ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group
ቴዲ አፍሮ _ Ethipoian News Amharic

ቦርከና ዜና

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ስቱዲዮ ትናንት ምሽት በታጠቁ አካላት መዘረፉን የቅርብ መረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሲኤምሲ (CMC) ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ይህ የአርቲስቱ የሥራ ቦታ፣ ዝርፊያው የተፈጸመበት ትናንት ሐሙስ ምሽት ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ እንደነበር ተገልጿል።

እንደ መረጃ ምንጮቹ ገለጻ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በታቀደ መልክ ሲሆን፣ መሣሪያ የታጠቁና በተሽከርካሪ የመጡ ግለሰቦች በስፍራው የነበሩ ጠባቂዎችን በኃይል በመደብደብ ጉዳት አድርሰውባቸዋል ተብሏል።

ታጣቂዎቹ ስቱዲዮውን ሰብረው በመግባትም አርቲስቱ ለሙዚቃ ሥራው፣ ለልምምድና ለቅንብር የሚጠቀምባቸውን በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ንብረቶች ዘርፈው ወስደዋል።

– Advertisement –

Advertise here _ borkena

ይህ ዝርፊያ እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ አርቲስቱ ለዓመታት የለፋባቸውና እስካሁን ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ በርካታ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎች፣ ግጥሞችና ዜማዎች በዚሁ ስቱዲዮ ውስጥ መገኘታቸው ነው።

ቴዲ አፍሮ አብዛኛውን ጊዜውን በዚሁ ስቱዲዮ ውስጥ በሥራና በልምምድ እንደሚያሳልፍ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለሌሎች አርቲስቶች የሚሰጣቸው ግጥሞችና ዜማዎችም በዚህ ጥቃት ሳቢያ አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ስጋት ደቅኗል።

ምንም እንኳን አርቲስቱ «ኢቶሪካ» የተሰኘው አዲስ አልበሙን ለሕዝብ ባደረሰበት በዚህ ወቅት፣ የሥነ-ልቦና ጫና የሚፈጥሩ ወከባዎች በአካባቢው ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በአሁኑ ወቅት ግን አርቲስቱ በደኅና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተረጋግጧል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከጸጥታ አካላት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

– Advertisement –

Advertise here _ borkena

__

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

Ethiopian NewsBorkena English