
ከ 5 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ
ትናንት እሁድ በለንደን የተካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን የበላይነት የያዙበት ነበር። በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ የራሷን ክብረ ወሰን በማሻሻል ኬንያውያንን አስከትላ አሸንፋለች።
በወንዶች ውድድር ደግሞ ኬንያዊው ሳባስቲያን ሳዌ እና ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጄልቻ ከሁለት ሰዓት በታች ተከታትለው በመግባት ዓለምን አስደምመዋል።
በለንደን ማራቶን ኬንያዊው አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ በወንዶች ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
የ30 ዓመቱ ኬንያዊ ሰባስቲያን ሳዌ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 1 ሰዓት 59.30 ደቂቃ ብቻ ወስዶበታል።
ይህም ማለት ኬልቪን ኪፕቱም እንደ አውሮፓውያኑ በ2023 በ2:00:35 በማስመዝገብ ከያዘው ክብረ ወሰን በአንድ ደቂቃ የፈጠነ ነው።
በዓለማችን ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች እንደሚሮጥ ያሳየው እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ነው።
ነገር ግን ይህ ክብረወሰን የተገኘው ይፋዊ ባልሆነ እና ቁጥጥር በተደረገበት ሁኔታ ውስጥ ስለሆነ አልተመዘገበለትም።
በለንደን ማራቶን ሌላው አስደናቂው ነገር ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጄልቻም በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት መሆኑ ነው።
ዮሚፍ ውድድሩን ያጠናቀቀው 1:59:41 በመግባት ነው።
ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ በሴቶች ማራቶን የራሷን ክብረ ወሰን በማሻሻል 2:15:41 ገብታለች።
የማራቶን ውድድርን ከኢትዮጵያ እና ኬንያ የተገኙ ሯጮች እንዴት ነገሱበት?

በምሥራቅ አፍሪካ በዘመናዊ ጫማ መሮጥ
ልክ እንደሌሎች ብዙ ስፖርቶች የረዥም ርቀት ሩጫ በስልጠና ስርዓቶች፣ በአመጋገብ እና በመሳሪያዎች መሻሻል ተጠቃሚ ሆኗል።
በተለይም ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ተወዳዳሪዎች ፈጣን ውጤቶችን ከሚያስገኙ፣ በክብደት ቀላል ከሆኑ እና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ከታከለባቸው ጫማዎች በብዙ ተጠቅመዋል።
ለምሳሌ የወንዶች የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከአራት ደቂቃዎች በላይ ተሻሽሏል። በሴቶችም ዘንድ በተመሳሳይ ፍጥነት የተከሰተ ነው።
እነዚህን የማራቶን ክብረ ወሰኖች ልዩ የሚያደርጋቸው ውጤቶቹ የተመዘገቡት በተመሳሳይ የውድድር መስክ ከጥቂት አገራት በመጡ አትሌቶች መሆናቸው ነው።
ባለፉት አምስት ኦሎምፒኮች የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ከ800 ሜትር ጀምሮ በተካሄዱ የሩጫ ውድድሮች አብዛኛዎቹን ሜዳሊያዎች አሸንፈዋል።
በወንዶች ማራቶን ውድድር ከ20ዎቹ ፈጣን ሯጮች ውስጥ ሁለቱ ብቻ በኬንያዊ ወይም በኢትዮጵያዊ ሯጭ አልተመዘገቡም።
በሴቶች ማራቶን ውድድር ከ20ዎቹ ፈጣን ሯጮች ውስጥ 18ቱ ከእነዚህ ሁለት አገሮች የመጡ አትሌቶች ናቸው።
ለአሸናፊነታቸው ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የሚገኘው ተራራማ አካባቢ አንዱ ነው።
ከኬንያም ሆነ ከኢትዮጵያ የመጡት አብዛኛዎቹ ታዋቂ ሯጮች የተገኙት ከዚያ አካባቢ ነው።
ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከባህር ወለል በላይ ከፍታ ባላቸው ከተሞች እና መንደሮች የሚኖሩ ሯጮች፣ በተለይም እዚያ የተወለዱት፣ ከፍተኛ ከፍታ ባላቸው ቦታዎች እና ዝቅተኛ የኦክስጅን መጠን ባለበት ስፍራ ልምምድ ሲያደርጉ የልብና የሳንባ ጥንካሬን ያዳብራሉ።
ይህ በእርግጥ ለስኬት ዋስትና አይሆንም። እንደ ኔፓል እና ቦሊቪያ ባሉ ተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ያሏቸው አገሮች አሉ።
ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ሯጮች ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ማሳደር አልቻሉም።
ኬንያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን የሚለያቸው ሩጫ በትውልዶች መካከል በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መቀረጹ ነው።

