ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

 የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት እጃቸው በካቴና ታስሮ በወታደሮች ታጅበው

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞውን የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ ዘመቻ ላይ የተሳተፈ የአሜሪካ ልዩ ኃይል አባል ምስጢራዊ ወታደራዊ መረጃን ተጠቅሞ በውርርድ ቁማር ተሳትፏል በሚል ተወንጅሎ ታሰረ።

የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ጋኖን ኬን ቫን ዳይክ ላይ መጀመርያ ክስ መስርቶ የነበረው በክሪፕቶ የሚታገዘው ፖሊማርኬት ላይ ምስጢራዊ መረጃን ተጠቅሞ ግብይት ፈጽሟል በሚል ነበር።

የፍትህ ቢሮው “ይህ በግልጽ ምስጢራዊ መረጃን ተጠቅሞ ገንዘብ ለማግኘት የተደረገ ሙከራ በመሆኑ በፌደራል ሕግ መሠረት ሕገ ወጥ ነው” ብሏል።

ቫን ዳይክ በሰሜን ካሮላይና በሚገኘው ፎርት ብራግ ተመድቦ የሚሠራ የአሜሪካ ጦር አባል ሲሆን በቁማርም 409,000 ዶላር አሸንፏል።

የአሜሪካ ጦር የቀድሞውን የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ማዱሮንና ባለቤታቸውን ሲሊያ ፍሎሬስን እአአ ጥር 3 ቀን በሌሊት በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ካራካስ ውስጥ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ኒውዮርክ ወስደዋቸዋል።

ከዚያም በኋላ በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በጦር መሣሪያና የአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው ቢደረግም ማዱሮ ግን ክደው ተከራክረዋል።

ቫን ዳይክ “ኦፕሬሽን አብሶሉት ሪቮልቭ” በመባል የሚታወቀውን የዘመቻውን ጊዜ እና ውጤት በተመለከተ ተወራርዷል በሚል ተጠርጥሯል።

ይህም “ትርፍ ለማግኘት በሚል የተደረገ ነው” ሲል የፍትህ ቢሮ ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ እንደ አውሮፓውያኑ በታህሳስ 26 2025 አካባቢ ቫን ዳይክ የፖሊማርኬት አካውንት ከፍቶ በማዱሮ እና ከቬንዙዌላ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ውርርዶች ላይ መሳተፍ መጀመሩን በመጥቀስ ይወነጅለዋል።

ስለ ዘመቻ ‘አብሶሉት ሪዞልቭ’ የወጡ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎችን እያወቀ ከ33,000 ዶላር በላይ ውርርዶችን አድርጓል በሚል ተከሷል።

ሐሙስ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለጠፈው መግለጫ፣ ፖሊማርኬት “በመንግሥት ምስጢራዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚቆምር ተጠቃሚን ስናገኝ፣ ጉዳዩን ወደ ፍትህ ቢሮ መራነው እና ለሚያደርጉት ምርመራ ትብብር አድርገናል” ብሏል።

ኩባንያው አክሎም “ምስጢራዊ መረጃን ተጠቅሞ ገንዘብ ማግኘት በፖሊማርኬት ቦታ የለውም። ዛሬ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ስርዓቱ እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው” ብሏል።

ቫን ዳይክ ሐሙስ ዕለት ምስጥራዊ የመንግሥት መረጃዎችን ለግል ጥቅም በሕገ-ወጥ መንገድ በመጠቀም፣ ይፋ ያልሆኑ መረጃዎችን በመስረቅ፣ ሸቀጦችን በማጭበርበር፣ ኢንተርኔትን ተጠቅሞ በማጭበርበር እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመፈጸም ክስ ተመስርቶበታል።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቶድ ብላንቼ “ወታደሮቻችን ተልዕኳቸውን በተቻለ መጠን ደህንነቱ በተጠበቀ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሳካት ለምስጢራዊ መረጃ የታመኑ ናቸው፤ እናም ይህንን በጣም ምስጥራዊ መረጃ ለግል የገንዘብ ጥቅም እንዳይጠቀሙበት ክልከላ ተደርጎባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“የትንበያ እና የውርርድ ቁማሮች በስፋት መጠቀም በአንጻራዊነት አዲስ ክስተት ነው፤ ነገር ግን የብሔራዊ ደህንነት መረጃን የሚከላከሉ የፌዴራል ሕጎች ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ይሆናሉ።”

በኒውዮርክ ዳኛ የሆኑት ጄይ ክሌይተን የግመታ ቁማሮች “ለግል ጥቅም ሲባል አላግባብ የተወሰዱ ምስጥራዊ ወይም ይፋ ያልሆኑ መረጃዎችን ለመጠቀም መሸሸጊያ አይደሉም” ሲሉ አክለዋል።

የፍትህ ቢሮ ባለሥልጣናት ቫን ዳይክ እንደ አገሪቱ ጦር አባል “ከወታደራዊ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ምስጥራዊ መረጃ በጽሑፍ፣ በቃላት፣ በምግባር ወይም በሌላ መንገድ በጭራሽ እንደማያጋልጥ፣ እንደማያሳትም ወይም አሳልፎ እነደማይሰጥ” ቃል በመግባት የፈረመበት ሰነድ መኖሩን ተናግረዋል።

የፌዴራል አቃቤ ሕጎች እአአ ከታህሳስ 8 2025 እስከ ቢያንስ እስከ ጥር 6 2026 ድረስ ቫን ዳይክ በዘመቻ ‘አብሶሉት ሪሶልቭ’ ዕቅድ እና አፈፃፀም ውስጥ ተሳትፏል ብለዋል።

በዚህም የተነሳ ምስጥራዊ መረጃዎችን የማግኘት ዕድል ነበረው ሲሉ ወንጅለውታል።

የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል ኤጀንሲ አካል የሆነው ‘ዘ ኮሞዲቲ ፊውቸርስ ትሬዲንግ ኮሚሽን’ (ሲኤፍቲሲ) ቫን ዳይክ በሚመለከት ምስጢራዊ መረጃዎችን ተጠቅሞ የውርርድ ቁማር ላይ ተሰማርቷል በሚል ክስ መመስረቱን አስታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በውርርድ ቁማር ላይ በመሳተፉ ስለተከሰሰው ወታደር ሲጠየቁ ምንም እንዳልሰሙ ነገር ግን ጉዳዩን እንደሚከታተሉት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ የግመታ ቁማሮች ወደ ምስጢራዊ መረጃዎች ገበያ ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ስለመኖሩ ሲጠየቁ፣ “በእነዚህ ነገሮች ደስተኛ አይደለሁም” ሲሉ መልሰዋል።

“ዓለም በሙሉ በሚያሳዝን ሁኔታ የቁማር ጨዋታ ሆኗል፤ እናም በዓለም ዙሪያ፣ በአውሮፓ እና በሁሉም ቦታ ምን እየተከናወነ እንዳለ ስትመለከቱ፣ እነዚህን የውርርድ ቁማሮች እያከናወኑ ነው” ብለዋል።

“እኔ ግን ብዙም አልደግፈውም።”