April 30, 2026

ዕለታዊዎቹን “አዲስ ዘመን” እና “ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጦች የሚያሳትመውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በበላይነት ለሚመራው የስራ አመራር ቦርድ፤ ዘጠኝ አዲስ አባላት በዛሬው ዕለት ተሾሙ። በፕሬስ ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ አባልነት ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት ተሹመው የነበሩት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በአሁኑ ሹመት ሳይካተቱ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም በ2011 ዓ.ም የወጣው አዋጅ፤ የተቋሙ ቦርድ አባላት በመንግስት አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ይደነግጋል። በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የዘጠኝ ቦርድ አባላትን ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ፤ ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 21፤ 2018 ለፓርላማ መላካቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከሰነዱ ተመልክታለች።

የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎች እና መመሪያዎች “ለህዝቡ በወቅቱ መተላለፋቸውን” የማረጋገጥ ኃላፊነት በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ተጥሎበታል። ድርጅቱ የሚያሳትማቸውን ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እና የኢንተርኔት ጽሑፎችን ይዘት “መገምገም”፣ “ስለሚሻሻልበትም ሁኔታ ሐሳብ ማቅረብ” ለቦርዱ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ነው። 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚሰጠው አገልግሎት “ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን መገምገም” ሌላው ቦርዱ እንዲያከናውን የሚጠበቅበት ተግባር ነው። የስራ አመራር ቦርዱ ህዝብ ይበልጥ ተጠቃሚ ስለሚሆንበት ሁኔታ “ሃሳብ የማቅረብ” ኃላፊነት እንዳለበትም በድርጅቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። 

ይኸው አዋጅ የተቋሙ ቦርድ “አግባብነት ካላቸው ተቋማት” እና “ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ” አባላትን መያዝ እንደሚጠበቅበት ይደነግጋል። ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሶስት ዓመታት በስራ ላይ የቆየው የፕሬስ ድርጅት ስራ አመራር ቦርድ፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከመንግስት ተቋማት እና ከግል ስራ የተውጣጡ አባላትን በውስጡ ይዞ ነበር። 

ይህንን የስራ አመራር ቦርድ በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ምህረት ደበበ ናቸው። ዶ/ር ምህረት በተሾሙበት ወቅት የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በዚህ ቦርድ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም በአባልነት ሲሰሩ ቆይተዋል።

ዲያቆን ዳንኤል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራር ቦርድ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየት የሚስተካከላቸው የለም። በ2010 ዓ.ም.፣ በ2012 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም. በተሰጡ ሹመቶች የድርጅቱ ቦርድ አባል የነበሩት ዲያቆን ዳንኤል፤ በአሁኑ ሹመት ሳይካተቱ ቀርተዋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነታቸውን ቢለቅቁም፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የስራ አመራር ቦርድን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ መሾማቸው አይዘነጋም። ይህ የስራ አመራር ቦርድ፤ ብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጣቢያዎችን በስሩ የሚያስተዳድረውን ኢቢሲን በበላይነት የሚመራ አካል ነው።

የህዝብ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን እና ልዩ ልዩ ጽሁፎችን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች “የማዘጋጀት፣ የማሳተም እና በመላ ሀገሪቱ የማሰራጨት” ኃላፊነት የተጣለበትን የፕሬስ ድርጅት የስራ አመራር ቦርድን በሰብሳቢነት እንዲመሩ በዛሬው ዕለት የተሾሙት ወ/ሮ ብሌን ማሞ ናቸው። ወ/ሮ ብሌን “ሆርን ሪቪው” የተሰኘ መገናኛ ብዙሃንን ከጥቅምት 2017 ዓ.ም ጀምሮ በስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩ ናቸው።

“ሆርን ሪቪው” በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ እና ደህንነት ላይ የሚያተኩር “ገለልተኛ የምርምር እና የሕትመት ተቋም” እንደሆነ በተሿሚዋ የስራ ልምድ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል። ወ/ሮ ብሌን የ“ሆርን ሪቪው” ህትመቶች ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር “ስትራቴጂክ ዳያሎግ” (strategic dialogue) የተባለ ፖድካስት ዋና ፕሮዲዩሰር እንደሆኑም ተመልክቷል።

አዲሷ ተሿሚ ካለፈው ወር ጀምሮ በኢቢሲ የውጭ ቋንቋዎች መምሪያ ስር የሚገኘውን የ“ኢትዮጵያ ድምጽ” (Voice of Ethiopia) ፕሮጀክት እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎቱን “ፐልስ ኦፍ አፍሪካ” (Pulse of Africa) መገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው። የሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ወ/ሮ ብሌን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ለንደን ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ደህንነት እና ዓለም አቀፋዊ አስተዳደር ይዘዋል። 

እንደ ወ/ሮ ብሌን ሁሉ በአማካሪነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ አፈወርቅ በደዊም፤ የፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ተሹመዋል። በCenter for Responsible and Peaceful Politics (CRPP) የሚዲያ ለሰላም ፕሮግራም ዋና አማካሪ የሆኑት አቶ አፈወርቅ፤ በኢቢሲ በሚተላለፈው “የሀገር ጉዳይ” ፕሮግራም ቋሚ ተንታኝ መሆናቸው በስራ ልምዳቸው ላይ ተጠቅሷል።  

በዛሬው የቦርድ ሹመት ከተካተቱት ውስጥ የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ አመራሮች ይገኙበታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፤ በዚህ ምድብ ውስጥ ያሉ ናቸው።

የማህበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ የሆኑት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታዋ ፈዲላ ቢያ ሌላዋ አዲስ የቦርድ አባል ናቸው። በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊነት የሆኑት ፈዲላ፤ የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍንም በምክትል ፕሬዝዳንትነት ይመራሉ። 

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሹመት ደብዳቤ ላይ “ማህበራዊ አንቂ፣ የበጎ አድራጎት እና ተግባቦት ተሳታፊ” መሆናቸው የተገለጹት አቶ መሀመድ ካሳም፤ አዲሱን የፕሬስ ድርጅትን የስራ አመራር ቦርድ ተቀላቅለዋል። አቶ መሀመድ በኪነጥበብ፣ በቴአትር፣ በፊልም፣ በሙዚቃ እና በሚዲያ ፕሮግራም ዝግጅት እና አመራር ዘርፍ “ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያ” መሆናቸው ለፓርላማ አባላት በተሰራጨው የስራ ልምዳቸው ላይ ተጠቅሷል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲሱ ተሿሚ በማህበራዊ አገልግሎት እና በበጎ አድራጎት ስራቸውም ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳያስ ካሳ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ Chief Portfolio Officer ወ/ሮ አስማ ረዲ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ዮናስ በቀለ ቀሪዎቹ የፕሬስ ድርጅት ቦርድ ተሿሚዎች ናቸው።

የእነዚህ የቦርድ አባላት ሹመት ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 20፤ 2018 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ ጸድቋል። ዘጠኙም አዲስ የቦርድ አባላት በዚሁ ስብሰባ ላይ በአካል ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)