
ከ 6 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ
የአውሮፓ አገራት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ውስጥ እንደማይሳተፉ ካሳወቁ በኋላ የትራንስአትላንቲት አገራት ግንኙነት እንደ አዲስ ሻክሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመገናኛ ብዙኃን ቃለ መጠይቆቻቸውን እና የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎቻቸውን በመጠቀም በተደጋጋሚ በአውሮፓውያን አጋሮቻቸው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። አሜሪካን ለአስርት ዓመታት ከዘለቀው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንደሚያስወጡ ጭምር ዝተዋል።
በድርጅቱ የመከላከያ በጀት እና በዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት ውስጥ አሜሪካ ያላት ድርሻ ከፍተኛ ነው። አሜሪካ ከጥምረቱ የምትወጣ ከሆነ የአውሮፓ አገራት ያለ ዋሽንግተን ወታደራዊ ድጋፍ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ማሳየት ይችላሉ?
ለምን ነበር ኔቶ የተቋቋመው?
ወታደራዊው ጥምረት በአውሮፓውያኑ 1949 የተቋቋመው እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ፈረንሳይ ባሉ 12 አገራት ነው።
ከአባል አገራቱ መካከል አንዳቸው የሚጠቁ ከሆነ ራሱን እንዲከላከል ሌሎቹ አገራት ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።
የዚህ ጥምረት መቋቋም ዋና ዓላማ ሩሲያ የበላይ በሆነችበት እና የኮሚኒስት ሪፐብሊኮችን የያዘችው ሶቪየት ኅብረት ወደ አውሮፓ እንዳትስፋፋ መግታት ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1991 ሶቪየት ኅብረት ከፈረሰ በኋላ በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ጥምረቱን ተቀላቅለዋል። አልባኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሀንጋሪ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስሎቫኪያ፣ ሮማኒያ፣ ሉቲኒያ፣ ላትቪያ እና ስቶኒያ የኔቶ አባል የሆኑ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ናቸው።
ለአስርት ዓመታት ገለልተኛ አገር ሆነው የቆዩት ሲውድን እና ፈረንሳይ ደግሞ ሩሲያ ዩክሬን ላይ በሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ በ2022 አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል።
ወታደራዊው ጥምረት በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ 32 አገራትን በአባልነት ይዟል።
ኔቶ የራሱ የሆኑ ሠራዊት የለውም። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ቀውስ በሚያጋጥምበት ወቅት አባል አገራት የጋራ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ።
የኔቶ ኃይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ውጊያ ውስጥ የገቡት በአውሮፓውያኑ 1994 የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች ቦሲኒያ ውስጥ የአየር ድብደባ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የሰርቢያ አውሮፕላኖችን መትተው በጣሉበት ወቅት ነው።
ጥምረቱ በአሁኑ ሰዓት እያካሄደ ካለው ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች መካከል ሜዲትራኒያንን ለመጠበቅ የሚደረገው ‘ኦፕሬሽን ሲ ጋርዲያን’ እንዲሁም በኢራቅ የሚገኘው የኔቶ ተልዕኮ ይገኙበታል። የኢራቁ ተልዕኮ አሁን በቀጣናው በተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት መቀመጫውን በኔፕልስ አድርጓል።
ዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ሳይሰጠው ቆይቷል።
ጥምረቱ የኒውክሌር መሣሪያ ከታጠቀችው ሩሲያ ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ሲል በዩክሬን ወታደሮችም የማሰማራት ወይም በአገሪቱ የአየር ክልል በረራ እንዳይኖር ከበረራ ነፃ ቀጠና የማቋቋም እርምጃን አልወሰደም።
ይሁን እንጂ አባል አገራቱ ለዩክሬን የጦር መሠሪያዎችን እና ትጥቆችን አቅርበዋል።

የአውሮፓ የመከላከያ አቅም
ኔቶ ወታደራዊ ጥምረት እንደመሆኑ ጠንካራ አቅም አሰባስቧል። እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ግን የአሜሪካ ተሳትፎ ከሌለበት ጥምረቱ ኃይለኛ ተቀናቃኞችን የመከላከል አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ይሳሳል።
እስከ ታህሳስ 2025 ድረስ ባለው 68 ሺህ ገደማ የአሜሪካ ወታደሮች በአገሪቱ 31 ጦር ሰፈሮች እና በሌሎች 19 ወታደራዊ ስፍራዎች ውስጥ በቋሚነት መስፈራቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
በአሜሪካው አትላንቲክ ካውንስል የ’ትራንስአትላንቲክ ሴኪዩሪቲ ኢኒሼቲቭ’ ዳይሬክተር ሆኑት ዶ/ር ቶሪ ታውሲግ፤ “በአሁኑ ሰዓት በመደበኛ እና በኒውክሌር ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ ለኔቶ የገባችው ቁርጠኝነት የማይተካ ነው” በማለት ይከራከራሉ።
ዳይሬክተሯ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ውስጥ የአውሮፓ ጉዳዮች እና ኔቶን በተመለከቱ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችን ላይ ሰርተዋል።
አውሮፓ ያለ አሜሪካ ድጋፍ እንደ “ስትራቴጂክ የወታደራዊ ማጓጓዝ፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ የክትትል እና የስለላ አቅሞች እንዲሁም የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓቶች” ባሉ ወሳኝ ዘርፎች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚቸገር ለቢቢሲ በኢሜል በሰጡት ምላሽ ላይ ገልጸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ግላስጎው በሚገኘው የስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ደኅንነት መምህር የሆኑት ዶ/ር ጋቪን ሀልም በተመሳሳይ አሜሪካ የምትወጣ ከሆነ የአውሮፓ ደኅንነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አንስተዋል።
ሀል፤ “አሜሪካ የሌሎች የኔቶ አባላት አቅም የጀርባ አጥንት ሆና ትቀጥላለች” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አውሮፓ አገራት የመጀመሪያው ምዕራፍ ወታደራዊ ኃይል የማሰባሰብ እና የማሰማራት እርምጃ አውሮፓ እና የኔቶ አባላት ላይ ስለሚወድቅ ያለ አሜሪካ እርዳታ ከፍተኛ ወታደራዊ አቅም መገንባት እንደሚጠበቅባቸው መረዳታቸውን ይገልጻሉ።
“እንደ የባልካን አገራት የአየር ክልል ጥበቃ፣ የሜዲትራኒያን የባሕር ላይ ጥበቃ ያሉ የኔቶ ዘመቻዎች በአብዛኛው የሚያከናውኑት ያለ አሜሪካ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው” ሲሉም ያስረዳሉ።

የኔቶ አባላት የመከላከያ ወጪ ምን ያህል ነው?
