April 30, 2026

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (RSF) የ180 ሀገራትን የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በሚመዘንበት ዓለም አቀፍ ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ 148ኛ ደረጃ አገኘች። የኢትዮጵያ ጎረቤት ኤርትራ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ በዝርዝሩ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች። 

ላለፉት 25 ዓመታት ይህን ዝርዝር ሲያወጣ የቆየው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ የ2026 የፈረንጆች ዓመት ዝርዝሩን ይፋ ያደረገው ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 22፤ 2018 ነው። ድርጅቱ በየሀገራቱ ያለውን የፕሬስ ነጻነት “ጥሩ”፣ “አጥጋቢ”፣ “ችግር ያለበት”፣ “አስቸጋሪ” እና “በጣም አሳሳቢ” ሲል በአምስት ምድቦች ይከፍላቸዋል።

በዝርዝሩ ከተካተቱ የዓለም ሀገራት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ ዓመት “አስቸጋሪ” እና “በጣም አሳሳቢ” ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ ዝርዝሩን ማውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ሀገራት የአሁኑን ያህል ዝቅተኛ ነጥብ አስመዝግበው እንደማያውቁ ገልጿል።  

በየሀገራቱ ያሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አውዶች፣ የህግ ማዕቀፍ እና የደህንነት ሁኔታ፤ ድርጅቱ ደረጃዎቹን ለማውጣት በጠቋሚነት የሚገለገልባቸው መመዘኛዎች ናቸው። እነዚህ ጠቋሚ ሁኔታዎች፤ በጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ከሚደርሱ በደሎች ብዛት አንጻር ይመዘናሉ። 

እንደ RSF ዓመታዊ ዝርዝር ከሆነ፤ ከሰሃራ በታች ካሉ 48 ሀገራት ውስጥ በሃያ አራቱ ያለው የዘንድሮ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ “አስቸጋሪ” በሚባለው ምድብ ውስጥ የሚወድቅ ነው። ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የሰሃራ በታች ሀገራት ያለው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ” እንደሆነ ጠቁሟል።  

በዚህ ምድብ ውስጥ ከተካተቱት ሀገራት መካከል ሶስቱ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ናቸው። በRSF ዝርዝር የመጨረሻው 180ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኤርትራ፣ 167ኛ ደረጃን የያዘችው ጅቡቲ እና ከእርሷ በስድስት ደረጃ ከፍ ብላ የምትገኘው ሱዳን፤ በሀገራቸው ያለው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በተመሳሳይ “በጣም አሳሳቢ” መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል። 

በዚሁ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ሌላዋ ከሰሃራ በታች የምትገኝ ሀገር ሩዋንዳ ነች። የምስራቅ አፍሪካዋ ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ በዘጠኝ ደረጃዎች ከፍ ብላ ብትቀመጥም፤ በተመሳሳይ ምድብ ከመካተት አላመለጠችም። ኢትዮጵያ እንደ ሁነኛ ስትራቴጂካዊ አጋር የምትቆጥራት የተባበሩት አረብ ኤምሬት፤ በዚሁ ምድብ ውስጥ 158ኛ ደረጃ አግኝታለች። የኢትዮጵያ ባላንጣ ተደርጋ የምትወሰደው ግብጽ ከጅቡቲ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ 169ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከኤርትራ ከፍ ብለው በዝርዝሩ የመጨረሻዎቹን ሶስት ደረጃዎች የያዙት ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ኢራን ናቸው። ለዜጎቿ መረጃ የማግኘት መብትን ለመስጠት “በጽኑ አሻፈረኝ ብላለች” በሚል በድርጅቱ የተወነጀለችው ኤርትራ፤ ጋዜጠኛን ለረጅም ጊዜ በእስር በማቆየትም ከዓለም ሀገራት ቀዳሚ ነች።

የስዊዲን ዜግነት ያለው ትውልደ ኤርትራዊው ዳዊት ይስሃቅ በኤርትራ ከታሰረ ዘንድሮ 25ኛ ዓመቱን ይዟል። ተመስገን ገብረ እየሱስ፣ ስዩም ተሾመ እና አማኑኤል አስራት ከተባሉ ባልደረቦቹ ጋር የታሰረው ዳዊት፤ በህይወት ይኑር ወይም ይሙት ለረጅም ጊዜ ሳይታወቅ ቆይቷል። 

የስዊዲን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ባለፈው ታህሳስ ወር ኤርትራን ከጎበኙ በኋላ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ማልመር ስቴይኑርጋርድ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መረጃ፤ የእነርሱ ግምገማ ጋዜጠኛው “በህይወት እንዳለ” መሆኑን ተናግረው ነበር። በጉብኝታቸው ወቅት ይህንኑ የሚቃረን አዲስ መረጃ አለማግኘታቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በወቅቱ አስታውቀዋል።

አራት ጋዜጠኞች ከሽብር ጋር በተያያዙ ክሶች ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የታሰሩባት የኢትዮጵያ ጉዳይም፤ የህግ ጉዳዮችን በሚመለከተው የድርጅቱ ጠቋሚ መመዘኛ ማብራሪያ ላይ ተነስቷል። ሀገሪቱ “የጸጥታ ጉዳዮችን” በምክንያትነት በማቅረብ፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መቀጠሏን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ጋዜጠኝነትን ወንጀል የማድረግ አካሄድ በብዙ ሀገራት እንደሚስተዋል የጠቆመው ዓመታዊ ሪፖርቱ፤ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ የፕሬስ ህጎችን ወደ ጎን በመተው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌዎችን እና የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን የአላግባብ እንደሚጠቀሙ አብራርቷል። ህጎችን በመጠቀም ጋዜጠኞችን ለመቆጣጠር የሚደረገው ሙከራ ጃፓንን በመሰሉ የአደጉ ሀገራት ጭምር እንደሚስተዋልም ድርጅቱ አክሏል።

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር በ16 ደረጃዎች አሽቆለቆለች። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት

ተሟጋች ድርጅት (RSF) በዓመቱ በሚያወጣው በዚህ ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ያገኘችው ደረጃ 130ኛ

ነው።

ዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/10813/ #WPFD2023

· 6,467Views

የህግ ጉዳዮችን ጨምሮ RSF ዓመታዊ የሀገራትን ደረጃ ለማውጣት በሚጠቅምባቸው መመዘኛዎች፤ ኢትዮጵያ ያገኘችው ነጥብ ካለፈው ዓመት በመጠኑ ዝቅ ያለ ሆኗል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያገኘችው 148ኛ ደረጃም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሶስት ደረጃዎች ቀንሷል። 

ሀገሪቱ ባለፈው 10 ዓመት ውስጥ ጥሩ የሚባለውን ውጤት አስመዝግባ የነበረው በፈረንጆቹ 2020 ዓመት ላይ ነበር። በወቅቱ 99ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረው ኢትዮጵያ በሁለት ዓመት ውስጥ በ15 ደረጃዎች አሽቆልቁላለች። በ2023 የነበረው የ130ኛ ደረጃ በዓመቱ በተጨማሪ 16 ደረጃዎች በመውረድ፤ ሀገሪቱን ከ“አስቸጋሪ” ወደ “በጣም አሳሳቢ” ምድብ አስገብቷታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)