ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጀምስ ኮሜይ

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ባጋሩት ምስል የትራምፕን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣል ዝተዋል በሚል ተከሰሱ።

አቃቤ ሕግ፣ ኮሜይ ላይ ያቀረበው ክስ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ለአጭር ጊዜ አጋርተውት ከነበረው ምስል ጋር የሚገናኝ ነው።

ጄምስ ኮሜይ በወቅቱ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ አጋርተውት የነበረው “86 47” የሚል ቁጥርን የሚያሳይ በሼል በባሕር ዳርቻ ላይ የተሰራ ምስል ነበር።

ኮሜይ ቁጥሮቹ ምን ማለት እንደሆኑ እንደማያውቁ የተናገሩ ቢሆንም ትራምፕ እና ሌላ የአስተዳደራቸው ባለሥልጣን ልጥፉ የ47ኛው ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበ ማስፈራሪያ ነው ብለዋል።

“ሰማኒያ ስድስት” ማለት ‘በአራዳ ቋንቋ’ “ማስወጣት” ወይንም “ማስወገድ” የሚል ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ማክሰኞ ዕለት በቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ የሰጡት ኮሜይ “አሁንም ቢሆን ንፁህ ነኝ። ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም። አሁንም ገለልተኛ በሆነው የፌደራል የፍትሕ ስርዓት አምናለሁ” ብለዋል።

ክሱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓታል እንደ ቀድሞ የኤጀንሲው ዳይሬክተርነታቸው ኮሜይ “እንዲህ ዓይነት ልጥፎችን ማጋራት የሚስበውን ትኩረት እና የሚያስከትለውን ቅጣት ሙሉ በሙሉ ያውቃሉ” ብለዋል።

“ጀምስ ኮሜይ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ሕይወትን አደጋ ላይ መጣልን በአሳፋሪ ሁኔታ በማበረታታ እንዲሁም ዓለም እንዲያየው በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ አጋርተዋል” ሲሉ ወንጀለዋቸዋል።

የቀድሞውን የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ ከዚህ ቀደም ለኮንግረስ የሰጡትን ምስክርነት ተከትሎ በሁለት ወንጀሎች ተከስሰው ነበር።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቺ የሆኑት ኮሜይ እአአ በ2020 መስከረም ወር ላይ ሚስጢራዊ መረጃን ለሚዲያ ተላልፎ እንዲሰጥ ፈቅደዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ለኮንግረስ በሰጡት ምስክርነት ላይ ዋሽተዋል ተብሏል።

ከሁለት ወር በኋላ የፌደራሉ ዳኛ ጊዜያዊ የፌደራል አቃቤ ሕግ ክሱን ለማቅረብ በአግባቡ አልተወከሉም በሚል ውድቅ አድርገውታል።

የአሜሪካ ደህንነት ቢሮ ሠራተኞች ስለ ፎቶዎቹ ኮሜይን ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር ማነጋገራቸው ታውቋል።

ኮሜይ የኢንስታግራም ልጥፋቸውን ያጠፉት “በሼሎቹ የተጻፉት ቁጥሮች የፖለቲካ መልዕክት ያላቸው ስላልመሰለኝ ነው” ብለዋል።

“አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ቁጥሮች ከአመጽ ጋር ያገናኙታል ብዬ አላሰብኩም” ያሉት ኮሜይ “ለእኔ አልመሰለኝም፤ ነገር ግን ማንኛውንም አመጽ የማልደግፍ በመሆኑ ልጥፎቹን አንስቻቸዋለሁ” ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል።

ኮሜይን በመተቸት የሚታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ግን “ይህ ምን ማለት እንደሆነ ሕጻን እንኳን ያውቃል” ሲሉ አስተያታቸውን አጋርተዋል።

ኮሜይ ክሱ መመስረቱ በይፋ ከታወቀ በኋላ በሰጡት አስተያየት “እንግዲህ ተመልሰዋል። አሁን ደግሞ የመጡት ከዓመት በፊት በካሮላይና የባሕር ዳርቻ አሸዋ ላይ በሼል የተጻፈ ጽሑፍ በማጋራቴ ነው። ይህ መጨረሻው አይሆንም። ነገር ግን በእኔ ዘንድ የተቀየረ ነገር የለም” ብለዋል።

ኮሜይ ትራምፕን በማስፈራራት እና ማስፈራሪያውን በማኅበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ወንጀሎች ተከስሰዋል። ሁለቱም ወንጀሎች እያንዳንዳቸው እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣሉ።

“የፕሬዚዳንቱን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣል ማስፈራራት የአገራችን ሕክ ክፉኛ መጣስ ነው” ያሉት ደግሞ ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ቶድ ብላንቼ ናቸው።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ኮሜይ በፌደራል አቃቤ ሕግ እአአ በ2020 ለኮንግረስ በሰጡት የምስክርነት ቃል ዋሽተዋል እንዲሁም የኮንግረሱ ምርመራ ላይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ክስ ተመሰረቶባቸው ነበር።

ክሱ የተመሰረተባቸው ዶናልድ ትራምፕ ኮሜይን ጨምሮ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ የአገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲያካሄዱ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።

ኮሜይ በጥቅምት ወር ችሎት ፊት ሲቀርቡ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን በመናገር የተከራከሩ ሲሆን በኅዳር ወር ክሱ ውድቅ ተደርጓል።

ዳኛ ካሜሮን በቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ላይ ክስ የመሰረቱት የአቃቤ ሕጓ ሊንድሲ ሃሊገን ሹመት “ተቀባይነት የሌለው” ነው በማለት ክሱን ሰርዘዋል።

በወቅቱ የሊንዚ ሃሊገን ሹመት ጊዜያዊ ዐቃቤ ሕጎች የሚሾሙበትን መንገድ የሚደነግገውን የአገሪቱን ሕግ የጣሰ ነው ሲሉ ዳኛዋ ተናግረዋል።

ሃሊጋን ከዚህ በፊት የዋይት ሐውስ ረዳት የነበረች ሲሆን የወንጀል ክስ መሥርታ አታውቅም።

ዳኛው መንግሥት በክሱ መቀጠል ከፈለገ በሚል ክፍት አድርገው ትተውት ነበር።

ኮሜይ ዳግመኛ በዚህ ጉዳይ እንደሚጠየቁ ያላቸውን ጥርጣሬ ሲናገሩ ትራምፕ “ዳግመኛ ክስ ሊመሰርትብኝ ይችላል” ብለው ነበር።

ኮሜይ ከኃላፊነታቸው የተነሱት እአአ በ2016 በተደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት ላይ የተደረገውን ምርመራ በመምራታቸው ነው።