ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group

ሙሉጌታ ቢያዝን
(ክፍል ሁለት)

ከምርጫ በፊት ሽግግር እና/ ወይም ንግግር የሚለው ትልቅ ሀሳብ ሲነሣ ሲጣል ሰንብቷል፤እየተነሣም ያለ ይመስለኛል፡፡ይህን ሀሳብ ባመነዠኩት፣ባሰላሰልኩት ቁጥር አንድ ታሪክ ከትውስታዬ ጓዳ ብቅ ይልብኛል፡፡

ከፊት ለፊት ወንዝ አለ-ሰው መብላት የለመደ፡፡ ወንዙን ታክካ አንድ ጀልባ ቆማ ትታያለች፡፡ ከጀርባ የተራበ ጅብ ድምፅ ይሰማል፡፡ጀምበር ወደቤቷ ለመግባት እየገሠገሠች ነው፡፡ ሁለት ተጣልተናል ብለው የሚያስቡ/የተኮራረፉ ወይም የተጣሉ ሰዎች ከወንዙ ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል፡፡ ሁለቱም ወንዙን ለመሻገር ቋምጠዋል፡፡  ጀልባዋ አንድ ሰው ብቻውን ከተሳፈረ የማዕበሉን ግፊት መቋቋም ስለማትችል መገልበጥ ዕጣ ፈንታዋ ነው፡፡ ሁለቱ  ሰዎች ይህ ገብቷቸዋል፡፡ ወደ ጀርባ ቢገላመጡ የሚመጣ ሰው ጠፋ፡፡ ከጀርባ የጅቡ ድምፅ እየቀረበ ነው፡፡ ፈጥነው ካልተሳፈሩ በጋራ መሞታቸው ነው፡፡ መወሰን አለባቸው፡፡ 

ጅል ካልኾኑ በቀር ‘ጅቡ ከሚበላን በልተነው እንቀደስ’ ሊሉ አይችሉም፡፡ 

– Advertisement –

Advertise here _ borkena

ጅል ካልኾኑ በቀር ዕጣቸውን በወረቀት ሸብልለው ‘ዕጣ የወጣለት የጀልባዋን መሪ ጨብጦ ይሻገራል’ ሊሉም አይችሉም፡፡ 

አማራጩ ሁለት ነው፡፡  

መጀመሪያ ‘ጥላችን እንዴት እንደጀመረ፣ በማን እንደተጀመረ፣ ጥፋተኛው ማን እንደኾነ ካልተማመንን/ካልተነጋገርን መሻገር አንችልም’ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህን ካሉ ለጅቡ እራት ለመኾን ወስነዋል ማለት ነው፡፡ ‘ላትጎዳኝ ማልልኝ’ መባባል ከጀመሩም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም ጋ እውነት ሊኖር ይችላል፡፡ [ካሕሊል ጅብራን Say not ‘I have found the truth,’ rather, ‘ I have found a truth.’] እንዲል ችግሩ የሚመጣው የኔ ብቻ ነው እውነት ስንል ይመስለኛል፡፡

የቀረው ብቸኛ አማራጭ ይህ ነው፡-ወንዙን እንሻገርና እንነጋገራለን፡፡

– Advertisement –

Advertise here _ borkena

ሁለቱም (ንግግርም ሽግግርም) ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄው የቱ ይቅደም የሚለው ነው-ቅደም ተከተል (priority)፡፡

ከጀርባ የጅቡ ድምፅ እጅጉ መቅረቡን የታዘበው አንደኛው ሰው እግሩን ወደጀልባው ሲያስገባ ሌላኛውም እያጉተመተመ ተከተለው፡፡ 

ዘይደዋል፡፡ 

በጋራ ከመሞት በጋራ መዳን የተሻለ ብቻ ሳይኾን ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ 

– Advertisement –

ለመቧቀስ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ሰዋዊ ነው፤ የሚጠበቅ ነው፡፡ ግን ‘ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡’ ለመቧቀስም መጀመሪያ መኖር ግድ ነው፡፡ ሕልውና የቅድሚያ ቅድሚያ ነው ሲባል በምክንያት ነው፡፡ 

ጀልባዋ ሚዛኗን ጠብቃ ሽር የምትለው ውኃውን ቆንጥጦ ሊይዝ የሚችል ክብደት ስትጫን ብቻ ሳይኾን አንዱ መልህቁን ሲጨብጥ ሌላኛው መሪውን መዘወር ስላለበት ነው፡፡

ጅቡን ወደኋላ ትቶ ወደ ወደቡ (ተስፋይቱ ምድር) ማተኮር ካልተቻለ ውጤቱ ሁለት ነው- አንድም በወንዝ አለያም በጅብ መበላት፡፡ 

‘ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት’ አያዋጣም፡፡ ክፉ ሐሳብ ወደ ወንዝ መጣልን እንደሚያመጣ ከዮናስ ታሪክ ያልተማረ ብቻ ነው፡፡ ጅቡን “ና ብላኝ” ብሎ እንደመጣራት ያለ ስለኾነ ሳልም አይበጅም ፡፡ 

ሁለቱ ተጣልተናል ብለው የሚያስቡ/የተኮራረፉ ወይም የተጣሉ ግለሰቦች ውክልናቸው የተለያዩ አመለካከቶች ቢኾኑም እንደ ግለሰብ ብናያቸው ወደ ጀልባው ሲገቡ ሳይነጋገሩ፣ቃላት ሳያባክኑ ተግባብተዋል፡፡

