
ከ 5 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን የአገራቸው ወታደሮች ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ በዩክሬን ጦር ላለመያዝ በሚል ራሳቸውን ማጥፋታቸውን አወደሱ።
ኪም ወታደሮቹን “ታላቅ ክብርን ለመጠበቅ ያለምንም ማመንታት ራስን ማጥፋትን የመረጡ… ” መሆናቸውን በመግለጽ “ጀግኖች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ከዩክሬን ጋር ሲዋጉ ቦምባቸውን በማፈንዳት ራሳቸውን የገደሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በማወደስ ለረዥም ጊዜ ሲጠረጠር የቆውን የጦር ሜዳ ፖሊሲ አረጋግጠዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ በዚህ ሳምንት ባደረጉት ንግግር “ታላቅ ክብራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ራሳቸውን ለማጥፋት የመረጡት ጀግኖች” ናቸውን ብለዋል።
ደቡብ ኮሪያ ቢያንስ 15 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ዜጎች ሩሲያ የምዕራባዊ ኩርስክን ክፍሎች እንድትቆጣጠር ለመርዳት መላኳ የሚገምት ሲሆን እስካሁን ከ6,000 በላይ የሚሆኑትም ተገድለዋል። ፒዮንግያንግም ሆነች ሞስኮ ቁጥሩን አላረጋገጡም።
የስለላ ተቋማት እና የከዱ ወታደሮች በዩክሬን ከመያዝ ይልቅ ራሳቸውን እንዲገድሉ በፒዮንግያንግ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
“ራሳቸውን መስዋዕት በማድረጋቸው የሚጠብቁት ምንም ካሳ ካለመኖሩም በላይ ለቁርጠኝነታቸው ምንም ሽልማት አያገኙም… ይህ የሠራዊታችን የታማኝነት ከፍታ ማሳያ ነው” ሲሉ ኪም ሰኞ ዕለት በፒዮንግያንግ ለተሰዉት ወታደሮች የቆመውን የመታሰቢያ ሐውልት ሲመርቁ መናገራቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሆነው ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር አንድሬይ ቤሎሶቭ እና የሩሲያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ቪያቼስላቭ ቮሎዲን በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት መካከል ነበሩ።
በሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ዘንድ መማረክ የክህደት ተግባር ተደርጎ ይቆጠራል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን፣ ኤምቢሲ፣ በዩክሬን ጦር ቁጥጥር ስር የዋሉ ሁለት የሰሜን ኮሪያ የጦር እስረኞችን የሚያሳይ ፕሮግራም ባስተላለፈበት ወቅት አንደኛው የራሱን ሕይወት ባለማጥፋቱ እንደተጸጸተ ተናግሯል።
“ሌሎች ራሳቸውን አጥፍተዋል። እኔ አልተሳካልኝም” ሲልም ተናግሯል።
የሴኡል ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት ባለፈው ዓመት ይህንን ተግባር የሚያመለክቱ መረጃዎችን ከሞቱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ማስታወሻዎች ላይ እንዳገኙ ገልጿል።
ኪም ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር በጦርነት የሞቱትንም አመስግነዋል።
እአአ በሰኔ 2024 የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም በሁለቱ አገራት ላይ “ጥቃት” ቢደርስባቸው አገራቸው እርስ በርስ እንደሚረዳዱ ቃል የገቡበትን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ኪም ስምምነቱን “ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንካራ” ሲሉ በወቅቱ አወድሰውታል።
ወታደሮችን ከመላክ በተጨማሪ ሰሜን ኮሪያ ኩርስክን እንደገና ለመገንባት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን እንደምትልክ ቃል ገብታለች።
