ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ኦኒየም የዩጋንዳ እና የአሜሪካ ዜግነት አለው

ከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአንድ ወር በፊት ላይ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በሚገኝ የሕጻናት ማቆያ ውስጥ አራት ጨቅላዎችን የገደለው ግለሰብ በስቅላት እንዲቀጣ ተፈረደበት።

የ38 ዓመቱ ክሪስቶፈር ኦኬሎ ኦኒየም በጊባ ወደሚገኝ የጨቅላ ሕጻናት ማቆያ ውስጥ በመግባት ኤቴኩ ጊዲዮን፣ ኬሻ አጌኖርዎዝ፣ ​​ሴሩያንጅ ኢግናቲየስ እና ኦዴኬ ራያን የተባሉ በአንድ እና በሁለት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት በስለት ወግቶ ገድሏል።

በኡጋንዳ የሞት ቅጣት ባይወገድም አልፎ አልፎ የሚፈጸም ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜተመሳሳይ ፍርድ የተሰጠው እአአ በ2005 ነበር።

የኡጋንዳ እና የአሜሪካ ዜግነት ያለው ኦኒየም ውሳኔው ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ 14 ቀናት አሉት።

አቃቤ ሕጎች ወንጀሉን አምኖ እንደተቀበለ እና ሀብታም እንደሚያደርገው ተስፋ ያደረገውን “የሰው መስዋዕትነት” መፈጸሙን መግለጹን ለችሎቱ ተናግረዋል።

ሆኖም በኋላ ላይ ጥፋተኛ እንዳልሆነ በመግለጽ ሆን ተብሎ የተፈጸመ መባሉን ክዷል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት የአእምሮ ሕመም እንደነበረበት እና የመግደል ዓላማ እንዳልነበረው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብተው ጠይቋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አሳዛኝ ግድያው በተፈጸመበት ማኅበረሰብ ውስጥ በተቋቋመ ጊዜያዊ ፍርድ ቤት ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ አሊስ ኮሙሃንጊ ካውካ፤ ኦኒየም በጥቃቱ ቀን “በጣም ጤናማ” እንደነበር ተናግረዋል።

“በዚህም የሞት ቅጣት እፈርድበታለሁ” ሲሉ ሕዝቡ ደስታውን ገልጿል።

“መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ዒላማ አድርጎ እንደ እንስሳት ገድሏቸዋል… ምንም ፍርሃት፣ እፍረት ወይም ለሰው ሕይወት ምንም ግድ አልነበረውም” ሲሉ ዳኛ ካውካ መናገራቸውን የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

“ወንጀለኛው ምንም ዓይነት ጸጸት አላሳየም ከማለት ባለፈ ቢያንስ ለሕጻናቱ ቤተሰቦች ይቅርታ እጠብቅ ነበር።”

በችሎቱ ወቅት አቃቤ ሕግ 18 ምስክሮችን አቅርቦ በፎረንሲክ፣ በዲጂታል እና በዓይን ምስክሮች ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ክርክር አደርጓል።

ከዋና ዋና ማስረጃዎች መካከል ኦኒየም ለግድያ የተጠቀመበት ቢላዋ ላይ ያለው ዲኤንኤ፤ ከጥቃቱ በፊት እንቅስቃሴውን የሚያሳይ በደህንንት ካሜሪ የተቀረጸ ምስል እና በቦታው ሆኖ ያደረገው የስልክ ጥሪ ተካተዋል።

ሁለት የሕጻናት እንክብካቤ ሠራተኞችም ታዳጊዎቹን ሲያጠቃ እንደተመለከቱ በፍርድ ቤት መስክረዋል።