Abbay TV

ሂውማን ራይትስ ዎች በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አድሏዊ አሰራር ተዘርግቷል በሚል ያወጣውን ሪፖርት ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ አጣጣሉ

ዓባይ ዜና፡ ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ አድሏዊ አሰራር ተዘርግቷል ማለቱን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ከእውነት የራቀ ሲሉ አስተባብለውታል፡፡

ውንጀላውን “ከእውነት የራቀ” እና “ወገንተኛ” ሲሉ ያጣጣሉት ከለኔል ደመቀ ድርጅቱ በእርሳቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው መጠየቁን በሚመለከት ሲመልሱም “እኔ ወንጀለኛ አይደለሁም” ብለዋል።

“በዞኑ ውስጥ የትግራይ ሰዎችን በማንነታቸው የሚገፋ አስተዳደር የለንም” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ “ሂውማን ራይትስ ዎች ከዚህ በፊትም እኛን ለመወንጀል ሞክሮ እንደነበር እናውቃለን” ሲሉ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የትግራይ ተወላጆች መታወቂያ እንዳያወጡ እየተደረጉ ነው በሚል ለወጣው ሪፖርት ምላሽ የሰጡት ኮሎኔል ደመቀ “እኛ እንደሱ አላደረግንም፣ እንደማንኛውም ሰው የነዋሪነት መታወቂያም፣ ፋይዳም እንዲያወጡ አመቻችተናል” በማለት መልሰዋል፡፡

“የአንድ ወገን ደጋፊ” ይመስላል ባሉት የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት “ማዘናቸውንም” ገልጸዋል።

ሪፖርቱ በአካባቢው አሁን ያለውን ሁኔታ አያንጸባርቅም ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ሂውማን ራይትስ ዎች በጉዳዩ ላይ እርሳቸውንም ሆነ አስተዳደራቸውን አለማነጋገሩን በመጥቀስ አድሏዊነቱን ጠቁመዋል፡፡

አስተዳደሩ ገለልተኛ የሆነ አካል በአካባቢው ተፈጽሟል የሚላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አጣራለሁ የሚል ከሆነ ፈቃደኛ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ይህን የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ውድቅ አድርጎታል።

አስተዳደሩ በመግለጫው፣ ሪፖርቱ በቂ ካልሆነ የናሙና ቁጥርና በውጭ ከሚገኙ የጥቅም ተሟጋች ቡድኖች በተገኘ መረጃ የተጠናቀረ በመሆኑ ተዓማኒነት የለውም ብሏል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ በበኩሉ የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት “ተዓማኒነት ያለው የሰብአዊ መብት ግምገማ ሳይሆን በምርጫ የተቀረጸ፣ በታሪክ የተዛባ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው አደገኛ አጀንዳ ሆኖ የሚያገለግል ሰነድ ነው” ሲል እንደማይቀበለው አሳውቋል።