ባሕል እና ፍላጎት
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ሯጭ ኃይሌ ገብረስላሴ ልጅ በነበረበት እና ረዥም ርቀት በእግር መጓዝ ልማድ ከነበረበት ዘመን ወዲህ በአፍሪካ በከፍተኛ ፍጥነት ከተሜነት እና ከተማ ማደጉን አስተውሏል። ነገር ግን ሩጫ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ዘንድ የባሕሉ አካል ሆኖ ቀርቷል።
በኬንያ ለብዙ ዓመታት የኖረውና የሠራው የቀድሞ የስፔን ሯጭ ማርክ ሮይግ፣ ልጆቹ በተማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ሩጫ ሲያወራ ሌሎች ወላጆች ያለመደነቅ ይሰሙት እንደነበር ያስታውሳል። ሮይግ እየቀለደ ሩጫ ባሕል በሆነበት አገር “ከእንግዲህ እዚያ ሯጭ ነኝ አልልም” ይላል።
ስፔናዊው በአሁኑ ጊዜ ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ በስተሰሜን 260 ኪ.ሜ. እና ከባህር ጠለል በላይ 2400 ሜትር ከፍታ ላይ በምትገኘው ኢተን ከተማ ውስጥ ታዳጊ ሯጮችን የሚያሰለጥን ፕሮጀክትን በበላይነት ይቆጣጠራል።
ኢተን በአካባቢው “የአሸናፊዎች መኖሪያ” በመባል ትታወቃለች። ምክንያቱም የኦሎምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊዎችን ጨምሮ ለብዙ ታዋቂ የኬንያ ሯጮች መገኛ ስፍራ ናት።
ሮይግ እንደሚለው የአካባቢው ታዳጊዎች ዝናቸው በየዕለቱ የሚነገርላቸው ውጤታማ አትሌቶች የኖሩት በአቅራቢያቸው ነው።
ጎዳናዎቹ እነዚህ ብርቅዬ አትሌቶች የሮጡበት መሆኑ ይህም በየዕለቱ በሚሰሙት የውጤታማነት ታሪክ መታጀቡ እነርሱንም ወደ ሩጫ እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል።
በተለይም ድህነት አሁንም ብዙዎችን እግር ተወርች በያዘበት አገር እና አህጉር ውስጥ መሆን ጥሩ ገንዘብ የማግኛ ተስፋም ይሆናል።
“ልክ በብራዚል እና አርጀንቲና ያሉ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የሚገኙ ልጆች የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን እንደሚመኙት ሁሉ፣ ኬንያውያንም በአትሌቲክስ ዘርፍ መተዳደሪያቸውን ለማድረግ ያልማሉ። እናም ብዙ አርአያዎች በመኖራቸው ሕልማቸውንም ወኔያቸውንም ያሞቀዋል” በማለት ሮይግ ያስረዳል።

ሳዌ የመጀመርያው ነው ማለት የማንችለው ለምንድን ነው?
በጉግል ላይ “የ2 ሰዓት ማራቶን” (2-hour marathon) የሚለውን የሚፈልግ ሰው የኢሉድ ኪፕቾጌን መረጃ ያገኛል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በቪየና በተዘጋጀ ልዩ ሩጫ ማራቶንን 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃ፣ ከ40 ሰከንድ ሮጧል።
ከሁለት ዓመት በፊት ናይክ በጣሊያን ሞንዛ ከተማ ባዘጋጀው ውድድር ላይም ኬንያዊው ይህንን ለማሳካት 26 ሰከንዶች ብቻ ቀርተውት ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ድሎቹ የተመዘገቡት በመደበኛ ውድድር ላይ በማይገኙ ሁኔታዎች ውስጥ ነው። ለምሳሌ ኪፕቾጌ ተራ በተራ ፍጥነቱን ለማስተካከል ከጎኑ በሚሮጡ አሯሯጮች ታጅቦ ነበር።
ኬንያዊው የሚጠጣውን የሚያቀብሉት በብስክሌት የሚከተሉት ሰዎች ነበሩ። ይህ ደግሞ በተለመደው ውድድር ውስጥ በአንድ ስፍራ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠን አንስቶ ከመጠጣት በእጅጉ የተለየ ነበር።
ኢሉድ ኪፕቾጌ በውድድሩ ላይ በመሳተፉ ብቻ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ስለተከፈለው ክብረ ወሰኑ ይፋዊ ሆኖ ባለመመዝገቡ ብዙም አልተጨነቀም። አብሮት የሠራው ብሪታኒያዊው የስፖርት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር አንድሪው ጆንስ እንዲሁ የክብረ ወሰኑ መመዝገብ ብዙም ግድ አልሰጠውም።
“በግሌ፣ ውጤቱ ይፋዊ አለመሆኑ ግድ አይሰጠኝም። በስፖርቱ ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ሰዎች ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ይቻል እንደሆነ ማወቅ ፈልገው ነበር፤ እናም ይህ የሚቻል መሆኑን አረጋግጠናል” ሲሉ የኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በቁጥጥር በሚደረግበት ከባቢ ውስጥ ቢሆንም፣ ኪፕቾጌ ውጤቱ እንዲሳካ አስደናቂ ብቃት ማሳየት ነበረበት።”