ትራምፕ ጥምረቱ እና ከዚህ ቀደም የመከላከያ ወጪን ማሳደግ አለመቻሉ ላይ ትልቅ ጥርጣሬ አላቸው።
በ2024 ለሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው የምረጡኝ ዘመቻ በሚያደርጉበት ወቅት፤ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ሩሲያ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸው ሁለት በመቶውን ለመከላከያ የማይመድቡ የኔቶ አገራትን እንድታጠቃ እንደሚያበረታቱ መናገራቸው አወዛግቦ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2014 ኔቶ ሁሉም አባል አገራት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸው ቢያንስ ሁለት በመቶውን መከላከያ ላይ እንዲያውሉ ጠይቆ ነበር። 2025 ላይ ሁሉም አባል አገራት ይህንን ግብ ማሳካት ችለዋል።
አባል አገራቱ አሁን የተቀመጠላቸው ግብ በ2035 ለመከላከያ የሚመድቡትን በጀት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸው ውስጥ አምስት በመቶ እንዲሆን የሚል ነው።
የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው የኔቶ አገራት በ2024 ለመከላከያ ወጪዎች ይዘው ከነበረው ጠቅላላ በጀት ውስጥ 66 በመቶ ያህሉ የአሜሪካ ነው።
ዶ/ር ቶሪ ታውሲግ የአውሮፓ አገራት የመከላከያ በጀታቸውን ማሳደግ ለምን ግዴታ እንደሚሆንባቸው ያስረዳሉ።
“አሜሪካ የኔቶ ዋና መሥሪያ ቤትን፣ ወታደራዊ ዕዝን እና መሠረተ ልማቶችን ለመደገፍ ከሚውለው የኔቶ የጋራ በጀት ውስጥ 15 በመቶ ያህሉን ታዋጣለች። አጋር አገራቱ የመከላከያ ወጪያቸውን እያሳደጉ ቢሆንም አሜሪካ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ የምታቆም ከሆነ ከዚህም የበለጠ [በጀት] ያስፈልጋል” ይላሉ።

ኔቶ ከሩሲያ አንጻር ምን ያህል የመከላከያ አቅሙን እያሳደገ ነው?
2023 ላይ የኔቶ ወታደራዊ አዛዦች ሩሲያ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ፣ በመካከለኛው አውሮፓ ወይም በሜዲትራኒያን ቀጣና ልትፈጽም የምትችላቸውን ጥቃቶች ለመቀልበስ የሚያስችል ዝርዝር እቅድን በተመለከተ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ጥምረቱ ከዚያ አንድ ዓመት አስቀድሞ ደግሞ በአውሮፓ የሚገኙ እና ከፍተኛ ዝግጁነት ላይ ያሉ ወታደሮች ቁጥርን ከ40,000 ወደ 300,000 ለማሳደግ ማቀዱን አስታውቆ ነበር።
በተጨማሪም ከሩሲያ ጋር በሚያዋስነው የምሥራቃዊ ግንባር እንደ አስፈላጊነቱ መጠናቸው እና ስብጥራቸው የሚለያይ ስምንት የውጊያ ቡድኖችን በማሰማራት የመከላከል አቅሙን አጠናክሯል።
ኔቶ በየሦስት ዓመቱ ከ32ቱ የኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ 90,000 ወታደሮች የሚሳተፉበትን እና ግዙፉን ‘ስቴዲፋስት ዲፌንደር’ የተባለ ወታደራዊ ልምምድ ያካሂዳል። ቀጣዩ ወታደራዊ ልምምድ በ2027 እንዲካሄድ እቅድ ተይዟል።
ሀል፤ “በቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ኔቶ መከላከል የመከላከል ተግባሩን ሊወጣ ይችላል። ለዚህም ግን ግልጽ የሆነ አመራር እና አቅጣጫ ያስፈልገዋል” ይላሉ። የኒውክሌር አቅሙን ማሳደግ እንደሚኖርበትም በአጽንኦት ያነሳሉ።
ፈረንሳይ እን ዩናይትድ ኪንግደም የኒውክሌር መሣሪያ ታጥቀዋል። ነገር ግን ሁለቱ አገራት ያላቸው የኒውክሌር መሣሪያ ድምር ከሩሲያ ክምችት ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው።
