
ከ 2 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር “ልዩ ግንኙነት” ያላት ብቸኛዋ ሀገር “ምናልባት እስራኤል” እንደሆነች በአሜሪካ የዩኬ አምባሳደር ተናገሩ።
ሰር ክርስቲያን ተርነር በየካቲት ወር ለትራንስአትላንቲክ ግንኙነት ተማሪዎች “ለጠቅላይ ሚኒስትሬ የምሰጠው ምክር ‘እጄን በጆሮዬ ደፍኜ ‘ልዩ ነው፣ ደህና ይሆናል ማለት አልችልም’ የሚል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህ አስተያየቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገቡት ማክሰኞ ዕለት በፋይናንሺያል ታይምስ ነበር።
ይህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት በኢራን ጦርነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ ከገባ በኋላ እና ንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ ወደ ዋይት ሐውስ ከመሄዳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ነው።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የግል እና መደበኛ ያልሆኑ አስተያየቶች” የመንግሥትን አቋም “በምንም ዓይነት መልኩ የሚያንጸባርቁ አይደሉም” ብሏል።
ሰር ክርስቲያን ከዩኬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ካደረጉት ስብሰባ ላይ ተቀድቶ በተለቀቀ የድምጽ ቅጂ ላይ “‘ልዩ ግንኙነት’ የሚለው አባባል ትዝታ የሚፈጥር፣ ወደኋላ የሚመለከት እና ብዙ ሸክም የሚፈጥር ስለሆነ ልገልጸው የማልሞክረው ነው” ሲሉ ይሰማሉ።
“ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ልዩ ግንኙነት ያላት አንድ አገር ያለች ይመስለኛል፥ እሷም ምናልባትም እስራኤል ናት” ብለዋል።
ይህ በዶናልድ ትራምፕ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር መካከል ያለው የሻከረው ግንኙነትን ለማጠናከር አሜሪካ ለደረሱት ለንጉሱ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
በቪዲዮው ላይ ሰር ክርስቲያን አሜሪካ እና ዩኬ “ጥልቅ ታሪክ እና ፍቅር” በተለይም በደህንነት እና በመከላከያ ረገድ እንደሚጋሩ እና ኢኮኖሚያቸው “በጣም የተቀራረበ” መሆኑን ገልጸዋል።
“ሌሎች ሁለት አገሮች በጋራ የማያደርጉት አብረን የምናደርጋቸው ነገሮችም አሉ።”
ዩኬ እና አሜሪካ “በመለያየት ጊዜ” ውስጥ እንዳሉ እንደማያምኑ ነገር ግን “በእርግጥ በአንድ ዘመን መጨረሻ ላይ ከመሆናችንም ባለፈ ዘመኑ እየተለወጠ ነው” ብለዋል።
“እኛ በአውሮፓ [ያለን] በአሜሪካ የደህንነት ጥላ ላይ ብቻ መተማመን አንችልም። ስለዚህ ከተፈለገ ልዩው ግንኙነቱ ሊቀጥል ይችላል፣ ነገር ግን የተለየ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ።
“ለጠቅላይ ሚኒስትሬ የምሰጠው ምክር ‘እጄን በጆሮዬ ላይ ጭኜ ልዩ ነው፣ ደህና ይሆናል ማለት አልችልም’ የሚል ሲሆን እኛም ማቅረብ የምንችለውን ነገር ለማሳየት በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ መስራት አለብን።”
በአንዳንዶች ጊዜ ያለፈበት የሚባለውን “ልዩ ግንኙነት” የሚለውን ሐረግ ዲፕሎማቶች ከእንግዲህ አይጠቀሙም ተብሎ ይታመናል።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃክ ስትራው ለቢቢሲ ሬዲዮ 4 ዘ ወርልድ ቱናይት ፕሮግራም ሰር ክርስቲያን እስራኤል ከአሜሪካ ጋር ልዩ ግንኙነት አላት ማለታቸው “ፍፁም ትክክል ነው” ብለዋል።
“ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል ወታደራዊ ወጪ፣ በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያዎች ላይ የምታወጣውን ጨምሮ፣ ድጎማ ታደርጋለች። እናም ይህ ብቻውን ግንኙነቱን ልዩ ያደርገዋል” ሲሉ ስትራው ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት “ልዩ ግንኙነት” የሚለውን ሐረግ በመጠቀም ረገድ ምቾት እንደማይሰማቸው” እና “ከጥቅም ውጭ” እንዲሆን ማድረግ እንደሚፈልጉ አክለዋል።
የቀድሞው የዩኬ አምባሳደር ሎርድ ዳሮች በበኩላቸው የተለቀቀውን ድምጽ “ክህደት” እና “ከፍተኛ የሆነ የእምነት ጥሰት” ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ ናይት ተናግረዋል።
“[ሰር ክርስቲያን] በዚህ ምክንያት ራሱን ይወቅሳል” ሲሉ አክለዋል።
ሰር ክሪስቲያን ስለ እስራኤል በሰጡት አስተያየት ዙሪያ ሎርድ ዳሮች ምላሽ ሲሰጡም “በዌስት ሚኒስተር ኮሪደሮች ውስጥ የሚደረግ ውይይት” ስለሆነ “ከዚህ ጋር የማይስማማ ሰው ማየት ከባድ ነው” ብለዋል።
እስራኤል በአሁኑ ጊዜ ከዩኬ ይልቅ በጣም ለአሜሪካ የቀረበች አጋር መሆኗ እውነት ነው። ሁለት አገሮች በአሁኑ ጊዜ በኢራን ጦርነት ጉዳይ ላይ ያልተግባቡ ሲሆን የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር በጦርነቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ሰር ክርስቲያን ባደረጉት ሰፊ ንግግር የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስታይን ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ “ማንንም ያልነካ” መሆኑን “ያልተለመደ” እንደሆነ ተናግረዋል።
በተቃራኒው በውዝግቡ ምክንያት የቀድሞውን ልዑል አንድሪው ማውንትባተን-ዊንሶርን እና በዋሽንግተን የዩኬ አምባሳደር የነበሩት ሎርድ ፒተር ማንዴልሰ “እንዳስወገዳቸው” ተናግረዋል።
ማውንትባተን-ዊንድሶር ከኤፕስታይን ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ስህተት እንዳልሠሩ ደጋግመው ገልጸዋል። ሎርድ ማንደልሰን በበኩላቸው ከኤፕስታይን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት በመቀጠላቸው ይቅርታ ጠይቀው “ስለ እሱ ያለውን ትክክለኛ እውነት” ያወቁት ከሞተ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአንዳንዶች ይህ የአሜሪካን የፖለቲካ እና የፍትህ ስርዓቶችን የመተቸት ጉዳይ መስሎ ቢታይም ስኬታማ ዲፕሎማት በፍጹም ሊከሰስበት የማይፈልገው ነገር ነው።
የጄፍሪ ኤፕስታይንን ስም መልሶ ወደ ትኩረት ያመጣዋል። ንጉሱ እና ንግሥቲቱ በአሜሪካ እያሉ ከኤፕስታይን ተጎጂዎች ጋር እንዲገናኙ ጫና እየተደረገባቸው ቢገኝም ያንን ለማድረግ ዕቅድ አልያዙም።
ፕሬዝዳንቱ ከኤፕስታይን ፋይሎች ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ተቃውሞ እያጋጠማቸው ቢሆንም፤ የኤፕስታይንን ስም በማንሳታቸው አምባሳደሩን ማንም አያመሰግናቸውም።
ሰር ክርስቲያን በታህሳስ ወር ነበር በአሜሪካ የዩኬ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በሰጠው መግለጫ “እነዚህ የግል፣ መደበኛ ያልሆኑ ወደ አሜሪካ ለተጓዙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው።”
“የዩኬን መንግሥት አቋም የሚያንጸባርቁ አይደሉም።”