የሰውነት ጡንቻን መግራት
ከዝነኞች ጋር ማራቶንን መሮጥ ማንም ከሚያስበው በላይ እጅግ ከባድ ነው። እአአ በ2023 ኬልቪን ኪፕቱም አንድ ኪሎ ሜትርን በ2 ደቂቃ ከ51 ሰከንዶች ሮጧል። ነገር ግን የዓለም አትሌቲክስ በ2019 ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ከሆነ አንድ ወንድ ሯጭ አንዱ ኪሎሜትርን ለመጨረስ በአማካይ 6 ደቂቃ ከ43 ሰከንዶች ይፈጅበታል።
ፕሮፌሰር ጆንስ እንደሚሉት፣ ይህ በሰውነት ጡንቻ ላይ ከባድ ቅጣት ሳይጣል የሚመጣ አይደለም።
“በከፍተኛ ብቃት ለመሮጥ ረዥም ርቀት ነው፤ ሯጩ በየትኛውም ደረጃ ላይ ይሁን የሰውነት ጡንቻ ቅጣት መቀበሉ አይቀሬ ነው። እንዲሁም የአእምሮ ጫናም አለ።”
አትሌቶች በሳምንት ቢያንስ 160 ኪ.ሜ የሚሮጡበት ከባድ ስልጠና ከጡንቻዎች፣ ከአጥንቶችና ከመገጣጠሚያዎች ጋር ተያይዞ የሚደርሰው ጫና ስም እና ዝና ያላቸው ሯጮች በዓመት ከሁለት በላይ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የማይችሉበትን ምክንያት ያስረዳል።
ሯጮቹ ከስምጥ ሸለቆ መገኘታቸው
ምንም እንኳ ኢሉድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ለመሮጥ ተመራጭ አትሌት ቢሆንም፣ ባለሙያዎች ግን ሌላ የማይጠበቅ ሯጭ ከስምጥ ሸለቆ እጅን በአፍ የሚያስጭን ድል ያስመዘግባል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ባለሙያዎቹ ኬልቪን ኪፕቱምን በምሳሌነት በማንሳት እአአ በ2023 ለሦስተኛ ጊዜ በሮጠው የማራቶን ውድድሩ አስደናቂ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል ይላሉ።
የቀድሞው ሯጭ ኬንያዊው ማርቲን ኬይኖ እአአ በ2024 ለቢቢሲ “በስምጥ ሸለቆ ገና ያላየነው እና ያልሰማነው ምርጥ ሯጭ ሊኖር ይችላል። በጣም በርካታ አቅም እና ተሰጥኦ ያላቸው ሯጮች አሉ” ብሎ ነበር።
ሳዌም በእርግጥ ያንን አድርጓል። በሪፍት ቫሊ የተወለደው የ31 ዓመቱ ወጣት በለንደን ክብረ ወሰን የሰበረበት ሩጫ አራተኛ የማራቶን ውድድሩ ነበር።
ነገር ግን ምልክቶቹ አስቀድመው ነበሩ። ሳዌ ቀደም ሲል የተካፈለባቸውን ሦስት ውድድሮች አሸንፏል፤ ነገር ግን ድሎቹ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተገኙ አልነበሩም።

ሴቶቹ “የማይቻል” የሚባለውን የጊዜ ገደብ ሰብረዋል?
በ1970ዎቹ ነው ሴት ሯጮች እንደ ኒውዮርክ ማራቶን ባሉ ዋና ዋና የጎዳና ላይ ውድድሮች እንዲወዳደሩ የተፈቀደው።
በ1980ዎቹ ደግሞ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸዋል።
ቦታ አልተሰጣቸውም ቢባል ስህተት አይሆንም። ፈጣኑ ሰዓት እአአ ከ1971 እስከ 2002 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ2፡55 ወደ 2፡17 ወርዷል።
በ2019 የቺካጎ ማራቶን ኬንያዊቷ ብሪጂድ ኮሴይ ርቀቱን 2፡14፡04 በማጠናቀቅ ክብረ ወሰን ጨብጣለች።
ይህ ክብረ ወሰን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በተደረገው ወንዶችና ሴቶች አብረው በሚሮጡበት ውድድር እአአ በመስከረም 2023 በትዕግሥት አሰፋ (2፡11፡53) ተሰብሯል።
እንደ እውነቱ ከሆነ እአአ በ2015 በአሜሪካ የስፖርት ሳይንቲስቶች የሰሩት ጥናት እንዳመለከተው ሴቶች እአአ በ2003 የለንደን ማራቶን ውድድር ላይ የብሪታንያዋ ፓውላ ራድክሊፍ በ2፡15፡25 ያስመዘገበችው ሰዓት “የማይቻል” የሚባለው ነበር።
