ልደቱ አያሌው-3ኛ መንገድ ·Follow

ሚያዚያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም

ለመገናኛ ብዙሃን

ጉዳዩ፦ ይቅርታ መጠየቅን ይመለከታል

በትናንትናው እለት በሀሳብ-ገበታ ሚዲያ ላይ ከአቶ አሉላ ሰለሞን ጋር የነበረኝን ውይይት ወይም ውዝግብ በተመለከተ

በርካታ አስተያዬቶች ደርሰውኛል።

የመጀመሪያው አስተያዬት፣ ከማይመጥንህ ሰው ጋር (ከአሉላ ጋር) ለምን ቀረብክ? የሚል ነው።

እኔ በዚያ መድረክ ላይ የቀረብኩት፣ አቶ አሉላ ሰለሞን የተካሄደው ትዕይንተ-ህዝብ ውጤታማ እንዳልሆነ፣

ትዕይንተ-ህዝቡን ያካሄደው የጋራ-መድረክም ጦርነት ለማካሄድ የሚፈልግ፣ ከጀርባም በህወሓትና በሻዕቢያ የሚመራ ድርጅት እንደሆነ አድርጐ አደገኛ የሀሰት ክስ ስላቀረበ ነው እንጂ አቶ አሉላ የሚመጥነኝ ወይም የማይመጥነኝ ሰው

ስለሆነ አይደለም።

በአንድ ተዋቂ የሆነ መገናኛ ብዙሃን ላይ አንድ በአወንታም ይሁን በአሉታ የሚታዎቅ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የብልጽግና አገዛዝን የሀሰት ክስ የሚያጠናክር ከባድ ውንጀላ ሲያቀርብ በዝምታ ወይም በንቀት ማለፍ ተገቢ የፖለቲካ አካሄድ ነው ብዬ አላምንም።

በተለይም በትዕይንተ-ህዝቡ ላይ ተናጋሪዎቹን በመጋበዝ እረገድ የራሱ ሚና ለነበረው ለእኔ አይነቱ ሰው በጋራ-መድረኩ ላይም ሆነ በተናጋሪዎቹ ላይ የቀረበውን የሀሰት ክስ የማስተባበል ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት።

በዚህ እረገድ እየቀረበ ያለው አስተያየት ከበጐነት የሚመነጭ መሆኑን ባልጠራጠርም የጉዳዩን ክብደትና የሚያስከትለውን ውስጣዊና ውጫዊ ጣጣ በውል ካለመረዳት የሚቀርብ አስተያዬት ነው ብዬ አምናለሁ።

ሁለተኛው አስተያዬት፣ “ለህውሓት ወገንተኛ ሆነህ ቀርበሀል” የሚል የተለመደ ትችት ነው።

እኔ በዚያ መድረክ ላይ ለመቅረብ የተገደድኩት የጋራ መድረካችንም ሆነ እኔ በተለዬ ሁኔታ ከህወሓት ጋር ተባብረን እንደምንሰራ ተደርጐ የቀረበውን የሀሰት ክስ እውነት እንዳልሆነ ለማስተባባል ነው።

በተግባር ያደረግሁትም ይህንኑ ነው። ይህንን ማድረጌን

በተቃራኒው ለህወሓት ጠበቃ መቆም እንደሆነ አድርጐ የሚያይ አካል ካለ ችግሩ የሱ እንጅ የኔ አይደለም። በዚያ

ውይይት ላይ ህወሓትን አስመልክቶ የሰጠኋቸው አስተያየቶችም በሙሉ እውነት ናቸው ብዬ የማምንባቸውና ኃላፊነት የምዎስድባቸው ናቸው።

ይህ ትናትም ሆነ ዛሬ ያለኝ፣ ወደፊትም የሚቀጥል አቋሜ ነው። በህወሓት ላይ ያለኝን ምክኒያታዊ አቋሜን ትቸ እንደሌሎች ጭፍን ጥላቻ እስካላራመድኩ ድረስም እንዲህ ዓይነቱ ያልተገባ ፍረጃ እና ክስ በእኔ ላይ ወደፊትም ተደጋግሞ መቅረቡ እንደማይቀር ጥርጥር የለኝም።

ሶስተኛው አስተያዬት፣ በውይይቱ ወቅት ስሜታዊ ሆነህ አላስፈላጊ ኃይለ-ቃል መናገርህ ስህተት ነው የሚል ነው። ይህ

ተገቢና ጤናማ ትችት ነው ብዬ አምናለሁ። ሆን ብዬ አቅጀ ያደረግሁት ባይሆንም የሀሰት ፍረጃውና ፍረጃውን እውነት

ለማስመሰል የሚካሄደው ሴራ ክብደት በድንገት ስሜታዊ አድርጐኝ በኃይለ-ቃል መናገሬ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ።

በዚያ ምክኒያት ቅሬታ ለተሰማችሁ ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

እንዲህ ዓይነት አስተያዬት የሰጣችሁኝም ለእኔ ካላችሁ ክብርና በጐ አስተሳሰብ ነው ብዬ ስለማምን ከልቤ አመሰግናለሁ።

ልደቱ አያሌው