ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

አምቡላንስ

ከ 1 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም ቼሸር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሺዓ እስልምና አባል ነን በሚሉ አማኞች ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ምክንያት በተካደሄ በሰፊ ዘመቻ ሰዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

በሃይማኖቱ ተከታዮች ውስጥ በሚደረግ ጾታዊ ጥቃት፣ የግዳጅ ጋብቻ እና ዘመናዊ ባርነት ተንሰራፍቷል በሚል የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ዘመቻ ዘጠኝ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ በሦስት ቦታዎች ከ500 በላይ የጸጥታ አካላት ተሰማርተዋል።

ሃይማኖታዊ ቡድኑ አሃማዲ የሰላም እና የብርሃን ሃይማኖት ይባላል። ይህ ሃይማኖታዊ እሳቤ ከአውሮፓውያኑ 2000 መጀመሪያ አካባቢ በሺያ ሙስሊም ተከታይ አባላት ዘንድ የተጀመረ ነው። ነገር ግን የሺዓ ሙስሊም እምነት አራማጆች አዲሱን ሃይማኖት አይቀበሉትም።

በእነዚህ ራሳቸውን የሺዓ ሙስሊም አካል አድርገው በሚቆጥሩት የአሃመዲ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ጥቆማዎች መሰጠት የጀመሩት ከ2023 ጀምሮ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም የቼሸር ፖሊስ ገልጿል። ፖሊስ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት የሃይማኖቱ ተከታዮች ክሬው በሚባል አካባቢ 150 አባላት አላቸው።

ፖሊስ

ፖሊስ ካሰራቸው ዘጠኝ ሰዎች መካከል ስድስቱ ወንዶች ሲሆኑ ሦስቱ ሴቶች ናቸው። የአሜሪካ፣ የሜክሲኮ፣ የጣሊያን፣ ስፔን እና የብሪታኒያ ዜጎች ይገኙበታል።

ፓሊስ ተጠርጣሪዎቹን ቢይዝም ምርመራ የሚያደርገው ግን ሃይማኖቱ ላይ አለመሆኑን ገልጿል። ከምርመራው ጋር ባይያዝም የማኅበረሰብ መስተጋብርን በመተላለፍ 13 ሌሎች ሰዎችም ታስረዋል።

የሃይማኖቱ ተከታዮች ቼሸር ውስጥ በርካታ ንብረቶችን አፍርተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸዋል። የ30 ዓመቱ ሜክሲኳዊ በግዳጅ ጋብቻ፣ ጾታዊ ጥቃት እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥሯል።