Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ·Follow
የስቶክሆልም አደባባዮች በነጻነት ድምፅ እየተናወጡ ነው፤ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት የሚቃወመው ዓለም አቀፍ ሰልፍ በደመቀ ሁኔታ ቀጥሏል!
በኢትዮጵያ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀልና አገዛዙ ሊያካሂደው ያቀደውን የይስሙላ ምርጫ ለመቃወም በስዊድን መዲና ስቶክሆልም የተጀመረው ታላቅ ሰልፍ አሁንም በደመቀ ሁኔታ ቀጥሎ እንደሚገኝ ታውቋል።
በስዊድን የአማራ ማኅበራት አንድነት ግብረኃይል አማካኝነት የተጠራው ይህ ሰልፍ፣ ከቀኑ 13:00 (7:00 ሰዓት) ጀምሮ ከሁምሌ ጋርደን (Humlegården) በመነሳት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት እየተከናወነ ይገኛል።
ሰልፈኞቹ “በዘር ማጥፋት መካከል ምርጫ የለም!” የሚሉ ጠንካራ መፈክሮችን በማንገብ የአብይ አህመድ አገዛዝ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያጋለጡ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት የዘለቀው የዘር ማጥፋት ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆምና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአገዛዙ ላይ የዲፕሎማሲ ጫና እንዲያሳድር ሰልፈኞቹ በጽኑ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ሰልፉ አሁንም በስቶክሆልም ጎዳናዎች ላይ ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ ኖራ ባንቶርጌት (Norra Bantorget) በማምራት ላይ ባለው በዚህ ታላቅ ሰልፍ ላይ ተሳታፊዎች የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማና የትግሉን ዓላማ በማንገብ “ትግላችን እስከ ነጻነት ይቀጥላል” የሚል የጽናት ድምፅ እያሰሙ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። #MinilikSalsawi