 ቅራኔን ከመፍቻ ዘዴዎች ውስጥ ‘ከነገሩ ጦም ይደሩ’ (Avoiding/withdrawal)፣ 

‘አንተ እንዳልክ’ (Accommodating)፣

 ‘እኔ ይሄን እተዋለሁ፤ አንተም ይሄን ተው’ (Compromising)፣ 

’ለእኔ ብቻ’ን (Competing) አልፈው ዋናው ‘መተባበር’ (Collaborating) ጋ ደርሰዋል፡፡ 

ይህ ማለት ቅራኔያቸው ለዘለቄታው ተፈትቷል ማለት አይደለም፡፡ ‘ለምጣዱ ሲባል አይጧ’ እንድታልፍ ተስማምተዋል፣ፈቅደዋል ማለት እንጂ፡፡ 

አይጧ በምዕራብ ወይም በምሥራቅ፣ በደቡብ ወይም በሰሜን ልታልፍ ትችላለች፡፡ በምጣዱ አናት ወይም በጉልቻ መካከል ሾልካ ልታልፍ ትችላለች፡፡ ‘በዚህ በኩል ነው ማለፍ ያለባት’ በሚል ግርግር ከፈጠርን ወይም በአይጧ ጾታ ላይ ክርክር ከገጠምን አይጧን አስደንብረን ምጣዱን እንደትሰብር መጋበዝ ነው፡፡ 

እንጀራ ይጋገርበታልና ምጣዱን መስበር ራስን እንደማጥፋት ያለ ይመስለኛል፡፡ ወደቡ ላይ ከደረሱ በኋላ ንግግሩ ሲጀመር የማይነካውን መንካት እንደማይቻል በግልጽ ካልተቀመጠ ምጣዱን ለመስበር ዕቅዳችንን አሳደርነው እንጂ (Tactical alliance) ምጣዱን ከመሰበር አልጠበቅነውም፡፡ ‘ኦሮማራ’ን ያየ በጊዜያዊ ትብብር (Tactical alliance) ቢበረይ ማን ይፈርድበታል?!

‘የለም የራሴ ምጣድ ያሻኛል’ ለማለትም በደንብ የተሟሸው ምጣድ በወጉ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ‘ዳስ ጥለን’ መቆዘም ሳይኾን መምከር የሚገባው ለዚህ ነው፡፡

‘ለዛሬ ብቻ አይጧ ትለፍ’ ወንዝ አያሻግርም፡፡ ከ’መተባበር’ (collaboration) ወደ ‘ለኔ ብቻ’ (Competing) ከተመለስን ከስረናል፡፡ “…መጀመሪያውኑም እንዴት አብረው ቆሙ፤ የውሸት ነው ብለን ነበር” ለሚሉቱ ጥሩ መሳለቂያ መኾን ነው፡፡ 

ምጣዱ እንዳይሰበር ላንዱ ወይም ለሌላው የማያደሉ፣ላንዱ ወይም ለሌላው የማያጋድሉ በሁለቱም ወገን የታመኑ ሐቀኛ አባመላዎች (Third-Party Intervention) የሚያስፈልጉት እዚህ ጋ ነው፡፡ 

ተጣልተናል ብለው የሚያስቡ/የተኮራረፉ ወይም የተጣሉ ሰዎች ጀልባው ላይ ያሳዩትን የትብብር ልምድ ወደቡ ላይ ሲደርሱም ሊደግሙት/ሊደጋግሙት ብሎም ባሕል ሊያደርጉት ይገባል፡፡ 

 ‘ትናንት እንዲያ ብለህ ነበር’ እያሉ ስሕተት መልቀም ጅቡን እንደ መጥራት ያለ ነው፡፡ ማንን ቀድሞ እንደሚበላ የሚያውቀው ደግሞ ጅቡ ብቻ ነው፡፡

ወደ ኃላ እየተመለከቱ ወደፊት መራመድ ከቶ አይቻልም፡፡ ሁለቱ ሰዎች ወንዙን ተሻግረው ወደ ወደቡ ሲደርሱ ቅራኔያቸውን ቁጭ ብለው መፍታት ቀዳሚ ተግባራቸው ሊኾን ይገባል፡፡ ቅራኔያቸውን መፍታት ከተሳናቸው ምክንያታቸው ከሚከተሉት ባንዱ ላይ ማረፉ እርግጥ ይኾናል፡፡ 

አንድም ፍቅራቸው ጥላቻቸውን ማሸነፍ ተስኖታል ወይም ቂማቸው ተስፋቸውን በልጦታል፡፡ አንድም ላለፈ ትናንትናቸው ዛሬና ነገአቸውን አጋድመው ለማረድ ወስነዋል ወይም ላለፈ ክረምታቸው ቤት ለመሥራት ቆርጠዋል፡፡ አለያም በቆሙበት ማእዘን ላይ ተቸክለው ‘እውነቱ ያለው እኔ ጋ ብቻ ነው’ ብለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ በ ‘ሽግግር’ና በ’ንግግር’ ፈንታ ‘ግርግር’ ስፍራውን ያለ ከልካይ ይረከባል፤ “ፍች የታጣለት የሀገራችን የፖለቲካ ቅኔም” በቅኔነቱ መዝለቁ ይቀጥላል፡፡

ያሰንብተን!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian NewsBorkena English

ኤክስ ፡ @zborkena