ አጥነት እና “የሀገር ፍቅር ማጣት” የሚሉትን ያካትታል።
ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች ዜጎች በተቃውሞዎች እንዲሳተፉ ለማሳመን እነዚህን ጉዳዮች ተጠቅመዋል ብሏል። ሠልፎቹ ሰላማዊም ሆኑ ሕጋዊ እንዳልሆኑ እና ለሕጋዊ ጥበቃ ብቁ እንዳልነበሩ አክሏል።
ዘጠኙ አባላት ያሉት ኮሚሽን በፕሬዚዳንት ሳሚያ ከተሾሙ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
ምርመራው “በተለይም መንግሥት በወንጀሎቹ ውስጥ ዋና ተጠርጣሪ በሆነበት ሁኔታ ገለልተኛ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