የአውሮፓ አገራት አስቀድሞም ቢሆን የመጀመሪያ ጥቃትን ለመመከት እና ፈጣን ስምሪት ለማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ እቅድ እያዘጋጁ ነው። ይሁን እንጂ ሀል ይህ ዝግጅት ለረጅም ጊዜ ሊቆይ መቻሉ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
“አስከፊው” መቆራረጥ
የአሜሪካ ጦር ወታደራዊ ታክቲኮችን መሻሻል እና የወታደራዊ ኃይሎችን በቅንጅት የመሥራት አቅምን ለማሳደግ ከሚያግዙ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ወታደራዊ ልምምዶችን ከአውሮፓ አጋሮች በመደበኛነት ያካሂዳል።
አሜሪካ የኔቶ አባል መሆኗ ሠራዊቷ አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወታደራዊ ሠፈሮችን ያለ እንቅፋት እንዲጠቀም ያስችላታል።
የ’ትራንስአትላንቲክ ሴኪዩሪቲ ኢኒሼቲቭ’ ዳይሬክተሯ ዶ/ር ቶሪ ታውሲግ፤ “ኔቶ ከሌለ አሜሪካ በእነዚያ አገራት ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከአገራቱ ጋር በሁለትዮሽ ደረጃ የመከላከያ ትብብር ስምምነቶችን መፈረም ይኖርባታል” ይላሉ።
አሜሪካ አሁንም ቢሆን ከበርካታ የአውሮፓ አገራት ጋር በተናጠል ስምምነት መፈረሟን የሚያስታውሱት ዳይሬክተሯ፤ ይህም ቢሆን ግን የመከላከያ ትብብር ስምምነት ካልደረሰችባቸው አገራት ጋር መፈራረም ሊያስፈልጋት እንደሚችል ያስረዳሉ።
እንደ ዶ/ር ታውሲግ ገለጻ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደዛቱት ከኔቶ የሚወጡ ከሆነ እርምጃው ወታደራዊ እና ፖለቲካ መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም።
“በፖለቲካ ረገድ አሜሪካ ከጥምረቱ ጋር መቆራረጧ በትራንስአትላንቲክ አንድነት እንዲሁም ኔቶ በሩሲያ እና በሌሎች ጠላቶች ላይ የሚያንጸባርቀው የመከላከል አቅም ላይ አስከፊ ጉዳት ያመጣል” ሲሉ ዶ/ር ታውሲግ ያስጠነቅቃሉ።
ኔቶ ለአሜሪካ የደኅነንት ዋስትና ከማስገኘቱ በተጨማሪ ዋሽንግተን አውሮፓ ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖራት ማድረጉን ይጠቅሳሉ።
“የኔቶ አንቀጽ 5 የጋራ መከላከያ ስርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው አሜሪካን ለመከላከል እንደነበር መዘንጋት የለብንም” የሚሉት ዶ/ር ታውሲግ፤ ይህ እርምጃ የተወሰደበት ዋነኛ ምክንያት “አሜሪካ ኔቶ እንደ ታማኝ አጋር መታየቷ” እንደነበር ይናገራሉ።
አገራት አንዳቸው ሌላኛቸውን ለመከላከል እንዲዘምቱ የሚደነግገው አንቀጽ 5 ተግባራዊ የሆነው በአውሮፓውያኑ መስከረም 11/2001አሜሪካ ውስጥ ከተፈጸመውን የሽብር ጥቃት በኋላ ነበር።
የዓለም አቀፍ ደኅንነት መምህሩ ዶ/ር ጋቪን ሀል በበኩላቸው ትራምፕ ከኔቱ እንደሚወጡ ያስፈራሩት መጠቅለል እንደሚፈልጓት ግሪንላንድ ወይም እንደ ንግድ ባሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የመደራደር አቅማቸውን ለመጨመር እንደሆነ ይጠረጥራሉ።
ከአሜሪካ ከጥምረቱ የምትወጣ ከሆነ ሁለቱም ወገኖች እንደሚጎዱም ያክላሉ።
“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የገነባውን የአውሮፓና አትላንቲክ ደኅንነት የማይነጣጠል ነው የሚለውን እምነት ያፈርሳል። የአውሮፓ ደኅንነት ከአሁን በኋላ አሜሪካን እንደማያሳስባት እና በአውሮፓ ደኅንነት ላይ የሚመጡ ለውጦች በአሜሪካ ጥቅም ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖራቸው የሚያውጅ ይሆናል” ሲሉም የሚያስከትለውን መዘዝ አስረድተዋል።
